Tidarfelagi.com

March 8 – ሴቶች የሚነቆሩበት ቀን

አንድ አድራጎት አስደማሚ የሚሆነው አድራጎቱ በዓለም ላይ “የመጀመሪያ” ሲሆን አልያም የአድራጊው ድርጊቱን መፈጸም ከአዕምሮ በላይ ሲሆን ነው… የኖረና የነበረን ጉዳይ እጹብ ድንቅ አድርጎ መሸላለም ግን አንድም ለአድራጊው የተሰጠን ዝቅተኛ ግምት አልያም ድርጊቱን ለማመናፈስ የተደረገን ጥረት ያሳያል…
___
አውሮፕላን በሴቶች ሲበር የመጀመሪያ አይደለም… የመጀመሪያ እንኳን ቢሆን ድንቅ አይደለም… ድንቅ እንኳን ቢሆን ድንቁ ከስሪቱ እንጂ ከኦፕሬሽኑ አይመነጭም… ሙያው የተከበረ መሆኑ ባይካድም ከመምህርነትም ሆነ ከሕግ ባለሙያነት የተለየ ግን አይደለም… ሁሉም ሙያ የየራሱ risk & responsibility አለውና… እናም አይወዳደርም… ስለዚህ ‘በሴቶች ብቻ የሚበር…’ ምናምን እያልክ ነገሩን ስታራግበው መልዕክቱ ሴትነትን ዝቅ የማድረግ ቶን ይጫነዋል… ይህን የምልህ Pessimist ሆኜ አይደለም… በጭራሽ… የሴቲቱን ስኬት በአድናቆት ሰበብ ወደ ወንዱ በሚስብ ማሕበረሰብ መሃል ስላደግሁ የገባኝን ነው የነገርኩህ… ‘ወንዳታ’ እያልኩ ‘በጨው ደንደስ በርበሬን ሳወድስ’ በመኖሬ የተገለጠልኝን ሰምና ወርቅ…
___
ጥያቄዬ ተግባሩን ወንዶች ሲፈጽሙት ካልገረመ ሴቶች ሲከውኑት ለምን ይደንቃል ነው… ሴቶችም ሰው ናቸዋ… ያውም የወንድ እናት… ይህ ተግባር በውሾች ቢከወን በተፈጥሮ ስጦታቸው ስላልሆነ ያስደንቃል… ሴት ግን ሰውነቷ እንጂ ሴትነቷ ስለማይነዳው አጃኢብ አያሰኝም… ችግሩ እኛ ሴትነትን የምናይበት መነጽር ከመሰረቱ ችግር ያለበት ነው… እንጂማ መደነቅ ያለበት አየር መንገዱ ሴቶችን የሚያይበት ዓይን ሚዛናዊነት እንጂ ሴቶች ያለ ወንዶች ድጋፍ አውሮፕላን ማብረራቸው አልነበረም…
___
አይበለውና በበረራው ላይ አንዳች ችግር ቢፈጠርስ?… ‘ድሮም ሴቶች…’ ልትል ነው? በሰላም ደረሱ… እሺ… ‘ወንዳታ’ ማለትህስ ረብ አለው?… ይልቅ… አንዳንድ አድናቆቶቻችን ውስጥ ራስን የማስወደስ ስውር ቅኔ ይታየኛል… የተግባሩን ክብደት ከፍ የምናደርገው እኛ እንደ ወንድ ያለንን ‘ብቃት’ ለማግዘፍ ጭምር ነው… ‘አያችሁ… ይህን ከባድ ተግባር ነው ስንከውን የኖርነው’ ለማለት…
___
ሴትና ወንድን ‘እኩል’ ለማለት የምንመርጠው መንገድ የተግባር ሚዛን ያሰረው መሆኑ በራሱ ቀሽምነቱን ያሳያል… ሴት ልጅ ማሕበረሰቡ ‘ለወንድ ብቻ’ የሚለውን ስራ ስለሰራች እኩል አትሆንም… ይልቅ ቀድሞ መቃናት ያለበት አስተሳሰቡ ነው… ወጌሻ የሚሻው የአመለካከት ስብራቱ ነው… እናም ነባሩን በመተቸት ተጠምደን ሳይሆን አዲስ ሞዴል በመገንባት ታትረን ትናንትን በዛሬ ማስረጀት ይኖርብናል ባይ ነኝ…
___
ወንድነት የጾታ መደብ እንጂ የእልቅና እርካብ አይደለም… ሴቶች ብዙ አውቀው ትንሽ በመናገር ሲደበቁ ወንዶች ጥቂት አውቀው ንግግር በማሳመር ሲሰብቁ እየተዛባ የመጣ ሚዛን አለ… ቀላል ምሳሌ ልስጥህ… ወንድና ሴት እየተቀባበሉ እንዲመሩት በሚጠበቅ የሬዲዮ ወይም የቲቪ ዝግጅት ላይ የሚሆነውን ልብ ብለሃል?… ሴቶች ‘አጫፋሪ’ እንጂ አጋፋሪ አይደሉም… ‘እህ…’ ‘እሺ…’ ‘ልክ ነው…’ ወዘተ እንዲሉ እንጂ ተገንዝቦዋቸውን እንዲሰነዝሩ ዕድል አይሰጣቸውም…የጀመሩትን ሃሳብ እንኳ ከአፋቸው ነጥቆ የሚጨርሰው ወንዱ ነው… ለምን?… በሴቷ ላይ እምነት መገንባት ስላልለመደ…ገራሚው ግን እዚሁ የበላይነቱን ባነገሰባት ስቱዲዮ ውስጥ ቁጭ ብሎ ‘ለመጀመርያ ጊዜ በሴቶች ብቻ የሚበር…’ ይልሃል… ሃሃሃ
___
ምን ለማለት ነው?… የእኩልነትን እውነት በቅን በአስተሳሰብ ቅኝት እንጂ በዕለት ተግባር ፍኖት አያሰርጹትም!!
_____________
ክብር ለሴትነት!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...