Tidarfelagi.com

[ዛሬ ቀን 11/12/13]

💥 ዛሬ ቀኑ 11 ወሩ 12 ዘመኑ ሁለት ሺ 13 (11/12/13) ነው። በዘመን ቀመር ቀን፣ ወር፣ ዓመት በአጻጻፍ 11/12/13 ሲደረደር ለዘመን ቀመር ተመራማሪ እጅግ ያስደስታል። ዛሬ በ11/12/13 ከጓደኞቼ መካከል ልደታቸውን የሚያከብሩ ነበሩና 11/12/13 ብለው ጽፈው በመመልከቴ ለእነርሱ የመልካም ልደት መታሰቢያ እንዲሆን የቁጥሩ መንፈሳዊ ቀመር ትርጓሜን 11/12/13 ጻፍኩት ሌሎቻችሁም ለዕውቀት ብታነቡት ደስ ይለኛል።
💥ቊጥር 11💥
👉 ቊጥርን ለሚመረምሩ ሰዎች 11 የውሳጣዊ ግጭት፣ ዐመጽ፣ ተቃውሞ፣ የፍርድ ምሳሌ ያደርጉታል።ምክንያታቸውም ቊጥር 7 እና 10 ፍጹም ቊጥርን ወካይ ናቸው። ለምሳሌ 7 የሳምንቱን ፍጹም ዑደትን የያዘና የፍጹም ሰው መሆን ቁጥር 4 ባሕርያትና 3 ባሕርያተ ነፍስ 4+3=7ሲሆን፤ ቊጥር 10 ደግሞ የአምላክ 10ሩን ትእዛዛት፣ ወካይ ነው።
ቀጣዩ 11 ግን ይህንን ፍጽምነትን የሚያጐድል፣ ሕግን የመሻር፣ የመደበላለቅ፣ የቀውስ ምሳሌ ተደርጎ በቀመር አጥኚዎች ይታያል።
👉 ቁጥርን ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የሚያራቅቁ ሊቃውንት ስለ 11 ሲገልጹ በኦሪት ዘፍጥረት 11ኛው ምዕራፍ ላይ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ አምጸው ሕግ አፍርሰው ታላቅ ግንብ እንደገነቡ ተጽፏል። በመጨረሻም ቋንቋቸውን እንደበታተነባቸውና ሕንጻቸውም እንደፈረሰና ቦታውም የመደበላለቅ መሠረት የሆነ “ባቢሎን” እንደተባለ ይገልጻልና 11 ይህንን የመደበላለቅ ወካይ ነበር ይላሉ።
👉 በተጨማሪም የአምላክን አገልጋዮች ይቃወሙ የነበሩ 11 ነገሥታት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መግለጻቸውን ይጠቅሳሉ።
💥 በዚህም ላይ ስመ አምላክ የሆነው “አልፋ ወኦ ቤጣ የውጣ” እያንዳንዳቸው ሲደመሩ 10 ፊደላት ናቸው። ይህንን የእግዚአብሔርን ስም የሚሳደበው 11ኛው ቀንድ ነው ይላሉ። ይኸውም በትንቢተ ዳንኤል በ10ሩ ቀንዶች ከተመሰሉ 10ሩ ነገሥታት በኋላ ሕግን ስለሚለውጠው፣ የእግዚአብሔርን ስም የሚሳደበው 11ኛው አደገኛው ቀንድ (ንጉሥ) ይጽፋልና ቀመር 11 ሕግን የመሻር ምልክት ይሉታል (ዳን 7፡24)።
💥 በተጨማሪም 11 ሰዓት (ሠርክ) የመጨረሻ ሰዓት ወይም የምጽአት የፍርድ ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል። ምክንያቱም ሰው በዚኽ ዓለም ሥራውን ሲሠራ ውሎ የቀን ደሞዙን የሚቀበል በ11 ሰዓት እንደኾነ ኹሉ ሰውም በአምላኩ ዘንድ የሥራውን የመጨረሻ የፍርድ ዋጋ የሚያገኘው በዓለም ፍጻሜ ነውና 11 ይህንን ይወክላል።
💥 በቤተ ክርስቲያን የትርጓሜ መጻሕፍት ውስጥ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከተሠጡት 2 ጠባቂ መላእክት ውስጥ የቀኑ ሲወጣ የሌሊቱ ሲመጣ በ11 ሰዓት ላይ መላእክት የሚለዩ ስለሆነ በቀላሉ በ11 ሰዓት ላይ ሰው በሰይጣን ሊፈተን ስለሚችል በዚች ሰዓት በቤተ ክርስቲያን የ11 ሰዓት ጸሎት እንዲጸለይ እንደታዘዘ ተጽፏል።
💥 በተጨማሪም 11 ሰዓት ከተፈጸመ ከ12 ሰዓት በኋላ ሌላ ቀን ነውና የመጨረሻና የማካተቻ የሰዓት ቁጥር 11 ነው።
💥 11 ጒድለትን ወካይ ነውና ሐዋርያትም ይሁዳ በወጣ ጊዜ 11 ሆነው ጎድለው ነበር በኋላ ማትያስ ገብቶ 12 ኾነው ሙሉ አደረገው እንጂ።
💥 ጌታም ስለሕዝቡ ኃጢአት መከራ የተቀበለውና የሞተው በ33 ዓመቱ ነው ይህም (3 x 11) ማለት ነው።
💥 በታሪክ አንጻር የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ያለቀው በ11ኛው ሰዓት በ11ኛው ቀን በ11ኛው ወር ሲሆን፤ ከቅርቡ ደግሞ ሴፕቴምበር 11 በአሜሪካ በደረሰው የሽብርተኞች ጥፋት ከ3000 ሰዎች በላይ የሞቱበትና ከ6000 በላይ የተጎዱበት ይታወሳል።
[ቊጥር 12]
💥 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 12 ቊጥር የእግዚአብሔርን ፍጹም ሥልጣን፣ የረቂቁም የግዙፉም ሥነ ፍጥረት ውበትና ቀመር የተገለጸበት አስገራሚ ቊጥር ነው። ለምሳሌ ብናይ፡-
👉12ቱ ነገደ እስራኤል
👉 12ቱ ሐዋርያት
👉 12ቱ ሰዓታተ መዓልት
👉 12ቱ ወራቶች
👉 12ቱ መናዝል (መገብተ አውራኅ ከዋክብት)
👉 12ቱ መላእክት
👉 12ቱ ምዕዛረ ፀሐይ
💥 መንፈሳዊቷ ዓለም ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ስናይ ያላት፡-
👉 12 ደጃፎች
👉 12 ጠባቂ መላእክት
👉 12 መሠረቶች
👉 ስማቸው የ12ቱ ነገደ እስራኤል የ12ቱ ሐዋርያት የተጻፈባት
👉 ስፋትዋ 12 ሺሕ ምዕራፍ
👉 ቅጥርዋ 144 ክንድ (12 x 12=144)
👉 ደጃፎችና የተሠሩባቸው 12ቱ ዕንቁዎች
👉 ከታላቁ መከራ የተረፉት 144,000 ሰዎች (12 x 12=144) ወይም 12 x 12,000=144,000
👉 የታነጸችው በ12ቱ የከበሩ ድንጋዮች ነው (ራእ 21)።
ሌላው የ12 መንፈሳዊ ቀመር
👉 ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ የኖረችበት ዓመት 12፤ ጌታችን በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ምሁራኑን ጥያቄ የጠየቀመበት ዕድሜው12 ነው።
👉 ሰውን ሰው የሚያሰኙት ሌሎችም ፍጥረታት የተዋቀሩባቸው 4ቱ ባሕርያት እያንዳንዳቸው ያላቸው 3ት ግብራት ሲደመር 12 ነው (3×4=12)።
👉 የጥንት የማያ ሕዝቦች የዘመን ቀመር የተጠናቀቀው ታኅሣሥ 12 በ2012 ዓ.ም.
👉 አስገራሚው ቀለበታማ የፀሐይ ግርዶሽን ያየነው ሠኔ 14 በ2012 ነበረ። ከዚህ በመቀጠል ስለ 13 ጥቂት ላንሳ
[ቊጥር 13]
👉 አንዳንዶች ተመራማሪዎች ቊጥር 13 በተቃራኒው ዐመጽን፣ ፈተናን፣ ዕልቂትን የሚወክል ቊጥር እንደሆነ የሚገልጹ አሉ። ለዚህም በዮሐንስ ራእይ 13ኛው ምዕራፍ የሚገልጸው ከባሕር ስለወጣው አውሬ ይጠቅሳሉ።
👉 ሌሎች ሊቃውንት የኢትዮጵያን ጨምሮ 13 ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ቃል ኪዳንን ይወክላል እንጂ ጥፋትን አይደለም ይላሉ። ለምሳሌ ፍቅር (ahavah) እና አንድነት (echad) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል አኃዛዊ ቀመሩ 13 ነው። በእኛም “ሰላም” የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ቀመረ ፊደል አወጣጥ፡-
ሰ፡- 7
ላ፡- 2
ም፡- 4 ድምሩ 13 ይሆናል። ለዚህ ነው አለቃ አስረስ የኔሰው በመጽሐፋቸው ላይ ሄዋን የሰላም ቊጥር አላት ብለው ሲገልጹ፡-
ሄ ፦ 1
ዋ ፦ 60
ን ፦ 30
በአንድ ላይ ሲደመር 91 ይሆናል። ይህን 91 ለ7 ስትመድበው 13 ሰንበት ይገኛል 91÷7=13 ስለዚህ 13 ቊጥር “ሰላም” ነው። የሰላም ቊጥር 13 ነውና የሚሉት።
👉 13 ቃል ኪዳንን ሲወክል አብርሃም ዘሩ ይበዛለታልና በ86 ዓመቱ እስማኤልን ወለደው (ዘፍ 16፡16)። በ99 ዓመቱ እግዚአብሔር ተገልጾ ለብዙዎች አባት እንደሚሆንና ሳራም ልጅ እንደምታገኝ ቃል ገባለት (ዘፍ 17፡1)። ቃሉ በተገለጸበትና ቃሉ በተሰጠው መካከል ያለው ዓመት 13 ነው። 99-86= 13 ይሆናልና የቃል ኪዳን ምልክት ይሉታል።
👉 በተጨማሪም ጌታችን በጸሎተ ኀሙስ ዐዲሱን ቃል ኪዳን ሲመሠርት 13 ነበሩና 13 የቃል ኪዳን መደምደሚያ ነው ይላሉ።
💥 በመጨረሻ 1+1+1+2+1+3=9
💥ለማንኛውም እኔ ለጓደኛዬ ልደት መታሰቢያ ይህንን ያህል በ11/12/13 ዙርያ ከጻፍኩ እናንተ ደግሞ ተራቀቁበት።💥
መጋቤ ሐዲስ ዶከተር ሮዳስ ታደሰ በ11/12/13 ላይ ጻፈው።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...