Tidarfelagi.com

ዝክረ- ኳራንታይን

ከወረርሽኙ መባቻ አንስቶ፤ ‹‹ብትችሉ ከቤት ንቅንቅ አትበሉ›› ከተባለ ጀምሮ፣ መደበኛ የቢሮ ስራቸውን በቢጃማ፣ ቢያሻቸው ሶፋቸው፣ ቢላቸው አልጋቸው፣ ሲያምራቸው መሬት ተቀምጠው በርቀት እንዲሰሩ ከተፈቀደላቸው፣ እድል ከቀናቸው ጥቂት አዲስ አበባዊያን መሃል ነኝ።

እግሮቼን ከሰፈር ሳልርቅ ለማፍታታት ወጣ ከማለት፣ ወጥ ወጥ፣ ቤት ቤት የማይል አየር ለመተንፈስ በረንዳ ብቅ ከማለት እና ስንቅ ለመግዛት እዚህችም እዚያም ከመታየት ከማለት ውጪ በገዛ ፈቃዴ የቤት እስረኛ ሆኜ ነው የሰነበትኩት። እንደ ሁሉ ሰው ሲሻው ከፍ በሚለው የህመምተኛ ቁጥር ስሸበር፣ ዝቅ ሲል ደግሞ የልብ ልብ ሲሰማኝ ነበር። ግን ከቤት አልወጣሁም። እንጀራዬን ከቤት ሆኜ በኮምፒውተር ማብሰል ከቻልኩ ምን አቅብጦኝ በሽታ ሸመታ እወጣለሁ?

የቀን ከቀን ሕይወቴ ተመሳሳይ ነው። የጊዜዬ አከፋፈሉም ብዙ የማይቀያየር ነው። ከመቶው ብዙውን እጅ የቢሮ ስራ፣ የተረፈውን ሙዚቃ እና ንባብ፣ ሌላውን ደግሞ ‹‹ርቀትን ጠብቆ›› የሚከናወን የትዝብት ሰአት ይወስደዋል።
ይህ አጭር ወግ የዚህ ሁሉ ቅልቅል ነው።

የቢሮን ስራ ከቤት
ምስጋና ለኢንተርኔትና የብዙ ሃገራት ዜጎች የቢሮ ስራን ከቤት ሆኖ መስራትን መለማመድ ከጀመሩ አመታት አለፈዋል። እነሱ በደህና ጊዜ ተለማምደውታል። ለእኔና ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግን አዲስ ነው። ቢሮ በር ላይ አሻራዬ ካልተወሰደ፣ ስራ ለመከታተል ሳይሆን በሰአት መግባቴን፣ ቀድሜ አለመውጣቴን ለማረጋገጥ የሚፈልገው አለቃዬ ቢሮዬ በር ላይ ካላንጃበበ፣ ‹‹አንዴ ትመጪ?!›› ብሎ የፋይል ክምር ከዴስኩ አንስቶ ክንዴ ላይ ካልጫነ፣ በውስጥ መስመር የሚጠራ የድንገቴ ስብሰባ ካላዛገ፣ በሳምንታዊ የሰአታታት ስብሰባ አእምሮዬ ካልዛለ…ምኑን ሰራሁት ብለን የምናስብ ትንሽ አንመስለኝም።

ከቤት የመስራት እድል ጥብቅ ዲሲፕሊን እና ‹‹አዩኝ አላዩኝ›› ሳይሉ ካንጀት የመስራት የሞራል ብቃትን እንደሚጠይቅ አስተምሮኛል።
ከቤት መስራት….አብረውኝ ከሚሰሩ ሰዎች ውስጥ አንዳንዶቹ እንኳን ከቤት ከቢሮም አይሰሩምና ስልካቸውን አጥፍተው፣ ባለ ክፍያ ቫኬሽን እንደወጣ ሰው እልም ሲሉ አይቼበታለሁ። ።
የቢሮ ታታሪነታቸው በቤት ምቾት ጎልብቶ ሌሊት ዘጠኝ ሰአት ላይ ዘጠኝ ኢሜይል የሚልኩ የስራ ባልደረቦቼን አውቄበታለሁ።

ከሚንጫጩ ህጻናት ልጆቻቸው ጋር እየታገሉ፣ አሁንም አሁንም እየመጣች ከምትረብሻቸው የቤት ሰራተኛ ጋር ‹፣ሻሼ! ስብሰባ ላይ ነኝ አልኩሽ እኮ!›› እያሉ የዙም ስብሰባን በትጋት የሚታደሙ ባልደረቦቼን ለይቼበታለሁ።
ዙም ስብሰባ ተጀምሮ ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ፣ በተለይም አለቃቸው ‹እንትኑ ምን ደረሰ?›› ብላ ስትጠይቅ ‹‹ኢንተርኔቴ አስቸገረ…›› ‹‹መስመሩ ጥሩ አይደለም›› ብለው እብስ የሚሉ፣ ስብሰባው ከማለቁ ቲክቶክን ሳይ ግን የፈረደበት ትልቅ መቀመጫቸውን ለካሜራው አይን ሰጥተው በዚያ በፈረደበት ሱዳንኛ ዘፈን የሚያንቀጠቅጡ ሴቶች መሃከል አንዷ ገፅ ላይ ‹‹ቆንጅዬ! እኔ እኮ ይሄ ቂጥ እንዴት እንደሚያስቀምጥሽ ነው የማላውቀው! እንዴት ነው የማያነጥርሽ?›› ብለው አስተያየት የሚተዉ አይናውጣ ሰራተኞችንም አስተውያለሁ።

ትዳር
በኳራንታይን መጀመሪያ ላይ ‹‹ይሄ ጊዜ ጥቁር ካባ ለብሶ የመጣ መልካም ጊዜ ሊሆን ይችላል›› ተባብለን ደስ ያለን ባለትዳሮች ትንሽ አይደለንም። ‹‹ጊዜ ማግኘት ችግራችን ነበርና በቤታችን አብረን ስንውል ፍቅራችን ይጎለብታል፣ ትዳራችን ያብባል። እሰየው! ከመጣ አይቀር እንጠቀምበት›› በሚል የጋለ ስሜት የተከርቸሙን ጊዜ የጀመርን ብዙ ነበርን።
ቀኑ በዝቶ፣ ሳምንቱ ተባዝቶ፣ ጊዜው ረዝሞ ወደ እብደት አፋፍ እስክንደርስ ፣
‹‹ለምን ይሄን ሰውዬ አገባሁ…ምን ቆርጦኝ ይህችን ሴት ለትዳር መረጥኩ?›› እስክንል ድረስ።
…የአስራ ምናምን አመታት ባለትዳር ሴቶች፣ ‹‹ስንጋባ የሰጠኝ ጥሎሽ በቂ አልነበረም›› ብለናል።
ባለትዳር ወንዶች የልጆቻቸውን እናት ማየት ታክተው፣ መስማት ሰልችተው‹‹ ኤዲያ! ያቺኛዋን ልጅ ባገባ ይሻለኝ ነበር›› ሲሉ ተደምጠዋል።
‹‹ሳይተዋወቁ ይጋባሉ፣ ሲተዋወቁ ይፋታሉ›› የሚለው የደረሰባቸውማ ቤታቸው ይቁጠራቸው።
የብዙዎቻችን መልካም ባሎች ኳራንታይኑ ሲጀመር ከእኛ ጋር ሊያሳልፉ በሚችሉት ጣእም ያለው የፍቅር ጊዜ ሰክረው ኡመር ካየምን ሳይጠቅሱ አልቀሩም።
አለ አይደል! ፡ ‹‹ የወይን ጽዋዬን በእጄ ይዤ እየተጎነጨሁ፣ የማፈቅራትን ልጅ ከጎኔ አድርጌ እየሳምሁ…ምን ሊጎልብኝ…? እንኳን ወር አመት ተከርቸም ቢሉኝ ምን ገዶኝ…?›› አይነት ነገር።
ሚስቶችስ ከእነሱ በምን አንሰን? በደበበ ሰይፉኛ. …‹‹የማይገኝ እድል ነው የገጠመን ውዴ! ..ከእንግዲህ ስንሳሳም የመጨረሻችን…ስንተቃቀፍ የመሰነባበቻችን እንደሆነ አስበን ብንኖር ሕይወት ጣእሟ ልዩ ይሆናል…ነገ ወደ አሰልቺው ሕይወታችን ልንመለስ እንችላለና ይህችን ጊዜ እናጣጥማት…አፍታዋን ዘልአለም እናድርጋት ›› አይነት ነገር ሳንቀኝ አልቀረንም።
ለብዙዎቻችን እውነትም የመጀመሪያው የኳራንታይን ሳምንት ልክ የጫጉላ ጊዜያችንን ይመስል ነበር።
‹‹አሁን በዚህች ሰአት እንደኛ የሚፋቀር ባልና ሚስት ስንት ይሆን?›› እያልን እንደ ኡመር ካየም ፍቅረና ጃኻን እንጠይቅ ነበር።
ድንግሎቹ ሲቀነሱ፣ የተሰላቹ ባልና ሚስት ሲወገዱ፣ ላጤዎች ከጨዋታው ሲወጡ ሁለትም አይሞሉ እያልን እንታበይ ነበር።

ጊዜ ግን የጥሩ ነገር ሁሉ ላጵስ ነው።
ልክ ፍቅር ሲጀምር የሚያቃቅርና የሚያራርቅ ነገር እንደማይታየው፣ አብረው የሚሳልፉት ጊዜ በበዛ ቁጥርም መልካሙ እየደበዘዘ፣ ጥቃቅኑ ረባሽ ነገር እያየለ ‹‹ኤጭ እና ኦፋ!›› መባባልን ያመጣል።

‹‹መሽቶ እሰኪነጋ-
እንቅልፍ የለም በዚህ አልጋ ››
ሲሉ የነበሩ ባለትዳሮች ከጊዜ ብዛት፣ አብሮ ከመሆን ውጥረት መተንፈሻ ያጣሉ። ‹‹አንተም በጫፍህ እኔም በጫፌ›› መባባል ይጀምራሉ።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ቢሮ መሄድ ኖሮበት ልነሳ የሚል ባላችንን ‹‹በናትህ ጥለኸኝ አትሂድ›› ብለን ጎትጉተን ‹‹የምሰጥህን አተውቅም›› እያልን ፣ በምናምን አባብለን ያስቀረን ሚስቶች ሶስተኛው ሳምንት ላይ ስንደርስ ‹‹ለነገሩ ሁለት ሶስት ቀን…ግማሸ ቀን ምናምን ..አለፍ አለፍ እያልክ ብትገባ ጥሩ ነው›› ወደ ማለት ተሸጋግረናል።፡ ‹‹ከጓደኛህ ጋር ርቀታችሁን ጠብቃችሁ ወክ ምንምን ብትሄዱም አይከፋም..እንዳትወፍር›› ብለን ከቤት ገፍትረን ያስወጣን ሚስቶችም አለን።
እኔ ለምሳሌ…የኳራንታይኑ ዘመን ከወር አልፎ ለሁለት ወር ሲጠጋ፣ ትላንት ማታ፣ ትሁቱ ባሌ አርፎ ተቀምጦ መፅሃፍ በሚያነብበት ሄድኩና፤
‹‹እኔ የምልህ…›› አልኩት
‹‹እ?›› አለ ቀና ብሎ እያየኝ
‹‹‹እንዲህ ጮህ በለህ መተንፈስ አለብህ ግን?
(ይቀጥላል)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...