Tidarfelagi.com

ፍቅፋቂ

“ዝም! ጭጭ! ጩሐት አይደለም ብትተነፍሺ በዚህ ጩቤ ነው የምዘለዝልሽ!” ብሎ አስፈራርቶኝ ነው እዚህ ሜዳ ላይ ያጋደመኝ።
በዚህ ውርጭ፣ በዚህ ጨለማ፣ ሰው ዝር በማይልበት ጥግ ልብሴን ገፎ ቆዳዬን ከአፈር እያነካካ፣ አጥንቴን ከድንጋይ እያማታ የሚያደርገኝን የሚያደርገኝ በጩቤ አስፈራርቶ ነው።
“ስጋሽን እዘለዝለዋለሁ” አለ?
አሁንስ እየዘለዘለኝ አይደለም?
ባልተዘጋጀሁበት፣ ባልጋበዝኩት የወንድ ጩቤው፣ በዚህ በማላውቀው ሰውነቱ…ስጋዬን እየዘለዘለው አይደለም?
አፌን በአንድ እጁ አፍኖ በሌላው እጁ የተራቆተ አከላቴን በፍፁም ስግብግብነት ይቧጥጣል።
ስስ ቆዳዬን ባልተከረከሙ ግርድፍና ጨካኝ ጥፍሮቹ ይቀረድዳል።
እንደ ሎሚ ይጨምቀኛል።
እንደ ቆሻሻ ልብስ ያሸኛል።
ምን አይነት ሰው ነው…?
ከእኔ የስቃይ ጉድጓድ ደስታን የሚቀዳ፣
ስሜን እንኳን ሳያውቀው፣
መልኬን እንኳን ሳያየው፣ ጓዳ ጎድጓዳዬን ጠርምሶ የገባ ይህ ምን አይነት ሰው ነው?
በእርግጥ አጥንቴን ወደ ፈሳሽነት በሚቀይር መጫን እንዲህ የሚደፈጥጠኝ የሰው አካል ነው?
ማቃሰት እና ማልቀሴን ሳይሰማ በአንዳች ነገር ተነድቶ ከንፈሬን የሚስም ሳይሆን የሚያኝክ ይሄ ሰው ነው?
ሰው ነው…?
የመንፈስ ሰላም በማያስከትል የፍትወት ማእበል ተገፍትሮ ውስጤ የገባው ይሄ ነገር ሰው ነው?
እህ…ወይኔ… ወይኔ !
አመመኝ።
የማህፀኔ ግድግዳ የተደረመሰ መሰለኝ። የሴትነቴ አበባ የረገፈ። አሜኬላ የፀደቀብኝ…እሾህ ብቻ የበቀለብኝ መሰለኝ።
በጋለ ብረት የተቆሰቆስኩ ያህል ተቃጠልኩ።
ወይኔ አመመኝ…
ተደፍጥጬ የተኛሁበት ጠጠርና ድንጋይ፣ አፈርና ሳር ቅጠል ጀርባዬን ይወጋዋል።
እሱ ደግሞ በክምር ሰውነቱ፣ በማያባራ መናጡ…ከላይ ያቆስለኛል።
ምንድነው እየሆንኩ ያለሁት?
ለምንድነው እንዲህ የሚያደርገኝ…?
ለምን…ለምን?
ይሄን የጥያቄ ሀረግ ተከትዬ ስሄድ ከአእምሮዬ ውስጥ ዋናው ሽቦ ተበጥሶ የማብድ መሰለኝ። ራሴን ከእብደት ለመከላከል ስል ያበጀሁት መላ ሌላ ነገር ማሰብ ነው።
በመቀጥቀጡ፣ በመቧጠጡ፣ በመደፍጠጡ፣ በመመታቱ፣ በመወጋቱ መሃከል ስለሌላ ነገር ማሰብ።
አመመኝ…
ለምን አመሸሁ…?ባላመሽ ጥሩ ነበር።
ለእማ እንዴት ብየ እነግራታለሁ?
አባዬማ ከሰማ ደሙ ከፍ ብሎ እዛው ክልትው ይላል….እማ “አታምሺ” ስትለኝ ባላመሽ…ላይብረሪ ባልቆይ ይሄ ሁሉ አይመጣም ነበር…
ለመሆኑ….ለመሆኑ…፤ ይሄን የሰው እንሰሳ…፣ ይሄን ሳልሞት ገሃነም የወሰደኝ ሰው እከሰዋለሁ…?
የት….የሰፈር ፖሊስ ጣቢያ….?ፖሊሶቹ ምን ይሉኛል…? “ለምን በዚያ ሰአት?” ….“ለምን እንዲህ አይነት ልብስ…?”ለምን አልጮኸችም…?“ፈልጋ ነው!” ይሉኝ ይሆን?
የለም :: …አልከስም::
ከሳሽን ተከሳሽ፣
ተበዳይን ጥፋተኛ በሚያደርግ ህግ ፊት አልቆምም።
የተደፋ አንገቴን ይበልጥ ለሚያስደፋኝ አንካሳ ፍትህ እያነከስኩ አልሄድም።
አውልቆ ያልጨረሰው ታይቴ ተረከዜ ጋር ሳይደርስ ተሰንቅሮ ጠፍንጎ ይዞኛል።
አፌን ሲከድን አብሮ የያዘው አፍንጫዬ መተንፈስ ተከልክሎ ፊቴ ላይ ሲያብጥ ይሰማኛል።
አይኖቼ ብቻ በእምባ መስታወት ተጋርደው ይሄን ሁሉ የሚሰራኝን ሰው ለማየት ይሞክራሉ። ግን ጨለማው እንዳይ የፈቀደው ጥላውን ብቻ ነው። ሰውነቴን ሰንጥቆ ከገባው ሰውነቱ ጋር ብድግ ምልስ የሚለው ጭንቅላቱ ጥላ ብቻ ይታየኛል።
“ዋ እጮሃለሁ ብትይ!” አለኝ ደግሞ…። አፍንጫዬን አየር ለማግኘት ከእጆቹ ጥፍነጋ ነፃ ለማውጣት ስጥር ተሰምቶት ነው። እጁ ሲንሸራተት ትጮሃለች ብሎ ፈርቶ ነው።
ግን እንዲህ ያለ ሰው ፍርሃትን ያውቃል?
ሌሎችን የሚያስፈራራ ሰው ይፈራል?
ከገደለ ወዲያ የሚፎክር ሰው ሊፈራ ይችላል?
ወይኔ…ወይኔ…ህመሙ …ቀዶኝ የገባው የሰላ ምናምንቴው ውስጤን ይሞርደኛል።
ያመኛል::
ወይኔ እናቴ! ወይኔ…!
እንዳላብድ ሌላ ነገር ላስብ…
ያቺን ታሪኳ ቡቲክ ያየኋትን ቡትስ ክረምት ሳይገባ በገዛኋት ኖሮ። ውድ ናት ግን በገዛኋት ኖሮ። ቀብድ እንኳን…50 ብር እንኳን ሰጥቻት ብመጣ ጥሩ ነበር። አባዬ ይሞላልኝ ነበር….ከምንም ልብስ ጋር ትሄድ ነበር። በዛ ላይ ትመቻለች። ሱሪ ባደርግ. ቀሚስ ባደርግ….ታይት ባደርግ…
ወይኔ ይሄ ታይት ሰንጎ ይዞኛል። የደም ዝውውሬን አቁሞታል።
ይሄ ሰውዬ አይበቃውም…?
የት ፈልቶ ነው እኔ ላይ ሊሰክን የመጣው…?
ምን አድርጌው ነው የሕይወቴን ብርሃን አለማስጠንቀቂያ ድርግም ሊያደርግ የመጣው ?
ቃልአብስ ምን ይለኛል…?ቃል አብዬ…ያምነኛል…?እንዲህ ሆኜ ነው ብለው ያምነኝ ይሆን…?.ይተወኝ ይሆን…?
አፌን እንዳፈነ ተነሳ።
እኔን ያለሁበት ጥሎኝ አፌን እንዳፈነ በርከክ ብሎ ተነሳ እና ሲሰቀስቁኝ በነበሩ እጆቹ ሱሪውን እየለበሰ ጩቤውን አብለጨለጨና ፤ “እጮሃለሁ ብትይ ተመልሼ ብትንትንሽን ነው የማወጣው!” ብሎኝ ስ…ል…ብ አለ።
ሄደ።
“ተመልሼ እበታትንሻለሁ” ነው ያለው? ምን ቀረኝና ምኔን ተመልሶ ሊመጣና ሊበታትን ነው?
በመሰቅሰቂያ መነሳት እስካስቸግር መሬት ላይ ተበታትኜ እያየኝ እንዲህ ይለኛል…?
የሰአት ግምቴ ጠፋ። ግን መሽቶ የነጋ መሰለኝ።
እዚያው ውዬ አድሬ፣ የሰው ዘር ያላገኘኝ፣ ወይ አግኝቶኝ “ይሀችማ የሰው ጭላጭ ሆናለች…የሰው ቅርፊት…ተዋት እዚሁ በስብሳ ትለቅ….” ብለው የተዉኝ መሰለኝ።
ቤተሰቤም የሆንኩትን ሰምቶ አናውቃትም ያለ፣ አልሰማንም ያለ መሰለኝ..።
የተረፈኝን ሰውነቴን፣ ፍቅፋቂዬን፤ ሰብስቤ ይዤ ቤቴ ስገባ ግን 4.10 ነበር። ይሄ ሁሉ የገሃነም ጉዞ በመደበኛ ሰአት አቆጣጠር አጭር ነበር ።
አዎ….ሕይወቴ እና ማንነቴ ለዘልአለም የተለወጠው የአንድ እጅ ጣት በማይሞሉ ደቂቃዎች ነው።
ቀጫጭን የደም መስመሮች የሸፈናቸው እግሮቼ አላነቃንቅም እያሉኝ ተነቃንቄ፣ አላስኬድም እያሉኝ ሄጄ ፣ ቤቴ እንደገባሁ እናቴን አየኋት።
ቤቴ።
ጠዋት ቤቴ ሳለሁ ንፁህ ነበርኩ።
ጠዋት ቤቴ ሳለሁ ሙሉ ነበርኩ።
እናቴ።
ጠዋት ስትሰናበተኝ ንፁህ ነበርኩ።
ጠዋት ቁርስ አብልታ ስትሸኘኝ ሙሉ ነበርኩ።
ቆዳዬን እንደ ጃኬት …እንደ ቀሚስ አውልቄ ብገባ ተመኘሁ። መርከሰኬን፣ ክርፋቴን ደጅ ጥዬው ብገባ ደስ ባለኝ…
እናቴ “ልጄን…ልጄን! ምን ሆነሽብኝ ነው!…” ብላ ልትይዘኝ ስትጠጋ፣
የሳሎኑ መሬት ላይ ስዘረር እና
“ጎድዬ መጣሁ እማዬ….”
“ጎድዬ መጣሁልሽ…” ስላት እኩል ሆነ።

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...