Tidarfelagi.com

ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል እብሪት ግን ለውድቀት ይዳርጋል

ጎሽ! ጎሽ! እሰይ
—-
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን በየእለቱ እየወደድኩት ነው። ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ያለኝ አድናቆትም እየናረብኝ ነው። ታዲያ አቶ ኢሳያስ ዛሬ ያደረገውን አስገራሚ ነገር ልብ ብላችኋልን? ፊርማውን ሲፈርም እኮ የባድመ ጉዳይ ከቁም ነገር ተቆጥሮ አልተነሳም።

ድሮስ? ድሮማ “ባድመን ካላስረከባችሁን ድርድር ብሎ ነገር የለም” ሲል ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙዎች “ግትር ነው” ይሉት ነበር።

ታዲያ ለብዙ ዓመታት በዚህ አቋማቸው የሚታወቁት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ዛሬ እየሳቁ በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው አላስደነቃችሁም?

አዎን! ያስደንቃል። ከተለያዩ ምንጮቻችን እንደተረዳነው ባድመ ለኢሳያስም ሆነ ለኤርትራ መንግስት ጉዳያቸው አልነበረችም። ጉዳያቸው የነበረው ከወያኔ አቀራረብ ጋር ነው። ጥላቸውም ከወያኔ እብሪት ጋር ነው።

ወያኔ በድንገት ባለቤቷ የረሳትን ኢትዮጵያን በመያዙ ብቻ “ማንም የማይነቀንቀኝ ኃይል ነኝ” በማለት ልቡን አሳብጦ ነበር። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወገኖቻችንን አላግባብ አስጨርሶ ካሸነፈ በኋላ ኤርትራንም እንደ ግል ጓዳው የማድረግ ፍላጎት ነበረው።

በመሆኑም ወያኔ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከሚመራው የኤርትራ መንግስት ጋር ለመቀራረብ ይሞክር የነበረው ራሱን እንደ አይበገሬ ጌታ፣ የኤርትራ መንግስትን ደግሞ እንደ ተዋራጅና ተሸናፊ ሎሌ በማድረግ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ የአልጄርሱን ስምምነት ተፈራርሞ ሳለ “እምቢ ካላችሁ ከዛላ አንበሳ አስመራ ሁለት መቶ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ብቻ ነው! የሁለት ቀን ጦርነት ነው የሚበቃን” የሚል የማስፈራሪያ ነጠላ ዜማም ለቆ ነበር። አልፎ ተርፎም የአቶ ኢሳያስ መንግስት እንደ ሶማሊያ የጦር አበጋዞች እና እንደ ደቡብ ሱዳን መሪዎች አንድ የወያኔ ጄኔራል ሲጠራው “አቤት” የሚል አሻንጉሊት እንዲሆንለት ይመኝ ነበር።
—–
ይህንን የወያኔ እብሪተኛ ባሕሪ የሚያውቁት ኤርትራዊያን ግን እብሪቱን ሊያስተናግዱለት ፈቃደኛ አልነበሩም። በመሆኑም በእርሱ ላይ በሩን ለመዝጋት ሁነኛ አማራጭ ሆኖ የታያቸው “በቅድሚያ ባድመን አስረክቡን” የሚል ሰበብ ማስቀመጥ ነበር። እንደዚህ ይባል የነበረው ወያኔዎቹ ሀሳቡን ለመተግበር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ስለሚያውቁ እንጂ ባድመ የተለየ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጠቀሜታ ኖሮአት አይደለም።

በቃ! የኤርትራ መንግስት ፍላጎት “ወያኔ ከሚባል ጭራቅና ከሃዲ ጋር አልደራደርም” የሚል ነበር። ለዚህም ብዙ ዋጋ ከፍሎበታል። በሀገሩ ላይ አላግባብ የሆነ ማእቀብ ተጥሎበታል። ነገር ግን ወያኔን “አይንህን ለአፈር” እንዳለው ለአስራ ስምንት ዓመታት ቆይቷል።
—–
ዛሬ ሌላ ቀን ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን እብሪትን አምክኖ በቅንነትና በፍቅር ቋንቋ የሚነጋገር መሪ አግኝታለች። በመሆኑም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ በቅንነት ሲቀርበው ለወትሮው ግትር ይመስለን የነበረው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሳቅ እየተምነሸነሸ ፊርማውን ገጭ አደረገለት።
—-
የእብሪተኛ መድኃኒቱ ይኸው ነው። ኢሳያስ፣ አቢይ፣ የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን እብሪት ንደውታል።

ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል። እብሪት ግን ለውድቀት ይዳርጋል።

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...