Tidarfelagi.com

ፍልስፍናህን ኑርበት እንጂ አታውራው!

(“Do not explain your philosophy. Embody it”)

ፈላስፋነት ጠያቂነት፣ መላሽነት፣ መርማሪነት፣ ምክንያታዊነት፣ ጥልቁን አዋቂነት፣ ረቂቁን ተረጂነት፣ እውነትን ፈላጊነት ነው። የፈላስፋነትን ባህሪ መላበስ የሚቻለው በጠያቂነት ሱስ መጠመድ ብቻ አይደለም። አዎ! ፈላስፋነት ድንቅ ጥያቄ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ከባባድ መልሱንም ጭምር መፈለግ ነው። መልስ የሌለው ጥያቄ ፈላስፋነትን አጉል ያደርጋል። ፈላስፋው ራሱ የጠየቀውን ራሱ መልሱን መፈለግ አለበት። ጠይቆ ለመተው ከሆነ የሚጠይቀው ባይጠይቅ ይሻለዋል። ጠይቀው መልስ ያገኙ ፈላስፋዎችን ታሪክ መዝግቦ አቆይቶልናል። ለዚህም ማስረጃችን አድርገን የምንቆጥራቸው ብዙ አሉን።

አንደኛው ፃድቁ አብራሃም ነው። አብርሃም ጠየቀ፤ ጠይቆ ብቻ ዝም አላለም። የጥያቄውን መልስ ለማግኘት አምላኩን ፈለገ። አንዴ ፀሐዩን፣ አንዴ ጨረቃውን፣ አንዴ ነፋሱን፣ ወዘተ አሰሰ። በመጨረሻም አምላኩም ተናገረውና መልሱን አገኘ።

ሁለተኛው ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ነው። እሱም የፈጣሪውን መኖርና አለመኖር ለማረጋገጥ ሲል፡-

‹‹ጆሮን የተከለ አይሠማምን? አስተዋይ አድርጎስ የፈጠረኝ ማነው?›› ሲል ጠየቀ።
ዘርዓያዕቆብ ጠይቆ አልቀረም። ጥያቄውን መረመረ፣ ፍለጋውንም አስከትሎ አንድ መላ ምት ላይ ደረሰ። መላምቱም፡-

‹‹ፍጡር ካለ የግድ ፈጣሪ መኖር አለበት። ምክንያቱም ፍጡር ራሱን በራሱ ሊያስገኝም አይችልምና›› በማለት አመክንዮውን አስቀመጠ። በኋላም ‹‹ተፈጥሮን ያየ እግዚአብሔርን አየ!›› ብሎ የእግዚአብሔርን መኖር በተፈጥሮው አመሳከረ።

በመጨረሻም ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ከብዙ ምርምርና ሕሊናዊ ፍለጋ በኋላ የመጨረሻው ድምዳሜ ላይ ደረሰ። ድምዳሜውም፡-

‹‹እኔ አዋቂ ብሆን ምንድነው የማውቀው? ከፍጥረታት ሁሉ የሚልቅ ፈጣሪ እንዳለ አውቃለሁ!›› ሲል የእግዚአብሔርን ሕላዌነት አረጋገጠ።

እውነት ነው! ተፈጥሮን ያየ እግዚአብሔር መኖሩን ያረጋግጣል። የራሱን ተፈጥሮ ለገመገመ ሰው የፈጣሪን ጥበብ ያደንቃል። በራስ ፀጉሩ ላይ አንዲት ኢምንት ፀጉር ማብቀል የማይችል፣ የኩላሊቱን አሰራር፣ የልቡን አመታት፣ የደሙን ዝውውር፣ የአዕምሮውን አሰራር፣ የስነ-በራሄውን አደራደር ለመረመረ እና የሰው ልጅ በገዛ ተፈጥሮው ላይ የሚካሄደውን አስደናቂ ለውጥ ካጠና ፈጣሪ በእሱ ተፈጥሮ ላይ ሁልጊዜም ከልጅነቱ እስከ መጨረሻ ሕይወቱ ድረስ በጥበብ እንደሚሠራ ይረዳል። በዚህም የፈጣሪን መኖር በገዛ ተፈጥሮው ያረጋግጣል።

እውነተኛ ፈላስፋና ትክክለኛ ፈላስፋነት ሲገናኙ እውነት ታበራለች፣ ዓለም በጥበብ ታሸበርቃች። ፈላስፋ መልካም ቀንን በመልካም ሃሳቡ ይሠራታል። መልካም ጊዜን ወደራሱ ይጎትታል እንጂ ፈላስፋ ጊዜን አይጠብቅም። Philosophers are optimists! ፈላስፋ ዘመኑን የራሱ ያደርጋል። ፈላስፋ ዘመኑን አሳልፎ ለመንጋው አይሠጥም። መንጋውን እየበተነ ራሱን እንዲያሰማራ ያደርጋል። መንጎች እረኞችን ይፈልጋሉ፤ እረኞች ደግሞ የመሪነት ስነልቦና ያስፈልጋቸዋል። ብልህ እረኛ የሌለው መንጋ በደመነፍስ ይነጉዳል። እረኛው በሮጠበት መንጋውም ይሮጣል። ሐቀኛ ፈላስፋ ግን ልክ እንደሶቅራጦስ መንጋው ራሱን እንዲያይና እንዲመለከት ‹‹ራስህን እወቅ›› (“Thy yourself”) ይለዋል።

እውነተኛ ፈላስፋ እውነትን ፍለጋ መባከኑን አያቆሙም። እውነት ብትቀጭጭ ሐሰት ብትፋፋ፤ መልካምነት ጠፍቶ ክፉነት ቢነግስ፤ ገንዘብ ዙፋን ተቆናጥጦ፣ አስተዋይነት ገደል ቢገባም ተስፋው አይሟሽሽም። ተልዕኮው የራሱን የማሰብ ባልቦላ በማብራት አስተዋይነትን፣ ሚዛናዊነትንና ምክንያታዊነትን ወደሰው ልጅ አዕምሮ መመለስ ነው። የጠፋውን የሰውን ልጅ ሰብዓዊነት ወደባለቤቱ ይመለስ ዘንድ ዕውቀትን መቧጠጥ፣ ጥበብን መከተል የፈላስፋ ዋነኛ ስራው ነው።

ፈላስፋ ትክክለኛው ሰውነት እንጂ ትርፍ ነገር አይስበውም። የእሱ ዋና ጉዳይ ሰውነትን አስቀድሞ መረዳት ነው። የፈላስፋ ቁምነገሩ እውነተኛ ሰውነትን ፈልቅቆ ማውጣት ነው። ፕሌቶን ጥበብ እያለህ ለምን ገንዘብ አላከበትክም ቢሉት፡- ‹‹ጥበብ ትክበር ብዬ ነው›› ብሏል። ጥበብን በነፃ መስጠት፣ ዕውቀትን ያለክፍያ ማደል የእውነተኛ ፈላስፋ መለያው ነው። ዘር፣ ጎጥ፣ ብሔር፣ ጎሳ በሚሉት ነገሮች ፈላስፋ አይጠለፍም። ሰውነቱን እንጂ የሚያረቅቀው በብሔሩ አይጠብም። በውስጠቱ ተጠብቦ ይሠፋል እንጂ በመንደር ፖለቲካ አያንስም። ፈላስፋነት ሌሎችን ማሸማቀቅም አይደለም። ፈላስፋነት እኔ አላውቅም እንጂ እኔ አውቃለሁ በሚል ትምክህት የሌሎችን እምነትም ይሁን አመለካከት አያበሻቅጥም። የሌሎችን ያከብራል፣ የራሱንም እውነት ይፈልጋል። ፈላስፋነት ውስጥ ስነምግባር አለ። ስነምግባር የሌለው ፈላስፋ ፈላስፋነት ምን እንደሆነ አልደረሰበትም ማለት ነው። ስነምግባር የፍልስፍና ሀሁ ነው። ሞራል የፍልስፍና ዋና ነው። እነዚህ ላይ ያልረቀቀ ፈላስፋ ፌክ ፈላስፋ (Fake philosopher) ነው።

አዎ ፈላስፋነት ሁሉን አዋቂነት አይደለም። ”Mastering all is mastering nothing” እንዲል ፈረንጅ ሁሉንም አውቃለሁ ብሎ እድሜውን አያባክንም። ሁሉንም አውቆ የጨረሰ የሰው ልጅ የለም። ዕውቀት እንደዱላ ቅብብል በትውልዶች መካከል የምትቀባበል ናት። አቀባባዩ ደግሞ ፈላስፋ ነው። ፈላስፋነት ነገሮችን ሳያረጋግጥ ሌሎች የሚከተሉትን እምነት ይሁን አስተሳሰብ ውሸት ነው ለማለት አይጣደፍም። ድምዳሜው ከምርምሩ የሚመነጩ እንጂ ከደመነፍሱ የሚፈልቁ አይደሉም። ፈላስፋነት በአንድ መስመር ጀምሮ ያቺን መስመር አጥርቶ ማወቅ ነው። በዕውቀቱም በተግባር ሆኖ መገኘት ነው። ፈላስፋነት መሆን እንጂ መምሰል አይደለም። ፈለስፋነት ስለእውነት እንጂ ስለውሸት ግድ የለውም። እርግጥ ነው! ‹‹ውሸት ራሷ የእውነት ማስረጃ ናት›› እንዲል ስፒኖዛ የውሸት መኖር የእውነትን መኖር ተናጋሪ ነው። ፈላስፋነት የጥበብ መንገድን መጀመር እንጂ መጨረስ አይደለም። የጥበብ መዳረሻው ደግሞ እውነት ነው። እውነት የነገር ሁሉ መጠቅለያ፣ የሚስጥራቱ ሁሉ መገለጫ ናት። እውነትን መጨበጥ የፈላስፋነት ግብ ነው!

ታላቁ ጥንታዊ ፈላስፋ ኤፒክቲተስ:-

‹‹ፍልስፍናህን አትግለፅ! ይልቅስ ኑርበት (“Do not explain your philosophy. Embody it”)›› ይላል።

እውነት ነው! ፈላስፋነት አዲስ ሃሳብ ፈጥረን በእውነት መንገድ እየተመላለስን በውስጡ የምንኖርበት እንጂ በዲስኩር ብቻ የምናቀነቅነው አይደለም። ፈላስፋነት ራስን ለለውጥ ማዘጋጀት ነው። ለውጥ የሌለው ማንነት አዲስ ሃሳብ አያመነጭም። ሕይወት ራሷ የለውጥ ውጤት ናት። ሕይወትህን ትለውጥ ዘንድ፣ ማንነትህን በአዲስ ማንነት ታበጃጀው ዘንድ፣ ፍልስፍናን ለበጎ ዓላማ፣ ለመልካም ስራ ታውላት ዘንድ ተፈላሰፍ። በእውቀት ምጠቅ፣ በጥበብ ተነጠቅ! በእውነት እርቀቅ! በእምነት ጥለቅ! ያን ጊዜ ፈላስፋነት ባህሪህ ይሆናል። ፈላስፋነት በማስመሰልና በውሸት መልፈስፈስ አይደለም።

ወዳጄ ሆይ.. ፍልስፍና ባህር ነው። ባህሩ የሚገኘው ከውስጥህ ነው። ውስጥህን ስታገኘው ከባህሩ ጥበብን ትቀዳለህ። በየቀኑም እየጨለፍክ ሠፊውን ዓለም በእውነትና በእውቀት ታለመልማለህ። ስለእውነት በእምነት የእውነት ወዳጅ ትሆን ዘንድ በዕውቀትና በጥበብ ተፈላሰፍ እንጂ በአፍ ብቻ ፍልስፍናን ስሟን አታንጠልጥለው የዛሬው መልዕክት ነው።

ቸር ፍልስፍና!

________________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ረቡዕ ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...