Tidarfelagi.com

‹‹ፉት ሲሉት ጭልጥ››

ዛሬ..
ግንቦት 20 ማለዳ 1.45
ከበራፌ ላይ ቀጭን እና ስለታም ድምፅ ‹‹ልዋጭ! ልዋጭ!›› እያለ ሲጮህ ነቃሁ። የዚህ ሰውዬ ድምፅ በዛሬ ቀን ከነገር ሁሉ ቀድሞ ጆሮዬ ጥልቅ ያለው የቀኑ ማጀቢያ ሙዚቃ ለመሆን አስቦ ይሆን?
‹‹ልዋጭ! ልዋጭ!›› መጮሁን ቀጠለ።
ተነስቼ ወጣሁ።
መደበኛው ትእይንት ተቀበለኝ። ሙሪዳ መዘፍዘፊያ ሙሉ እጣቢ ውሃ ደፍታ ስትመለስ አገኘኋት።
‹‹እንኳን አደረሰሽ!›› አልኳት::
‹‹ለምኑ?›› አለች ግንባሯን አጨማዳ ::
‹‹እንዴ…!ዛሬ እኮ ግንቦት ሃያ ነው ሙሪድ››
‹‹ነገ ደግሞ ግንቦት ሃያ አንድ…!እና ምን ይጠበስ? ›› አለችኝና ወደ ቤቷ ገባች።
ቡና የምጠጣበት ቤት ደረስኩ።
እንደ ተቀመጥኩ መፅሐፍ የሚሸጥልኝ በረከት ከረጅም ጊዜ በፊት ያዘዝኩትን የቆየ መፅሃፍን እንዳገኘ ነግሮኝ- ‹‹ቆይ.. ይዤልሽ ልምጣ‹‹ ብሎኝ ሲሄድ ቡናዬን መጠጣት ጀመርኩ።
ሁለቴ ሳብ እንዳደረግኩ ሌላኛው ቅዳሚያዊ ትእይንቴ ተጀመረ።
ደሬ መጣ። <<ወሰድ ያደርገዋል>>፣ <<ነካ ያደርገዋል >> የምንለው ደረጀ መጣ።
ቅዳሜ ቅዳሜ ምን ሰአት እንደሚያገኘኝ ስለሚያውቅ የሻይ ሊቀበለኝ በለመደው አኳሃን ተጠጋኝ።
‹‹እህስ ደሬ…እንዴት አለህ…?እንኳን አደረሰህ›› አልኩት የወሬ ቱባ ልተረትር።
የደሬ ወሬ ካለ ቡናዬ ስኳር አይፈልግም።
<<አስተማሪ ነበርኩ>> ‹‹ፒኤች ዲ ጀምሬ ነበር›› ይለኛል። ዝርዝሩን ግን ነገሮኝ አያውቅም። ዝርዝሩን አላውቅም።
የማውቀው ጨዋታው ከ 14 ብር ቡና በላይ እንደሚያነቃኝ ነው።
ከማር እንደሚጥመኝ ነው።
አንዳንዴ ደግሞ ከኮሶ እንደሚመረኝ።
‹‹ምን አልሽኝ?››
‹‹እንኳን ለግንቦት ሃያ አደረሰህ!››
‹‹ኤዲያ! እሱን በደንብ የተያዘው ማሳ ላይ ለከረሙት…ለእነዚያ… ለግንቦት ሃያ ፍሬዎች በይ …! ልማቱ እኮ ለእኛ ፉት ቢሉት ጭልጥ ነው…››
‹‹እ?››
‹‹ፉት ቢሉት ጭልጥ…ጢንጥ…ልብ የማይደርስ….››
በግርምት ሳቅኩ።
‹‹ንገረኝ ካልሽማ…›› አለ።
‹‹ንገረኝ በናትህ›› ቶሎ መለስኩ።
‹‹ ንገረኝ ካልሽማ …እንደውም እኛ የግንቦት ሃያ ገለባዎች ነን›› አለኝ።
ተጀመረ።
‹‹የግንቦት ሃያ.ገለባዎች…ህም! ለመሆኑ አንዳንዱ ፍሬ ሲሆን ሌላው እንዴት ገለባ ሆነ!›› ምን ይመለስ ይሆን ብዬ እየጓጓሁ ጠየቅኩት።
‹‹ሲጀመር ተዘርተን እንዳናፈራ ዘራችንን ወስደው ቆልተው በሉታ!። እናም ፍሬ ቢስ ሆነን፣ ተሰባብረን…ቀለን ቀረን›› አለኝ አንገቱን እያከከ።
ወትሮም ንግግሩ ይከብዳል። አንገቱን እያከከ፣ ሳንቲም እየለማመነ፣ ገደድ ብሎ ቆሞ እንደ ዋዛ ሲናገረው የገለባ ያህል ይቀላል እንጂ የደሬ ወሬ ከእርጥብ ጋቢ ይከብዳል።
ዝም አልኩት።
‹‹ይጨመራል…?ላብራራ?…›› አለኝ።
‹‹አብራራ››
‹‹ አየሽ…በዚህ ቀን ምክንያት ስጋ ከሳለ ቢላዋ ጋር የተሰጠው ብዙ አለ…እንደኔ አይነቱ ግን ስጋም ቢላም አልደረሰውም….እከክ ብቻ ነው የደረሰው…እከክ ብቻ። ያውም ጥፍር ሳይሰጠው…ገባሽ…. ?ገባሽ ወይስ ላብራራ?››
ሌሎች ሰዎች ጆሮ መግባቱን ሳውቅ ማቆም ፈለግኩ እና ‹‹ገብቶኛል>> ብዬ የጨዋታውን አቅጣጫ ለመቀየር፤
‹እኔ የምልህ….ዛሬስ ልማቱ ላይ ሸናህ?›› አልኩት እየሳቅኩ።
መንግስት ያሰራው የባቡር ሃዲድ፣ መንገድ ወይ ህንፃ ላይ ሲሸና ‹‹ልማቱ ላይ ሸናሁ›› ነው የሚለኝ።
‹‹ድብን አድርጌ…ዛሬማ አንፎለፎልኩት እንጂ….!››
‹‹የቱ ጋር?››
‹‹ሃያ ሁለት ጋር የተከፈተው አዲስ ሆቴል ጋር….ዛፍ ቢተክሉበት በሁለት ቀን ያድግላቸው ነበር…! ይልቅ ብሩን ስጪኝ ርቦኛል›› አለ ፈጠን ብሎ።
ሰጠሁት።
ጥፍር በሌለው እጁ የሚያሳክከውን ለማከክ እየሞከረ ሄደ።
እስኪጠፋ በአይኔ እየተከተልኩት ሳለ በረከት ከመፅሃፌ ጋር ተመለሰ።
ከፈትኩት።
ልጅ ሆኜ በተደጋጋሚ አነበው የነበረውን የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ግጥምን ማንበብ ጀመርኩ።
‹‹ሊመጣ ነው ሲሉኝ የሰላም የደስታ የጥጋብ ዘመን፣
የት ደርሷል ስላቸው ተቃርቧል እያሉኝ ፣
መች ይመጣልም ስል ተዳርሷል እያሉኝ፣
ይሄው አርባ አመቴ በናፍቆት አለሁኝ ፤
ወይ ዘመኑ መጥቶ በደስታ አላሻረኝ፣
ናፍቆቱ…. ናፍቆቱ … ናፍቆቱ… ገደለኝ ››
የዛሬ ሃያ አምስት አመት የኢህአዴግ ሰራዊት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ትንሽ ልጅ ነበርኩ።
ከሁሉ ትልቁ ወንድሜ እጄን እየጎተተ በታንክ በተሞላው የሰፈራችን አውራጎዳና ይዞኝ ሲሄድ ያየሁት ትእይንት ግን አእምሮዬ ላይ እንደንቅሳት ቀርቷል።
ለሰላምታ የሚውለበለቡ መዳፎች፣
በታንኩ አፍ ላይ የዘንባባ ዝንጣፊ እና አበቦችን የሚሰኩ እጆች፤ ዛሬም ትዝ ይሉኛል።
እልል የሚሉ እንጥሎች አሁንም ይሰሙኛል።
ሆ ሲሉ የነበሩ ጎረምሶች ሁኔታ ዛሬም ይታየኛል።
እነዚያ ለሰላምታ የተውለበለቡ መዳፎች፣
እነዚያ ታንኮችን ወደ አበባ ማስቀመጫነት የቀየሩ እጆች፣
እነዚያ ከእልልታ ብዛት ያልደከሙ እንጥሎች፣
ሆ ባይ ጎረምሶች…
ዛሬ፣ ከሃያ አምስት አመታት በኋላ እስቲ ድገሙት ቢባሉ ይደግሙት ይሆን?
ገጣሚው እንዳለው የናፈቁት የደስታ እና የጥጋብ ዘመን ደርሶላቸው እረክተው ይሆን?
ስንቶቹ የዚህች ቀን ፍሬ ስንቶቹስ ገለባ ነን ብለው ያምኑ ይሆን…
ይሄን እያመነዠኩ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ዋናው አስፋልት ዳር ያለውን ዝነኛ ጠጅ ቤት አየሁት።
ከደለቡ ዝምቦች በስተቀር ሰው የለውም።
አጠገቡ ያለው ትልቅ ግቢ አጥር፤ ‹‹ሰላም ›› የሚል ቃል የበዛበት መፈክርን ከጥግ ጥግ የያዘ ባነር ተሰቅሎበታል።
‹‹እውነተኛ ሰላም የጦርነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን የፍትህ መኖር ነው›› ያለው ማን ነበር…?
ጠጅ ቤቱ እረጭ ብሏል። በዚህ አባባል የተቃኘው ጆሮዬ ግን ይሄንን የአዝማሪ ሙዚቃ የሰማ መሰለው።
‹‹ጮማውን በካራ አንተው ብቻ በልተህ
ጠጁን በብርሌ ብቻህን ጠጥተህ
የት ትገባ ይሆን ሆድህን አንዘርጠህ ››

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...