Tidarfelagi.com

ፈሪ ነኝ!

ፈሪ ነኝ! ሞዴል ፈርቶ አደር! ውሃ ውስጥ ሆኜ የሚያልበኝ። በርግጥ ውሃው “ፍል ውሃ” ከሆነ ማንም ሊያልበው ይችላል። እኔ ግን አጥንት በሚቆረጥም ውሃ ውስጥም ያልበኛል።

መፅሀፉ፣ “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ይላል። እኔ ግን “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ፣ መጨረሻውም ሁሉንም መፍራት ነው” ብያለሁ። ፈርቻለሁም። እግዜር ሰይፍ የያዙ መላዕክት አሉት። መንግስት ዱላ እና ጠመንጃ የጨበጡ ፌደራሎች አሉት። ስለዚህ እግዜርንም መንግስትም መፍራት ጥበብ ነው። የሰው ልጅ ከላይ በሰይፍ ከታች በዱላ የታጠረ ምስኪን ፍጡር ነው።

“ሴት የላከው ሞት አይፈራም” ይላሉ። እኔን አይመለከትም። ዓለማችን ላይ ያሉ ሴቶች ሁሉ ተሰባስበው ቢልኩኝ ንቅንቅ አልልም። አሉ የተባሉ ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች ተሰብስበው አይደለም ጠብ ያለበት ቦታ፣ እዚህ ከቤቴ ፊት ለፊት ያለው አንዋር ሱቅ ቢልኩኝ አልሄድም። “ሴትን ያመነ ጉም የዘገነ” እያሉ ጥርጥሬ እየዘሩብኝ ነዋ ያደኩት!

ፈሪ የእናቱ ልጅ ነው ብለውኛል። ማን የእናቱ ልጅ መሆን ይጠላል? የእናቴ ልጅ ለመሆን እፈራለሁ። ፈርቼም የእናቴ ልጅ ሆኛለሁ። አባቴን አላውቀውም። በልጅነቴ ነው ጥሎኝ የሄደው። ጥሎኝ የሄደው አባት መሆን ስለፈራ ይመስለኛል። ስለዚህ እንዳባቴ ፈሪ ነኝ! የእናቴም የአባቴም ልጅ ነኝ ማለት ነው። ድሮስ የማን ልጅ ልሆን ኖሯል?

አፄ ቴዎድሮስ ሽጉጡን ጠጥቶ ሞተ ይሉኛል። እኔስ ቢሆን እስክሞት ደረቅ ጂን እየጠጣሁ አይደለም? ድራፍቴን እየላፍኩ፣ ጭላንጭል ድፍረቴን አለቅልቄ እንደደፋሁ ሳያውቁ ነው? ግን ሰክሬም፣ ነፃነት ከምትባል ኮማሪት ጋር አድራለሁ እንጂ፣ “ነፃነቴን ስጡኝ” ብዬ አልጮህም። እፈራለኋ! እራሴን እስክስት ጠጥቼም እፈራለሁ። ብርጭቆ ውስጥ ልደበቅ ብሞክርም፣ ድብቁ የአዕምሮዬ ክፍል “አየሁህ” እያለ ያባንነኛል። ግራም ነፈሰ ቀኝ…. ኸረ እንደውም ነፈሰም አልነፈሰ… ፈሪ ነኝ! ፈሪ በመሆኔ ነው እድሜዬን ሙሉ አንዲት ችግኝ እንኳ ሳልተክል፣ “ልማታዊ” የሆንኩት። ፈሪ በመሆኔ ነው፣ ምሳሌ የማይሆን ይዤ “ሞዴል” የተባልኩት።

“የወንድ ልጅ እናት፣
ታጠቂ በገመድ
ልጅሽን አሞራ እንጂ፣ አይቀብረውም ዘመድ” ይላል ዘፋኝ። ታዲያ አሞራ እንዲቀብረኝ ነው ጀግና የምሆነው? አሊያማ ለምን እድር ገባሁ? እስከዛሬ ለዕድራችን ምን ያህል እንደከፈልኩ ታውቃላችሁ? አታውቁም! ብታውቁማ አሞራ ይቅበርህ አትሉኝም። እኔ ግን ፈሪ ነኝ! ፈሪ ስለሆንኩ ዕድር እንጂ አሞራ አይቀብረኝም! ስንት አሞራ ባናቴ እንደሚያንዣብ አታውቁም? አሞራ ሊቀመንበር፣ አሞራ ፌደራል ፓሊስ፣ አሞራ ጆሮ ጠቢ…. አሞራ ብዙ ነገር፣ መሃል ላይ እኔ!

እኔ የምለው? “አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ” ተብሎ የተዘፈነላት ልጅ ግን አታሳዝንም? እስካሁን አሞራው ወስዷት ይሆን ወይስ ዘንድሮም እያያት ይሆን? መቼም ልበ-ፅኑ አሞራ መሆን አለበት። እኔ ግን ፅኑ ልብ ስለሌለኝ ፈሪ ሆኛለሁ። ጀግንነት ልቤን ስሞ ለፍርሃት አሳልፎ የሰጠኝ የፍርሃት መሲህ ነኝ። እና እድር የት ሄዶ አሞራ ይቀብረኛል? እድርን ያቋቋሙት እኔን መሰል ፈሪዎች መሆን አለባቸው! ዘፋኝ ማለት፣ “ጎመን በጤናን” የዘፈነ ነው! በየቀኑ ልቤ ላይ ትልቅ ኮንሰርት የሚያዘጋጅ ይህ አይነቱ ዘፋኝ ነው… ጎመን በጤና የሚል! ትንሽ አሻሽሏት፣ “ምንም በጤና” ብሎ ቢዘፍናት ደግሞ እንዴት ባማረበት!

“እሳት አመድ ወለድ” ይሉኛል። ቀድሞስ እሳት ምን ሊወልድ ኖሯል? በባንክ ቤት ሕግ፣ ገንዘብ ገንዘብን ይወልዳል። እሳት ግን በገንዘብ ሕግ አይተዳደርም። እሳት እሳትን አይወልድም። እናም አባቶቼ እሳት ከነበሩ፣ አመድ ከመሆን ውጪ አማራጭ የለኝም። አዎ አመድ ነኝ! ግለትም ሙቀትም የሌለኝ አመድ! የእሳት ልጅ! አመዳም ትሉኝ ይሆናል….. እንዳሻችሁ።

ስልጣናቸውን አላግበብ የተጠቀሙ ሰዎች ስልጣን ይልቀቁ ከማለት፣ ሀገር መልቀቅ እመርጣለሁ። ፈሪ ነኛ! ለምን አባቴ ደፋር እሆናለሁ? ኋላ ሕገ መንግስቱን ሊንድ ሞከረ ብባልስ? ሕይወቴን መገንባት አቅቶኝ የምፍጨረጨር ሰውዬ በመናድ ልከሰስ? አፍራሽ ሃይል ልባል? ሕገ መንግስት እኮ ጨረቃ ቤት አይደለም ጎበዝ! “ሕገ” ከሚለው ጋር “መንግስት” የሚል ተጣማሪ አለው። መንግስት አልኩ አይደል? አንተን አይደለም ጥቁር ውሻን ልበል ይሆን? ታውቃላችሁ፣ ሕገ መንግስቱን ሳስበው ሆኑ ግንበኞች ተሰብስበው የገነቡት በጣም ትልቅ ካብ ነው የሚመስለኝ። ምስኪን ሕገ መንግስት፣ ስንቶች ሊያፈርሱት ሞክረው ፈርሰው እንደቀሩ ቢሰማ በሳቅ ይፈርስ ነበር!

 

***************************************** ክፍል ሁለት *****************************************

 

ፈሪ ስለሆንኩ ነው ሳይልኩኝ ወዴት የምለው? ፈሪ ስለሆንኩ ነው “ዲግሪህን ረስተህ ስራ ፍጠር” ሲሉኝ እናንተ ካላችሁ “ሕይወት ፍጠር ብትሉኝም እሞክራለሁ” ያልኩት። ፈሪ ስለሆንኩ ነው “እቅዳችን ግቡን ይመታል ሲሉ( ማንም ማንንም ባይመታ ደስ ቢለኝም) እንጥሌ እስኪፈርስ “ይመታል!” እያልኩ የምጮኸው!

መፍራት ነውር ነው? ፈሪ ታክሲ እንዳይሳፈር የሚከለክል አዋጅ ወጣ? በሊማሊሞ ያቋርጥ… በሱዳን በረሃ ከሀገር ይውጣ ተባለ? ፈሪዎች ዛሬ ማታ ተረሽን ይደሩ ተባለ? ታዲያ ለምን አልፈራም? “የፋራ ይመለስ ይሉኛል” ጉረኞች! መጀመሪያ ካለሁበት መች ተንቀሳቀስኩና? ሳይሄዱ መመለስ አለ? በማይዘልቁት ጉዞ ከመባከን መዳን የፈሪዎች ፀጋ ነው!

እንደ እነርሱ ለነብር “ና እንዋጋ” ብዬ መዕክት የምሰድ ልቤ ያበጠ ፍየል አይደለሁም። ነብር ዝር በማይልበት ሀገር እስከ ዓለም ጥግ የምሸሽ ፈሪ ነኝ። ንገሩኝ እስቲ ለምን አልፍራ? 50 ሜትር ከማይርቁት ጎረቤቶቼ ጋር መተባበር ያቃተኝ ሰውዬ ባህር ማዶ ካሉ የሽብር ቡድኖች ጋር በመተባበር ልከሰስ? እራሴን በራሴ መቀስቀስ አቅቶኝ በቁሜ የተኛሁ ሰውዬ አመፅ በመቀስቀስ ልከሰስ? ያልነቃ ቀስቃሽ ልሁን?

“ጎበዝ ይሙት ፈሪ ይኑር ቢሻው፣
አተላ መሸከም ይችላል ትከሻው” ይላሉ። አተላ ምን አላት? አይደለም አተላ ዓለምን ልሸከም እንደምችል ባይገባቸው ነው። አትላስ የግሪኩን ቦታ ልቀይረው እችላለሁ። አትላስ ዓለምን የመሸከም እርግማን የወደቀበት ፈሪ ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም።
“አሁን ለምን ይሆን ፈሪ ማቶንቶኑ፣
ቅጠል ላይበጠስ ካልደረሰ ቀኑ” ቢሉም፤
ሰው መሞቻ ቀኑን ፈፅሞ ባያውቅም፣
ፈሪ መሰንበቱ አያጠያይቅም! ….. ብያለሁ።

ፈሪ ነኝ!
“ጠላታችን ድህነት ነው… ከድህነት ጋር እንዋጋለን!” ሲሉኝ እንዴት በፍርሃት እንደምርድ እኔ ነኝ የማውቀው! አፍሰው ወደ ጦር ሜዳ የሚወስዱኝ እየመሰለኝ እደነብራለሁ። ለምንድን ነው ከድህነት ጋር የምንዋጋው? ችግሮቻችንን ለምን በሰላማዊ መንገድ አንፈታም? ድህነት ከሚለው ቃል ይልቅ “እንዋጋለን” የሚለው ቃል ጮሆ የሚሰማኝ ፈሪ ነኝ! የቀድሞ ጠቅላያችን ታንክ ተደግፈው መፅሐፍ ያነቡ ነበር ይባላል። እንዴት ጀግና ነበሩ ጃል! እኔ በሕልሜ እንኳን ታንክ የመደገፍ ድፍረት የለኝም። ታንክ ተደግፌ ላነብ ይቅርና የማነበው መፅሐፍ ውስጥ “ታንክ” የሚል ቃል ካየሁ በድንጋጤ መፅሐፉ ከእጄ ሊወድቅ ይችላል።

“ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም” ትላላችሁ። ወገኞች! ወግ አያልቅም መቼም። ደፋሮች ዛሬ የት ነው ያሉት? ማዕከላዊ አይደለም? ቃሊቲ አይደለም? ታዲያ መውጫ ነው መግቢያ የማያጡት? የተበላሸ አባባላችሁን እንኳ ለማረም ትፈራላችሁ። የጀግና ልብስ እና ጥሩር በመልበስ እኮ ጀግና አይኮንም። ዶን ኪዎቴዎች ሁላ!

“የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው” ስትሉም ሰምቻለሁ። እኔ ግን ፈሪ ነኝ። እቺ የተከራየኋት ቤት ናት ቤቴ። አሁን ደግሞ ኮንዶሚኒየም ተመዝግቢያለሁ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የራሴ ኮንዶሚኒየም ይኖረኛል። ያኔ ከአባባላችሁ ተቃራኒ “የፈሪ ቤቱ ኮንዶሚኒየም ነው” ትሉ ይሆናል። ያሻችሁን በሉ። ያሻኝን ያህል እፈራለሁ።

ሰውን ተፈጥሮ አይደለም ፈሪ የሚያደርገው። ፈሪም ደፋርም የሚያደርገው የባለጋራው አቅም ነው። ምን ደፋር ብትሆን “ዛሬ አንበሳን ላግኘው እንጂ አበሳውን ነው የማሳየው” የምትል ሚዳቋ አለች? የለችም። ምን ፈሪ ብሆን “ዛሬ አግኝታ ቁም ስቅሌን እንዳታበላኝ…. ብቻ ፈጣሪዬ አንተ ጠብቀኝ” የሚል ጅብ አለ? የለም።

ይሄ ፅሁፍ ረዝሞ ያሰለቻችሁ ይሆናል ብዬ “ስለፈራሁ” እዚህ ጋር ላቁመውና ክፍል ሶስትን ከአፍታ ቆይታ በኋላ ልቀጥል።

 

***************************************** ክፍል ሶስት *****************************************

እናንተ እየዛታችሁ ወደ አንበሳ የምትሄዱ ሚዳቆዎች ሆይ! የይዋጣላን ደብዳቤ ለነብር የምትልኩ ፍየሎች ሆይ! ….. “ልያዝህ” ብላችሁ ወደ ተኩላ መልዕክት የምትሰዱ በጎች ሆይ! ስለምን በፈሪነቴ ትሳለቃላችሁ? አዎ ፈሪ ነኝ! ወንዙም ንፋሱም ፍርሃትን እየሰበከ ያሳደገኝ ፈሪ! ወንዙ የጀግና ሰው ደም ይዞ ሲፈስ አይቻለሁ። ንፋሱ ሞት ደፍሮ የቆመ ጎበዝን “እሪ በከንቱ” እየጋለበ ሲነፍስ ሰምቻለሁ። በእኩለ ቀን የመሸባቸውን ጀግኖች አይቻለሁ። በጠራራ ፀሐይ የዘነበባቸውን ደፋሮች ተመልክቻለሁ። እቺ ሀገር መች ነው ጀግና ከመብላት ፆማ የምታውቀው? ነይ ነይ ሳትል ሁዳዴ ስንቱን ጀግና አልበላችም? እና ለምን አልፈራም? ድብን አድርጌ ፈራለሁ!

አንድ የምደፍረው ነገር ቢኖር ፈሪ ነኝ ማለትን ነው። አይደለም ሕገ-መንግስት የእንቧይ ካብ ናድክ የማያስብለኝ ይህ ቃል ነው። የማንንም የሽብር ሀይል እርዳታ ሳላገኝ በግሌ ልናገረው የምችለው ቃል ቢኖር ይህ ቃል ነው። በህቡዕ ሳልደራጅ የምናገረው ቃል ቢኖር ይህ ቃል ነው። ከውጭ ሃይሎች ገንዘብ ሳይከፈለኝ ልናገረው የምችለው ቃል ቢኖር ይህ ቃል ነው። ፈሪ ነኝ! ምን ታመጣላችሁ? እኔስ ምን አመጣለሁ? ማ ምን ያመጣል?

“ተዋጋ ብዬ ብሰጠው ጦር፣
አድርጎት መጣ ያጥር ማገር” ብለው ይዘፍኑብኛል። እኔ ግን መጀመሪያዉኑም ጦር አልቀበልም። ምን ይሁነኝ ብዬ? ሊያውም ተዋጋ ብለው የሚሰጡኝን? ቀልደኞች። እንደው ብቀበልስ እነሱ ጦር የሚሰጠው እና የማይሰጠው ለይተው አያውቁም እንዴ? እሺ ተቀብዬ ያጥር ማገር ባደርገው ምን አጠፋሁ? የአባቴን ጦር ለአጥር ማገር ባውለው ልማታዊ አስብሎ ሊያስወድሰኝ እንጂ፣ ፈሪ አስብሎ ሊያስወቅሰኝ ይገባል? ለዚያ እኮ ነው ፈሪዎች የልማት ሀይል ሲሆኑ ደፋሮች የጥፋት ሀይሎች ናቸው የሚባለው። ይህ ዘፈን ግን በምን መለኪያ ነው የሰርግ ዘፈን የሆነው? እስቲ ቢያንስ በሰርጋችን ቀን ተዉን! ደሞ ሌላም ሰርግ ዘፈን አለላችሁ፤
“ብር አምባር ሰበረልዎ፣
ብርአምባር ሰበረልዎ….. ( “አሃሃ…” ይላሉ አጃቢዎች)
ጀግናው ልጅዎ!”

ድንግልናን ማፍረስ የጠላትን ምሽግ ከማፍረስ እኩል ጀግና ሲያስብል አያስቅም? እኔ በአጃቢዎቹ ቦታ ብሆን “አሃሃ…” በማለት ፋንታ ሃሃሃሃሃ ብዬ ነበር በሳቅ የምፈርሰው። ቀስ በሉ እስቲ! ሀዘኑም ዘፈኑም የጀግና ሆኖ እንዴት ይቻላል?

በዕውቀቱ በእንቅልፍ እና ዕድሜ’ መፅሀፉ “የስልጣኔ መነሻው ፍርሃት እንጂ ጀግንነት አይደለም፤ መስጠም ማይፈራ ሰው የዋናን ጥበብ አይፈለስፍም” አላለም? ታዲያ ስለምን የፍርሃቴን ጥሞና በጀግንነታችሁ ማሽላላት ታውኩታላችሁ። ፈሪ መሆን ሃጢያት፣ ደፋር መሆን ፅድቅ ነው? እሱ የድፍረት መናፍቅ ነብያት ያስተማሯችሁ አይደለም? ስንት ጀግኖችን ወደ ገሃነም አልሸኘንም?

ሃጥኣንን ሊያድን እንጂ ፈሪዎችን ሊያደፋፍር የመጣ መሲህ አለ? አያችሁ…. እኛ ፈሪዎች በሰማይም በምድርም የተዘነጋን ነን። ፍርሃታችንን ግን አንዘነጋም። ተግተን እንፈራለን። ጦርነት የእኛ የፈሪዎች ነው እንዴ? መግደል የፈሪዎች ነው? አመፅ የፈሪዎች ነው? ሁሉም እንደ እኔ ፈሪ ቢሆን ዓለም ሰላማዊ አትሆንም ነበር?? ሁሉ እንደ እኔ መግደል ቢፈራ፣ ሁሉ እንደ እኔ ጦርም ጦርነትም ቢፈራ፣ አመፅ ቢፈራ ከምድራችን የገዘፈ ገነት ይኖር ነበር? ፈሪ ባገሩ አይከበርም እንጂ እኛ ፈሪዎች ነበር መከበር ያለብን። ለነገሩ እዚህ ሀገር ማን ይከበራል? ፈሪ አይከበር። ጀግና አይከበር። ግንቦት ሃያ ብቻ። እኔም ፈሪ አይደለሁ? ግንቦት ሃያን ከባለቤቶቹ በላይ አከብራለሁ። ፈሪ ስለሆንኩ የጠሉትን እየወቀስኩ፣ የወደዱትን እያወደስኩ እኖራለሁ። አዳሜ የመናገር ነፃነት የለም ቢልም በአደባባይ ፈሪ ነኝ ስል ግን ቅንጣት አልፈራም።
ፈሪ ነኝ! ፈሪ!!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...