Tidarfelagi.com

ፀጥታ ነጋሲ

ይኼ አብኛዛውን የምንኖርበት አለም ፀጥታ ነው፡፡ ያልተነገረለት ነው፡፡ ሆሄ፣ ቃል፣ አንቀፅ፣ ምዕራፎች፣ ቅዳሴና ዘፈን፣ እንጉርጉሮና ምንትስ አልተነዳበትም የሚባል፡፡ ምድር ላይ ከተሰሩና ከተደረጉ ከታሰቡና ከታለሙ ነገሮች የተመዘገበው ስንቱ ነው? የአዳም የመጀመሪያ ሳቁ ተመዝግቧል? የመጀመሪያው የአዳም ወይ የሄዋን እንጉርጉሮ ይታወሳል? የሐጢያት መጀመሪያ የተባለቸው በለስ የተበላችባትን ጊዜ፣ ሰዐትና ደቂቃ የሚያውቅ አለ?……

ሙሴ ቀይ ባሕርን ሊሻገር ሲል ያን ያህል የውሐ ብዛት አይቶ ስለማያውቅ ሽንቱን ደጋግሞ በመሽናቱ የተበሳጨው ወንድሙ ኢያሱ ‘ይኼ ተብታባ ምን ሆነ? መንገዱን ገና ሳናጋምስ ፊኛውን ታመመ እንዴ?’ ብሎ መናገሩን ማን መዘገበ? ሙሴ ይኼን ሰምቶ ያዙኝ ልቀቁኝ ‘ይሄን ምላሳም ካልደበደብኩ’ ማለቱስ?……

……ናምሩድ አፉን የፈታበት ቋንቋ ምን ነበር? ሰለሞን ንግስት ሳባን ኦፊር ምድር እንሰት ኮባ ስር የደበቀቻትን ድንግልና እንደ ተራ የሊባኖስ በለስ አልጋው ላይ ስትጥልለት ድንቁርናዋና ልጅነቷ አስገርሞት እየሳማት፡ ‘የእኔ ጅል ያንን ሁሉ የተጓዝሽው ለዚህ ነው?’ ማለቱን ክብረ ነገስት መዝግቦታል? ሳባስ እብራይስጥ ባለማወቋ እንደተተረበች ሳይገባት መሞቷን እናውቃለን? ሳባ ገላዋን ስትታጠብ አንድ ታይጋና የተባለ ጉብል ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቆ የንግሥቲትን እፍረት በማየቱና ያየውንም በአክሱም ከተማ እየዞረ ‘ንግሥት ጭናቸው ላይ ንቅሳት አለ፣ ደ’ሞ ገና አልጨጎኑም’ እያለ በማውራቱ ዐይኖቹ እንዲወጡ ሆነው በዕውርነት አልተቀጣም? ይሄን የሚያውቅ አለ? በዚህም ሰበብ ከርሞ ልጁ ሲሞት ቀብር ላይ የመጀመሪያው ተሰለብ ሰለሞን(1) ሙሾ አልወረደም?……

……ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ በስደት ዘመኑ ዋሻ ተደብቆ ማልቀሱና መናፈጡ በየትኛው ድርሳን ሰፍሯል? ነገረኛ ጳጳስ አባሮት ከኢንፍራንዝ አገው ምድር ከአገው ምድር ዳሞት ሲሮጥ ሰላሳ ሰባት ጊዜ በአፍጢሙ መውደቁ ተመዝግቧል? ሰላሳ ሰባት ጊዜ፡፡ ለመሆኑ ተማሪው ወልደ ሕይወትስ ይኼን አስታውሶ ፅፎለታል? ኧረ ዛሬ ‘ሙሎ’ ስለሚባል ደብተራ የሚያውቅ አለ? በልብነ ድንግል ጊዜ ወደ አዋሽ የሚሄድ መልዕክተኛ አጅብ ተብሎ መልዕክተኛው ሰው ቀረጢት ውስጥ በአጋጣሚ የቤተ ክርስቲያን ዝርዝሮች ያሉበት የሚስጢር ካርታ (ስዕል) አግኝቶ የኼን ለማጋለጥ ወደ እንጦጦ ሲያመራ በአቡኑ ሕቡዕ ወታደሮች መገደሉ? ይኼ ካርታ ለቱርኮች እንደተላከ ከአቡኑና ከእሱ ሌላ ማን ያውቅ ነበር?……

……ታላቁ ራስ አሊ የመጀመሪያ ሚስታቸውን በጥፊ ሲመቱ እልፍኝ ውስጥ ማን ነበር? በዚህ ሰበብ ከልጅቷ አባት ጋር ግብግብ ገጥመው የፊት ጥርሳቸው አንዱ የላይኛው በቆመጥ እንደረገፈ የት ተመዝግቧል?……

ሚኒሊክ ልጅ እያሉ ደሴ ገበያ ማታ ለጋ ጨረቃ የወጣች ዕለት ዐይተዋት ስለ ወደዷት የአፋር ልጃገረድ እሳቸው ለማን ነግረዋል? አንዱ አሉባልታ ሰምቶ የሙዚቃውን ባቲ(2) (ኧረ ባቲ ባቲ/ ባቲ ገንደልዩ……) ቀኝት የፈጠሩት ሚኒሊክ ናቸው ቢለን ምን ልንል ነው?……

……በዚህች በኮተቤ ገጠርና በዚያች በሰማይዋ ፀሐይ መሃል ምን አለ? በዚህች በኮከበ ፅባሕ ዳገት መሃልና ባራት ኪሎ ስንት ነገር አለ ካርታ፣ የሰው ትውስታና የብርሃንና ሰላም ጋዜጠኛ ያልያዘው? ጋሼ? ሰማሽ እቱ? ብዙው ጉዳይ አልተመዘገበም፡፡……

……እተጌ መነን ለስደት ሎንዶን ሲገቡ በትካዜ ‘አንቺ ሆዬው ለእኔ’ን ማንጎራጎራቸውን ማን ተናገረ? ቤታቸው ሲገቡ ተፈሪ በቀስታ ጢማቸውን እየላጉ ‘መነንዬ ሰማሁሽ፣ በእግዜር በባህታ ይዤሻለሁ እዛ መናፈሻው ጋ አትዝፈኚ ፈረንጅ ይሰማል፣ ‘ይህቺ ባሪያ አበደች’ ይሉሻል’ ሲሉአቸው መነን ‘አንተ አላበዛኸውም’ ብለው አኩርፈው መኝታ ቤት ገብተው ለአንድ ሳምነት በራሳቸው ላይ እንደ ዘጉ ተመዝግቧል? ኃይለሥላሴ ታላቁን ንግግር የዓለም ማህበር ላይ ተናግረው ሲያበቁ መልካም መልስ በማጣታቸው ከረዳታቸው ከሎሬንዞ ትዕዛዝ እንኳን ተደብቀው ለማንም ሳይታዩ መታጠቢያ ቤት ገብተው ማልቀሳቸው ተፅፎአል?……

……ልዕልት ተናኘወርቅ ታላቋ ብሪታኒያ በጣሊያን ወረራ ዘመን በስደት ላይ እያለች ባዝ ጎዳና ላይ በትህትና የተዋወቃትን ዲላን ቶማስ(3) የተባለ የዌልሽ ጉብል መውደዷን ብላቴን ጌታ ሂሩይ አውቀው፣ ብላታም ተበሳጭተው ሰው በሌለበት ጠርተው ቤት ዘግተው ‘ጉግሳን የመሰለ የመኳንንት ልጅ እያለ ምኑም ከማይታወቅ አረመኔ ጋር ምን ልትሰሪ? ብትችይ ሱባዔ ነበር፣ ባልወልድሽም እቀጣሻለሁ’ ብለው የትልቋን ልዕልታችንን ጭን እንደ ሕፃን ልጅ ጭን አልመዘለጉትም? እያለቀሰች ለመነን ለእናቷ ብትናገር ‘ደግ አደረገ ልቤን አራሰልኝ…… ከሞላ የአገርሽ ወንድ እነ ባልቻ አሉ እና ማን ናቸው እነ አርአያ አሉ…… ያ ደ’ሞ ልጄ ስንቱ ስንቱ አበበም አለ ምን የመሰለ ሎጋ ደ’ሞ ነጫጭባ ምን አሰኘሽ ልጄ?’ አላሏትም? ይሄን ማን ሰምቶ ነበር? ማን ያውቅ ነበር? ተናኘ የመጀመሪያ ሴት ልጇን ባዝ ከተማ ስትወልድ ጋሼ ሎሬንዞና አዛዥ ወርቅነህ ድንገት ዲቃላ ከተወለደ ‘አስፈላጊው እንዲፈፀም’ ተብለው በተጠንቀቅ ሲጠብቁ እንደ ነበር ማን ያውቃል? እተጌ ‘እንደ አገራችን ዓይነት ፍል ውሃ እዚህ እኮ አለ፡፡ ነይ ታጠቢ’ ተብለው ሲሄዱ እዛም ደርሰው ሲጠይቁ ‘ጥንት የሮሜ ሰዎች የታጠቡበት ነው’ ቢሉአቸው ‘እምቢ የፋሽሽት ነገር አልፈልግም ተናኘ ነይ ውሃ አፍሽልኝ’4 ብለው በችኮላ አልወጡም? ሲወጡስ በር ላይ ያገኛቸው አንድ አእሩግ ፈረንጅ ወደ አንገታቸው ንቅሳት እያሳየ አልሳቀምና……’ንቅሳቴን ከጠላህ ዘርህ አገሬን ለምን ወሰደ?’ አላሉትም? (እሱ ግድ ባይሰጠውም) እነሱ ሳያዩ ዲላን ቶማስ ጉልበቱ ደካማ ቢሆንም ተሳዳቢውን ቢራ ቤት ድረስ ተከትሎ ሄዶ ሊደበድበው አልሞከረም? ስለዚህ ገጠመኝ እንደፃፈ ማን ያውቃል?(5)…….

……አቶ ቃልኪዳን ታች ሰፈር ያለው የሙዚቃና የቪዲዮ ካሴት ነጋዴ ሲሞት እንደ ሞተ ማን አወቀ? መሞቱን አውቆ ከቀበረው ስንቱ ነው በትክክል በምን ምክንያት እንደሞተ የአወቀ? ዛሬ ከሃያ ዓመታት በኋላ አቶ ቃል ኪዳንን የሚያስታውስ አለ? ያቺ እንጀራ ጋጋሪ ሴት ልጇን ፅንስ አስወርዳ ብትታመምባት ሰፈሩ ከሚያወራባት ውርደት ለመደበቅ ብላ ገጠር ከተማ ልካት እዛ ብትሞትባት፣ ከዚህ ዓለም ማለፏን ለማን ነገረች? አሁን ድረስ ‘ልጄ በሕይወት አለች’ ብላ ታወራ የለም? ያ የልጅቷን አለመኖር የሞላውን ልብወለድና ቀናሽ ፀጥታ እያሽካካን እንኖረው የለ? የልጅቷ እናት የጋገሩትን እንጀራ ያልበላ የሠፈር ሰርገኛስ ነበረ?……

……ያ ይሄ ፀጥ ያለ ሕዋ ነው፡፡ ሕዋው ድንቁርና ነው፡፡ የታቀደም ያልታቀደም፡፡……

……እህቴ ሆይ! ሃሙስ በተባለ ቀን ዕድሜሽ ሁለት ወር እያለ እናትሽ ጡጦ ስትነጥቅሽ ምን እንዳልሽ፣ አንቺም እናትሽም ትዝ ይላቸዋል?……

……ገጣሚውና ጸሐፊ ተውኔቱ ዮፍታሄ ንጉሴ አልጋው ላይ ተንበልብሎ (ገና ከየካ አስቀድሶ የእግር መንገዱ አድክሞት ኩታውን እንኳ ሳይጥል) እንደተኛ ከማጅራቱ ሊያንቁት ስለመጡት በአራት ጣቶቻቸው ላይ የወርቅ ቀለበት ያጠለቁ እጆች ያወራው ማን ነው?…… ዮሐንስ አድማሱን ሊያጠፋ ተቀጥሮ አስመራ ፔንስዮን ስላረፈው ቀጭን ወጣት አናርኪስት ኮማንዶ ዛሬ የሚያውቅ ማን ነው? ይሄም መልከ መልካም ሰልካካ ልጅ ሐያሲውንና ባለቅኔውን ሊገድለው ሲል ‘ወደ ጌታህ ልልክህ ነው?’ ብሎ መናገሩን ማን ሰማ? ምን ማለቱስ ነበር?……

……ኮሎኔል መንግስቱ ከኬንያው መሪ ጋር ተገናኝቶ ‘ሰላም ወዳድ አይደለህም’ ብለው አራፕ ሞይ ሲናገሩ ‘የቀረኝ ነገር ሚስቴን ውብ አንቺን ለኢሳያስ መዳር ነው’ ብሎ መልሶላቸው የኬንያውን የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር አላሳቀም? ማን ይሄን በጋዜጣ ዘገበው?……

……ታላቁ አብዮት ይዘነጉታል እንጂ መርሳትን የመቀናቀን ነው፡፡ ታላቁ አብዮት ይናቃል እንጂ ሰፊ አባባሎችን፣ አጠቃላይ መደምደሚያዎችን ዘንግቶ ወደ ረቂቆቹ መውረድ ይሆን? ጀግንነት ትንንሽ የመሰሉ ነገሮችን የማስታወስ፣ የመርሳትንም ተራራ ማፍረስ ይሆን? ያን ያን ታሪክ ማድረግ ይሆን አዋቂነት?……
—————————————–
1 ‘ተሰለብ ሰለሞን’ በንግሥት ሳባ ጊዜ በመታወር ለተቀጣው ልጅ እናቱ ያወረደችለት ሙሾ ስም ነበር፡፡ (በድሮ ጊዜ ሙሾዎች በሴማ በሴማ ይመደቡ ነበር) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባለስልጣኖች በሃሙራቢ አረማዊ ሕግ መሠረት ‘ሕግ አፈረሰ’ የተባለ በሞት ከቀጡ በሟቹ ቀብር ላይ የሚወርደው ሙሾ ሁሉ መጠሪያ ስሙ ‘ተሰለብ ሰለሞን’ ተባለ፡፡ (‘ተሰለብ ሰለሞን’ ሲጀመር ትርጉሙ የንግሥታችንን ድንግልና ጠቢቡ ሰለሞን በማታለል ከወሰደ አጥፍቷልና እሱስ ለምን ብልቱን በመሰለብ አይቀጣም ለማለት ይመስላል) ሴትዮዋ ለልጇ ያወረደችው ሙሾ በከፊል ይሄን ይመስል ነበር፡፡

የጤፍ ዳልጋ ብሰርቅ……ቆረፁት እጄን
ቆንጆ አጋጥሞኝ ብስቅ……ቆረፁት አፌን
የሰው ድካ ብዘል……ሰበሩት እግሬን
ተንተክትኬ ብስቅ……ናዱብኝ ችንቼን
አስታርቶን እንዳያይ……ልጄን አወሩት
ተሰለብ ሰለሞን……ነክተሃል ንግስት

ግጥሙ የተገኘው ታሪክና አፈታሪክ ከተባለው የፀሐይ አታክልት መፅሐፍ ነው፡፡ (1964) አአ አርቦሽ ማተሚያ ቤት፡፡

2 በወረሞ አፍ ለጋ ጨረቃ ማለት ነው

3 በታላቋ ብሪታኒያ ስዋንሲ ዌልስ እአአ በ1914 ተወልዶ በ1953 ያረፈ ገጣሚ

4 ‘እኚህ ሴትዮ አገራቸው ይኼ ዓይነት መታጠቢያ መቼ ሰሩና ነው የሚኩራሩት?’ ብለው አቶ አበበ ረታ እተጌን ለተናኘ አምተዋቸዋል ይባላል፡፡ (የሎሬንዞ ትዕዛዝ የቃል ማስታወሻ)

5 አንዳንድ ሰዎች እኤአ በ1934 የታተመው 18 ግጥሞች የተባለው የመጀመሪያው የግጥም መጽሐፍ የተናኘ ወርቅ መኝታ ቤት ውስጥ የግል መጽሐፍት መደርደሪያቸው ላይ እንደ ነበር ‘አየን’ የሚሉ ይናገራሉ፡፡ እና ከመጽሐፉ ልባስ ስር በእንግሊዝኛ ግልፅ በሆነ አፃፃፍ በፍቅር የተጠራ የተናኘ ስምና ማንም የሚያውቀው የዲላን ፊርማ ነበር፡፡ በተጨማሪም ስለ ዲላን ካጠኑና ከሚያጠኑ ሐያሲያን
……if I were tickled by the rub of love……/I would not fear the gallows nor the axe/ Nor the crossed sticks of war… የተባሉት ስንኞች ቶማስ ለተናኘወርቅ ሲል መደባደቡን/ ከሰው መጋጨቱን የሚገልፁ እንደሆነ የሚያውቁ ስንት ናቸው? ከሰላሳ ዓመታት በፊት በንጉሠነገሥት ኃይለሥላሴ ፅ/ቤት አንድ እንግዳ ፋይል ውስጥ የሽቶው መዐዛ ያልጠፋ ልዕልቲቷ ለአቶ ቶማስ በአማርኛ የፃፈቸው ደብዳቤ ተገኝቷል፡፡ ደብዳቤው ሳይላክ ይቅር፣ ወይ ራሳቸው ልዕልቲቷ እንደማስታወሻ ላራሳቸው ይፃፉት፣ ወይ በንጉሱ የስለላ ድርጅት ተለቅሞ እዚያ ይግባ፣ ወይ ከተላከ በኋላ በእንግሊዝ የስለላ ድርጅት ለንጉሱ ይመለስ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ ግጥሙ ይሄ ነበር፣

‘ስዘነጋ እላለሁኝ……ልቤ ጠፍቶብኝ ወድቆ
የባዝ የደንጋይ ምንጣፍ ላይ……በቶማስ ሌባው ተሰርቆ፡፡
ወረቀት የሚመስል ሶብይ……ጠጉረ መልካም ወድጄ
አልሆን አለ መገናኘት……እዚህ ጦቢያ ተወልጄ፡፡
የእኔም አገር ታላቅ ናት……የአንተም አገር ታላቅ
ግን ሁለታችን ተለያየን አንድ ቀን እንኳ ሳንስቅ፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ አንጀበኛ……የማይሆን ነገር ቢያስተምርም
ቶማስ ይወዳታል እስተ ሞቱ……ይቺን ዛላ አይጠረጥርም፡፡
ሁሉ ነገር በልብ ነው……እንላለን በዚች አገር
በጡፍህ ውስጥ የኛን ጉዳይ……አምልጦህ እንኳን አትናገር፡፡
ይህቺንም ለራሴ ነው……ተደብቄ የማስባት
ማንም ቀልቃላ ደብተራ……ታሪክ ናት ብሎ እንዳይጥፋት’

(የተፃፈበት ቀን አልተገለፀም፡፡ ምናልባት 1950ዎቹ ውስጥ ነው)
እቴሜቴ ሎሚ ሽታ (ገጽ 191 – 195)

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...