Tidarfelagi.com

ጭራቆቹ ሜጋ ፕሮጀክቶች

#፩
ዶር አብይ ከ ባለሀብቶች ጋር ያደረጉትን ቆይታ ዘግይቼ አየሁት ።ይቅርታ አድርጉልኝና ፤ ለዛ ሁላ ጉምቱ ባለሀብት ያደረጉት ንግግር Economy 101 ሰጥተው የመውጣት ያህል ነበር።

በ ውጭ ምንዛሬ ጉዳይ ላይ ባነሱት ሀሳብ ላይ ግን የምሰጠው አስተያየት አለኝ።

1-የውጭ ኃዋላ [ Remittance ] ን በተመለከተ እንደ በፊቱ አይናፋር ባለስልጣናት ሳይቅለሰለሱ ዲያስፖራው የሚልከው ገንዘብ ለሀገሪቷ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ና በዚህም ላይ የተጀመረው የፖለቲካ የዕቀባ ቅስቀሳ ተገቢ አለመሆኑን መናገራቸው ልክ ነው።

ኣሃ!
ባለፈው አመት እኮ ከድያስፖራው የተላከው [ ወደ 4 ቢልየን ዶላር] ገንዘብ በኤክስፖርት ከተገኘው [3 ቢልየን ዶላር] አንፃር ሲታይ ….ድያስፖራው ምንያህል ኢኮኖሚውን በጀርባው እንደተሸከመው መገመት ይቻላል።

[ ግን ደግሞ መለስ ብለው ዕቀባው መንግስትን አይነካም የታችኛውን ህሰብ ነው የሚጎዳው ማለታቸው አይነፋም።]

ሰውየው እንደ ነብር ጭራ አልያዝ ካለው የኤክስፖርት ዕቅድና ውጤት ጋር ከመዳረቅ ፤ ቀላል ስራ ከሚጠይቀው የውጭ ኃዋላ ገቢ ላይ አተኩሮ መስራት ይሻላል ብሎ ያሰበ ይመስላል።በተለይ አሁን የተፈጠረውን አንፃራዊ መግባባትና ተቀባይነት ተጠቅሞ “እባካችሁ በዶላር እጥረት ልንፈነዳ ነውና እርዱኝ” ማለቱ የ ብልህ ነው።

2- ሀገሪቷ የገባችበትን የኢኮኖሚ በተለይ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ቀውስ ለመቅረፍ ግን [ዶሩ የጠቀሷቸው] ቁጠባን ማዳበር ፣ ኮንትሮባንድን መቀነስ፣ የውጭ ኃዋላን መጨመር፣ ኤክስፖርቱን ማበረታታት ከሚሉት የተለመዱ ተርሞች በተለየ ጠለቅ ያለ ግምገማ እና በአጭር ግዜ የሚተገበር አፋጣኝ የ ፖሊሲ ወይም የGTP ዕቅዶች ክለሳ ይፈልጋል ባይ ነኝ።

አዎ !
[Kill the mega projects else they will eat us. They are monsters !!] ሜጋ ፕሮጀክቶች ጭራቆች ናቸው። ዲዛይናቸው ያጓጓል። የሚያመጡት ለውጥም ምራቅ ያስውጣል።

ነገር ግን በተጠና ዕቅድና ወቅቱን ጠብቀው ካልተጀመሩ
ጠቃሚነታቸው ወደ ጎጂነት በፍጥነት ይቀየራል።
ከተጀመሩም በኋላ ግንባታቸው በታቀደለት ግዜና የገንዘብ መጠን ካልተጠናቀቁ ፣ [ ከሙስናው ጋር ተደማምሮ ] ሀገሪቷ ያላትን የዶላር እና የሀብት ክምችት እምሽክ አድርገው ይበሉታል።

በቀላሉ በ GTP 2 ዘመን በ 2018/2019 ዓም ብቻ ለ ካፒታል ኢንቨስትመንት እስከ 27 ቢልየን ዶላር ድረስ እንደሚያስፈልገው ያሰበው መንግስት ፤ የውጭ ምንዛሬ ገቢያችን ጉዳይ እንደታሰበው አለመሆኑን እንኳ አይቶ የታቀዱ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አላዘገየም ። ወይም አላቋረጠም። አልያም ፕላኑን አልከለሰም።

ይልቅ አብዛኞቹን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ጀምሯቸዋል። ለዛውም ከ GTP 1 ተጎትተው ና ተበለሻሽተው የመጡትን ጨምሮ እየተንደፋደፈባቸው ነው። የ ማዳበርያ፣ የስኴር ፣ የ ባቡር ፣ እና የ ሀይድሮ (የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ) ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ጭራቆች ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ ዕጣፈንታቸውን በቶሎ የሚወስንላቸው ባለቤት ካጡ ይበሉናል ! ወደባሰ ቀውስና economic recession ይወስዱናል።

አዎ !
በ 2018/19 ዘመን ኤክስፖርት ፣ ኃዋላ ፣ እርዳታና ብድርን ጨምሮ [በጣም የዋህ ሆኜ ] 10 ቢልየን ዶላር ብናገኝ እንኳ ፕሮጀክቶቹ ከሚፈልጉት የዶላር ምንዛሬ [ 27 ቢልየን ዶላር ] አንፃር አልተገናኝቶም ነው።

እናማ ለጊዜው በቀጥታ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ወይም የምንዛሬ ወጪ ማስቀረት የማይችሉ ፕሮጀክቶችን በአስቸኳይ ማጠፍ ተገቢ ነው ባይ ነኝ።

ለምሳሌ፡
[ እስከ 4 ቢልየን ዶላር የሚፈጁት የባቡር ፕሮጀክቶችን ማጠፍ ] [አስፈላጊ ከሆነ ከዚህ በኋላ እስከ 4 ቢልየን ዶላር የሚፈልገውን የህዳሴውን ግድብም ቢሆን ባለበት የተወሰነ ሀይል እንዲያመነጭ አድርጎ ማቋረጥ] [የተጨመላለቁትንና ብዙ ሀብት የበሉትን የስኳርና የ ማዳበርያ ፋብሪካዎች፤ ጥናት ላይ ተሞርኩዞ፤ በደረሱበት የግንባታ ደረጃ ላይ አቋርጦ ና አቅማቸውን አሳንሶ ወደ ምርት ማስገባት ]

የሚልንየም ጎሎችን ከምናሳካባቸው ፕሮጀክቶች ውጭ ያሉትን ጭራቆች በጥንቃቄ ገምግሞ ዕጣፈንታቸውን መወሰን ያስፈልጋል።
አለበለዝያ ጭራቆቹ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ውስን ሀብትና የዶላር ክምችት መብላት ከቀጠሉ ፤ ለ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት ምላሽ ( መድሃኒትን ጨምሮ) የሚሆን ምንዛሬ እናጣለን።


#፪

1000 ሜጋዋት አመታዊ ብክነት ማለት አሁን ባለው የኤክስፖርት ዋጋ መሰረት ከ 500 ሚልየን ዶላር በላይ አመታዊ ገቢ ማጣት ማለት ነው።

ያው እስከ 8 % ብክነት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ለ መድሃኒት እንኳ በጠፋ የውጭ ምንዛሪ ፣ ይህን ያህል ብክነት የጤናም አይደል።

ታድያ 1000 ሜጋዋት ባከነ እየተባለ ፣ ሌሎች ጭራቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የሀገር ሀብትና የውጭ ምንዛሬ ከማባከን ፤ ዕቅዶችን መከለስ ግድ አይልም ወይ ?


#፫

በመንግስት የተለጠጠ ዕቅድ መሰረት በ 3 ቢልየን ዶላር አምስት የማዳበርያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ታስቦ ነበር።
‘The game changers’ የተባለላቸው ፕሮጀክቶች!

ታድያ !
ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው እና በ 2012 በ 800 ሚልየን ዶላር ዕቅድ የተጀመረው የያዩ ማዳበርያ ፕሮጀክት በ 2 አመት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታሰብም ዛሬ በስድስት አመቱ 43% ያህል ብቻ ነው የተጔዘው።
ባለፈው 9 ወራት ግንባታው 1 % እንኳ ለውጥ አላሳየም ። ምክንያትህ ምንድነው የተባለው ሜቴክ ‘የዶላር ወረፋ ይዘን ልናገኝ አልቻልንም ‘ብሏል።

በዛ ላይ የፕሮጀክቱ ባለቤት (ኬሚካል ኮርፖሬሽን) እስከ አሁን ወለድ ብቻ 1.8 ቢልየን ብር ከፍያለሁ፤ ከ አሁን በኋላ ፋብሪካውን ጨርሳችሁ ብትሰጡኝም አክሳሪ ነው የሚሆነው ብሎ ተናግሯል። 😀

በአሁኗ ደቂቃ ፤ ይህ የሞተ ፕሮጀክት በሜቴክ በኩል ቢያንስ በግምት 300 ሚልየን ዶላር ያህል የውጭ ምንዛሪ እስኪፈቀድለት ከመድሃኒትና መሰረታዊ ሸቀጦች አስመጭ እኩል ተሰልፎ እየጠበቀ ነው። [ለዛውም ፤ የማምረቻ ሴክተር ውስጥ ስለሆነ ቅድምያ ይሰጠዋል ]

በዛ ላይ በብሄራዊ ባንክ ሪዘርቭ ውስጥ ያለው የዶላር ክምችት ለ ሁለት ወር ብቻ የሚበቃ ነው። ይህ ክምችት፣ ከሁሉም አዳጊ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አንስተኛው ነው።

እና ምን እየተጠበቀ ነው ?
ታድያ ከዚህ በላይ ውስን የሆነውን የሀገር ሀብትና ውጭ ምንዛሬ የሚበላ ምን አይነት ጭራቅ ፕሮጀክት አለ ?

እንዴ !
መገንባት ወይም ማትረፍ ብቻም ሳይሆን በአንስተኛ ኪሳራ ፕሮጀክት ማጠፍ ወይም ማቆምም እኮ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ጥበብ ነው።

#kill_monster_projects


#፬

በኢትዮጵያ ለአስርት አመታት በብቸኝነት ጎማ ሲያመርት የነበረው ሆራይዘን (አዲስ )ጎማ ፋብሪካ ጥሬ ዕቃ ለማስገባት የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻሉ በወር ውስጥ ስራ ሊያቆም ነው።

በመአት ችግሮች በተተበተበው የ ሀገራችን ኢንደስትሪ ዘርፍ ውስጥ እየተንገዳገዱ ዛሬ ላይ የደረሱት የብረት አምራች ፋብሪካዎች በውጭ ምንዛሬ ችግር ምክንያት ስራቸውን በማቆምና ባለማቆም መሀል እያመነቱ ነው።

ታድያ እነዚህ መሬት የረገጡ ፋብሪካዎች እየተዘጉ ባለበት ሁኔታ ለማይጠረቁት ጭራቅ ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሬና የሀገር ሀብት ለምን እናባክናለን !?

የውጭ ምንዛሬ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኮምፕሊት ቀውስ ከመሄዱ በፊት የአጭር ግዜ መፍትሄ ያስፈልጋል።

ጭራቆቹ ሜጋ ፕሮጀክቶች መራራ ውሳኔ ያስፈልጋቸዋል።
እንደህዳሴ ግድብ ያሉት ባሉበት ስራ እንዲጀምሩ ይደረግ ።
የተበላሹቱ (ምሳሌ ማዳበርያ ና ስኳር ፋብሪካዎች) ይታጠፉ ! ቢያልቁም በቀጥታ የውጭ ምንዛሬ የማያስገኙት (ምሳሌ የባቡር ፕሮጀክቶች) ለተወሰነ ግዜ ሰስፔንድ ይደረጉ !


#፭

ዶር አብይ 100 ቢልየን ብር የሚገመቱ ፕሮጀክቶችን ከሜቴክ እንዲነጠቁ አዘዙ።

እናመሰግናለን !

<<ለመከላከያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በከፍተኛ የገንዘብ መጠን እንዲሰራቸው ተሰጥተውት የነበሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ትዕዛዝ እንዲሰረዙ መታዘዙን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ተናገሩ።>> ምንጭ ዋዜማ

እንዴ !

መገንባት ወይም ማትረፍ ብቻም ሳይሆን በአንስተኛ ኪሳራ ፕሮጀክት ማጠፍ ወይም ማቆምም እኮ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ጥበብ ነው።

ከሜቴክ መንጠቅ ብቻ ሳይሆን….

ጭራቆቹ ሜጋ ፕሮጀክቶች መራራ ውሳኔ ያስፈልጋቸዋል።
እንደህዳሴ ግድብ ያሉት ባሉበት ስራ እንዲጀምሩ ይደረግ ።
የተበላሹቱ (ምሳሌ ማዳበርያ ና ስኳር ፋብሪካዎች) ይታጠፉ ! ቢያልቁም በቀጥታ የውጭ ምንዛሬ የማያስገኙት (ምሳሌ የባቡር ፕሮጀክቶች)ሰስፔንድ ይደረጉ።


#፮

የእድገታችን አጋር ፣ የጭንቅ ግዜ ደራሽ የምንላት ቻይና እንኳ ኤግዚም ባንኳ (import export bank of china) ለኢትዮጵያ በሚሰጥ ብድር ላይ ያለውን አካሄድ ለመቀየር እየተገደደ ነው።

ምክንያቱም ባለፈው አመት ኢትዮጵያ መክፈል ከሚጠበቅባት አንድ ቢልየን ዶላር ገደማ የብድር ተመላሽ እና ወለድ ውስጥ መክፈል የቻለችው ከ 500 ሺህ ዶላር አይበልጥም። 🤤 #ምፅ #ምፅ

ሀገራዊ ዕዳዋ 23 ቢልየን ዶላር የደረሰው ኢትዮጵያ ፤ የብድር ተመላሽ ለመክፈል በውጭ ምንዛሬ እጦት እያቃሰተች ባለችበት ሁኔታ የማይጠረቁት ጭራቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል ?

ጭራቆቹ ሜጋ ፕሮጀክቶች መራራ ውሳኔ ያስፈልጋቸዋል።

እንደህዳሴ ግድብ ያሉት ባሉበት ስራ እንዲጀምሩ ይደረግ ።
የተበላሹቱ (ምሳሌ ማዳበርያ ና ስኳር ፋብሪካዎች) ይታጠፉ ! ቢያልቁም በቀጥታ የውጭ ምንዛሬ የማያስገኙት (ምሳሌ የባቡር ፕሮጀክቶች)ሰስፔንድ ይደረጉ።

ይሄ የምንዛሬ እጥረቱን ለጊዜው ለማረጋጋት የሚወሰድ የአጭር ግዜ ብቸኛ የመፍትሄ ካርድ ነው።
የረጅም ግዜ መፍትሄውን ለማውራት በቂ ግዜ አለን።


ህምም!

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚንስቴር ማለት የሀገሪቷን ከግማሽ በላይ የሆነ ሀብት የሚቆጣጠር ቤት ነው።
ጭራቅ ሜጋ ፕሮጀክቶቹን በባለቤትነት የያዙትን ኮርፖሬሽኖች የሚቆጣጠር። [ እነ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ኬሚካል ኮርፖሬሽን የመሳሰሉትን ]

ከተቋቋመ ሶስት አመት የሞላው ይህ መስርያቤት ሶስተኛ ሚንስተሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተሹሞለታል። 😀😀

እናማ አምባሳደር ተሾመ ከረዥም የ አምባሳደርነት ስራቸው ተመልሰው የሀገሪቷን ዕጣፈንታ የሚወስኑትን ፤ በብዙ ችግሮች የተተበተቡትን እና የውጭ ምንዛሬ ክምችታችን በላተኛ የሆኑትን ጭራቅ ፕሮጀክቶች መፍትሄ ሊሰጡ !?

አይመስለኝም !


#፯

በአለም አቀፍ ንግድ ውስጥ አንድ አስመጭ ከ ላኪው ጋር ንግድ የሚፈፅመው መሀል ላይ ሁለቱንም ወክለው ዋስትና በሚሰጡ ሁለት ባንኮች ታጅበው ነው።

ታድያ ላኪው ዕቃውን ልኮ ሲያበቃ በላኪው ባንክ በኩል የጭነትና ሰርትፊኬሽን ዶክመንቱን ለአስመጪው ባንክ ይልካል።

የአስመጭው ወኪል ባንክም ዋስትና የገባበትን ሰነድ እንደተረከበ ብሩን ከአስመጭው አካውንት ቀንሶ በውጭ ምንዛሬ መልክ ለ ላኪ ባንክ ይከፍላል።

ታድያ የኢትዮጵያ ባንኮች (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ) ዋስትና የገቡበትን እና ከአስመጭው በብር የሰበሰቡትን ክፍያ በውጭ ምንዛሬ ለላኪው ባንክ ለመክፈል በወራት ደረጃ ሲዘገዩ ና ሲንገዳገዱ ማየት ከጀመርን አመታት አልፈዋል።

ምክንያቱም ምንዛሬው የለማ !

አሁን አሁን ልክ እንደ ናይጄርያ ባንኮች ፤ የኢትዮጵያዎቹም ባንኮች በአውሮፖ ከብዙ ባንኮች ጋር የመስራት ዕድላቸው ተዘግቷል። ብላክ ሊስት ውስጥም የገቡ አሉ።

ታጋሽ የነበሩት የቻይና ባንኮችም በቅርቡ ከኢትዮጵያ በሚመጣ የንግድ ውል ( import permit ) ላይ ተጨማሪ ቅድመሁኔታዎችን ለማስቀመጥ እየተዘጋጁ ነው።

እኔ መለዋወጫውን ተረክቤ መሸጥ ከጀመርኩ ቢቆይም ሰፕላየሬ ግን ገንዘቧን አላገኘችም።አያሳፍርም ወይ ? ታድያ ይህችን ምስኪን ሰፕላየር ምን ልበላት ?
ሀገሬ ዶላር የላትም ልበላት ?
አይዞሽ ሰሞኑን ይከፈልሻል ልበላት ?

#kill_monster_projects

መልካም ቀን !😊

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...