Tidarfelagi.com

ጎሬ-ቤቶች!

(ፀሀፊው፣ እኔ)
*****
ጎረቤታሞች ናቸው፡፡ ከአጠራቸው ውጪ ግን ምናቸውም አይገናኝም። የአንዷ ኑሮ ቅንጦት የሌላኛዋ እጦት ነው፡፡ ያችኛዋ የምትበላው የላትም። ይህችኛዋ የማትበላው የላትም።
አንድ ቀን…
ያቺ የድህነት አቅም ማሳያዋ ሴት….ወሰነች! “የምበላው አጥቼ፣ ገርጥቼ ነጥቼ ከምሞት… አንድ ቀን እንኳን ጀመበር እስክትጠልቅ አጊጬ፣ተውቤ ልታይ… ቢያንስ አንድ ቀን እንኳ!” ስትል ወሰነች። መወሰን ጥሩ! ግን የሚለበስ ከየት ይምጣ? ደልቃቃዋ ጎረቤቷ ታሰበቻት። ይሉኝታዋን ተራምዳ ወደ ጎረቤቷ ሄደች።
ኳ ኳ ኳ ኳ….
ተከፈተ። በሩን የከፈቱት ሰውዬ የምትናገረውን ቢጠብቁ…ዝም! ዝምም!
“እስቲ ግቢ የኔ ልጅ!” ከበሩ ገለል ብለው አስገቧት።ያችን ቅምጥሏን ልጅ ነው የፈለገችው። በእድሜ በአንድ ዓመት እና ወሰን በሌለው የኑሮ ከፍታ የምትበልጣትን ልጅ። ወደ ቤቱ ውስጥ ዘለቀች። ቅምጥሏን አየቻት።ሁለት ሴቶች በዙሪያዋ ተቀምጠዋል። የሆነ ሆዳን በአምሮት ያላወሰ ምግብ በየተራ ያጎርሷታል። ምራቋን ውጣ፤
“…እ…እ…ደህና ነሽ?..” አፏ ተሳሰረባት። ድሮስ ምን የማያሳስረው ነገር አለ?
ቅምጥሏ፣ እንደምንም በአፋ ያለውን ምግብ ከጎረሰች በኋላ ፣ “ምን ፈልገሽ መጣሽ?” አለቻት በንቀት። ድሮስ ደሃ ጥቅሙ የሃብታምን የንቀት ስሜት ማርካት አይደል?
“ እ እ…የ… ም…” ብዙ መንተባተብ። “…የማትለብሺው አንድ ልብስ ካለ እንድታውሺኝ ልጠይቅሽ ነበር…?”
ሁለቱ ሴቶች ቅምጥሏን ማጉረስ ቀጥለዋል። ልጅቷ መብላቱን የጠላች ትመስላለች። የደሃዋን ጥያቄ ስትሰማ ግን ሳቅ ትን አላት። በሳቁ ትንታ ምግቡን ተፋችው( ነው ሆን ብላ ስለሰለቻት?) ከት ብላ ከሳቀች በኋላ፤
“ትበላው የላት ትከናነበው አማራት!” ብላት ሳቋን ቀጠለች። ለአፍታ ዝም አለች ደሃይቱ። የሆነ አረፍተ ነገር ወደ አፏ ሲንደረደር ተሰማት፣ ተናገረችው፤
“ የበላችው ያቅራታል፣ ከላይ ከላይ ያጎርሷታል!” ይሄን ተናግራ ወጣች። የሷን ረሃብ እና የጎረቤቷን ቁንጣን በደከመ አዕምሮዋ እያሰላሰለች ወጣች…….. እንዳቀረቀረች( ድህነት ወንበሩ ጭንቅላት ላይ ይመስል ያስደፋል)

ሁለቱ አጉራሾች ልጅቷን ብቻ ሳይሆን ሰፈሩንም ወሬ የሚያጎርሱ ነበሩና፣ የሁለቱን ሴቶች ንግግር ወዲያው አዳረሱት። ሰፈሩ ተቀብሎ ተቀባበለው። ለሌሎች ሰፈሮችም አቀበለው። መቀባበሉ ቀጠለ…. ቀጥሎ ቀጥሎ….. ቀጥሎ…እኛ ጋር ደረሰ!! እኛ ጋር ሲደርስ ግን ታሪኩ ተቆርጦ፣ የሁለቱ ሴቶች ንግግር ብቻ ነበር።
ዛሬ!
ሁለቱ ንግግሮች፣ እንደ ተለያዩ ምሳሌያዊ ንግግሮች ይጠቀሳሉ። በአንድ ሁነት ተፈጥረው፣ በተለያየ መንገድ ይጓዛሉ። በእርግጥ በአባባሎቹ ዘንድ ምንም ጉርብትና የለም። በባለታሪኮቹም ዘንድ የአጥር እንጂ የኑሮ እና የልብ አልነበረም። መሰል ታሪኮች ግን ዛሬም አሉ። የድሮው ምሳሌ፣የዛሬ እውነት ነው። አጥሩን “በአደገኛ አጥር” ባጠረውና አጥር በሌለው መሃከል ግርብትና የሚል ስም አለ። ያኛው ጠግቦ፣ ይሄኛው ተርቦ ይሞታል። ያኛው በሥጋ ታንቆ፣ ይሄኛው አንጀቱ ተጣብቆ ይሰናበታል። የድሮው ታሪክም፣ የድሮው ምሳሌም አልተለወጠም። ሞኞች “በድሮ በሬ ያላረሰ የለም” ይበሉ። እኛ ግን አይተናል፤ በድሮ በሬ ያላረሰ የለም። ሊያውም በድሮ በሬ፣ የድሮ መሬት!…

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • solomon215mekonnen@gmail.com'
    ሠለሞን መኮንን commented on August 5, 2019 Reply

    ስትመቸኝኮ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...