Tidarfelagi.com

ግጥምና ገድል (ቅፅ 1)

“ከመዳኒት ፍቱን ወሸባና ኮሶ
ከሰው መልካም ባልቻ : ከፈረስም ነፍሶ”

ከላይ የጠቀስኩት ለስመጥሩው አርበኛ ለደጃዝማች ባልቻ ከተዘመሩት ግጥሞች አንዱ ነው። አዝማሪው ባልቻን ሲያሞጋግስ እግረመንገዱን ስለኖረበት ዘመን የህክምና ታሪክ ነግሮናል ። ስለኮሶ ምንነት ለማብራራት የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም። “ወሸባ ” የሚለውን ቃል ትርጉም ብዙ ዘመናይ አንባቢ የሚያውቀው ስላልመሰለኝ ላስረዳ። ወሸባ ማለት በዛሬው አነጋገር steam bath ማለት ነው። ቀደምቶቻችን ቁርጥማት እና መሰል ህመሞችን ለማስታገስ በተፈጥሮ በእሳተ ገሞራ የጋመ አለት ያፈላው ውሃ ይጠመቁ ነበር። አንድ ሰው በተፈጥሮ ፍል ውሃ ከሰው ተለይቶ ሲጠመቅ “ወሸባ ገባ ” ይባል ነበር። ዛሬ ስቲም ገባሁ ከማለት ወሸባ ገባሁ ብንል ምን ይለናል? : ” አያቶቼ ነፃ አወጡኝ ” የሚል ህዝብ ቃል ሳይቸግረው ከባእድ ቃል አይበደርም።

የፈረስ ስም መሰየም ከወሎ(የጁ) የመነጩ ጌቶች ያስተዋወቁት ባህል ነው ይባላል። በአፋን ኦሮሞ Abaa የሚለው ቃል “ባእለ “ ከሚለው የግእዝና ያማርኛ ቃል ጋር እኩያ ነው። አባ ነፍሶ ማለት ነፍሶ የተባለው ፈረስ ባለቤት ማለት ነው። ዛሬ በንብረት ዘመን : እገሌ የንትን ሆቴል ባለቤት ነው ብለን እንደምናስተውቅ በዘመቻ ዘመን የትልልቅ ሰዎች መለዮ ፈረሳቸው ነበር። ለምሳሌ “አባዲና ” የሚባል ትምርት ቤት አዲሳባ ውስጥ የሚገኝ መሰለኝ ። “አባዲና “የሸዋው ንጉስ የሳህለስላሴ የፈረስ ስም ነው። አባ ነጋ የራስ አሉላ አባነጋ የፈረስ ስም መሆኑን ብዙ ሰው ያውቃል። እኔ ከሁሉ የሚያዝናናኝ የሃይለማርያም ማሞ የፈረስ ስም ነው:-አባ ጎፍንን😀!!

ባገራችን እልል ያሉ ተዋጊና ፈረሰኛ ሴቶች ቢኖሩም የፈረስ ስም የሚሰጣቸው አይመስልም። ለምሳሌ የወሎዎቹ ሀሊማ( መነን ቀዳማዊት) እና ወይዘሮ መስታወት ስመጥር ተዋጊ ቢሆኑም የፈረስ ስማቸው አልደረሰንም ። ምናልባት ። ለወንድ የሚያደላው ባህላችን : ሴቶች ፈረስ እንዲቀልቡ እንጂ እንዲጋልቡ አልፈቀደላቸውም።

በታሪካችን : “አባ ነፍሶ ” በሚለው የፈረስ ስም ለመጀመርያ ጊዜ የታወቀው: የዳግማዊ ቴዎድሮስ ሎሌ የነበረው: በሰው አገር ደመከልብ ሆኖ የቀረው : እንግሊዛዊው ፕላውዴን ነው። በጅሮንድ ባልቻ ይህንን ስም ወርሶ ገኖበታል።

ባድዋ ጦርነት ወቅት ባልቻ የተሳተፈው በመድፍ እና በመትረየስ ተኳሽነት ነው። በውጊያው ላይ ህይወቱን ከማጣት የተረፈው በተአምር ነው ማለት ይቻላል ። አንድ የጥልያን ወታደር በባልቻ ግንባር ላይ አናጣጥሮ የተኮሰው ጥይት የጀግናውን ጆሮ ሎቲ ማሰርያው ላይ በጥሶት አለፈ። ከጦርነቱ በሁዋላ ባልቻ በደረሰበት አደጋ ምክንያ አጥርቶ መስማት ሳይችል ቀረ። በጊዜው ጉትቻ ማንጠልጠል የገዳይ ወይም የዝሆን አዳኝ ምልክት ነበር። ለምሳሌ -ዳግማይ ምኒልክ : ግራ ጆሮው ላይ ያልማዝ ሎቲ ያንጠለጥል እንደነበር ይነገራል። የዚያ ዘመን አዝማሪት : በባልቻ ጆሮ ላይ የሚታየው የወርቅ ወይም ያልማዝ ሳይሆን የጥይት( የርሳስ ) ምልክት መሆኑን ስትነግረን:

“ማን እንዳንተ አድርጉዋል : የርሳሱን ጉትቻ
መድፍ አገላባጩ አባ ነፍሶ ባልቻ”

ብላ ዘፍናለታለች።

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • wondafrashaber@yahoo.com'
    ወንዴ commented on May 2, 2020 Reply

    ሰሞኑን ወሻባ ማለት quarantine ነው ያሉ አሉ ብውቄ አንተ ደሞ እዚህ ፅሁፍክ ላይ ወሻባ ማለት steam bath መሆኑን አስረድተሃል፡፡ የትኛው ነው ትክክለኛ ትርጉሙ፡፡
    ሁለቱም ክህክምናው አለም ውስጥ ያሉ ቢሆኑም በፅንስ ሃሳብ ደረጃ ግን ለየቅል አይመስሉክም?

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...