Tidarfelagi.com

ግጥሎት

ቀጥሎ የምታነቡት ነገር በግጥምና በፀሎት ማሃል ያለ ነገር ነው። ግጥሎት ብየዋለሁ😉ትናንት በእንቅልፍና በንቃት ማሃል ሆኘ የመጣልኝ ነው። ወፍ እንዳገሩዋ ትጮሃለች! ነፍስ እንደዘመኑዋ ትፀልያለች! የፅሁፌ አላማ ራሴን እና ብጤዎቼን ለማዝናናት ብቻ እንደሆነ ይታወቅ!

አባት ሆይ ! እንሆ ዛሬ ተወለድሁ!
ካለመኖር ወደ መኖር ተሰደድሁ።
ፋኖቼን በመልካም እድል -ፋኖዎቼን በካራ ባርክልኝ
ከእድሜየ ጨመር ከርጅናየ ቀነስ
በተከዘች ልቤ ላይ ትንሽ ደስታ ነስነስ- አርግልኝ

አባትሆይ የናቶቼ አምላክ
Wish me good luck
የእለት እንጀራየ ደርሶኛል አሁን ደሞ ወጡን ላክ።

በጨለማ የጠፋሁ ልጅህን -በጄኔረተር ታግዘህ ፈልገኝ!!
አህያ የነዳሁ ልጅህ- የግል ጄት ስነዳ ልገኝ።
የመንፈቅ ኮቴን -ያመት ቦይኮቴን አትንፈገኝ!

አባት ሆይ
በስተጎኔ ግራና ቀኝ ጣምራ ክንፎች ግጠምብኝ
ወይም ለጄት
በቂ በጄት
ልቀቅብኝ።

ጌታሆይ እረኛየ ነው
በለመለመ መስክ ያሳድረኛል።
እኔ ግን በግ አይደለሁም ካንጋሮ ፍራሽ ያምረኛል።

አባት ሆይ !

ከፀጋየ ባጋራ የማውቀውን ባካፍል
ከስድ ዘመን ተቃራኒ ቅኔና ወግ ብፈለፍል
እንዴት ያቅራራብኛል ማንም አንደኛ ክፍል
ጌታሆይ ጠላቴን አርበድብደው!
ስንቁ እንደ ጥጥ ሸክም ይቅለል-ቆለጡ እንዳለሎ ይክበደው!
አባት ሆይ ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ!
ጨለምተኝነቴም አለቀ!
በነገራችን ላይ በላይ ዘለቀ
አማራ ነው ኦሮሞ
አሁን ይህን ከዚህ ፀሎት ጋር ምን አገናኘው ደሞ?

አባት ሆይ ተመስገን! ተመስገን
ተመስገን ደሳለኝ!
እኔስ ያላንተ ማን አለኝ?!

እበላለሁ እሰባለሁ
እወጣለሁ እገባለሁ
እገባለሁ እወጣለሁ!
ግን ከጭቆና መች አመልጣለሁ?
እንኩዋስ በምድረ ጦቢያ እዚህ አመሪካ አገር
የማርቲን ሉተር ሀውልት እንደ ማለዳ እንትን ቢገተር
black lives don’t matter.

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

 • birhantewolde@gmail.com'
  tewolde commented on July 19, 2017 Reply

  አንተ በሕይወት ሥትሳለቅ
  እኛ በኑሮ ስንሳቀቅ
  ስጋችን እየገዘፈ
  ብዙ መንግስት አለፈ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...