Tidarfelagi.com

ግጥሎት(ግጥምና ጠሎት)

ሲፈርድብህ በማለዳው እንዲህ ያለ ሀሳብ ይልክብሃል!!

ግጥሎት(ግጥምና ጠሎት)

አቤቱ ውሃን አየር ላይ ያረጋህ
ከቀዳሚ ትውልድ ፤እስከ ከዳሚ ትውልድ ዘመንህን የዘረጋህ
በጃርት ወስፌ ጠንቁለህ ፤ያሞራን አይን ያፈሰስህ
ካላጣኸው እጄጠባብ፤ ኤሊን ድንጋይ ያለበስህ
ካልቸገረህ ወጣትነት፤ አዳምን ባርባ ዐመት ያስረጀህ
በህዳር በሽታ ዘመዶቼን የፈጀህ

ሀቅ ሀቁን ልንገርህ፤ እንደሌሎች ሳልሸነግል
ድሃ ሲጠልይልህ፤ ሃብታሞችን ምታገለግል
በሊብያ ምድረበዳ፤ባርያ ምታስፈነግል

ያባቴ አምላክ ያያቴ
አቤቱ እድል ፋንታየ፤አቤቱ እድል ስፕራይቴ
ርዳኝ
ወደ ዶላር ክምር ንዳኝ
ድህነቴ ለዘላለም፤ አስጎንብሳ ከምትከዳኝ
የቺስታነት ዘመኔ፤እንደቁመቴ ይጠር
ለዘላለም ከምትቦዝን፤ ለኔ ሚሆን ስራ ፍጠር
ከሻኪሶ የወርቅ መስክ፤ድርሻየን ሸርፈህ እጠር
ወይ ፈረንጁን አራራልኝ ፤save the children ልቀጠር

ያ ካልሆነም አንደበቴን ፤ነቢይነት አስተምራት
አድርገኝ መላከ መንክራት
ኩርማን ልቤን ውሰድና፤ባዱኛ በዝና አስክራት
በበጎች ሀብት አምበሽብሸኝ ፤ በመባ ባስራት በኩራት
ይሄ ሰንበሌጥ ምመን ፤ ከፊቴ ይውደቅ ይነሳ
ልፎግረው በምላሴ ፤ልገርስሰው በዳበሳ
እንደ አባባ ማርግ ፤እንደ ፍልስጤም ዳንሳ

አቤቱ ድንቅ ነው ስራህ! አቤቱ ድንክ ነው ስራህ
በዳይኖሰር መቃብር ላይ፤ የሰውን ህይወት የዘራህ
አቶ ምላስ ዜናይን እያጣደፍህ የጠራህ
ሙጋቤን ከጥልቅ እንቅልፍ ፤ወደ ወታደር እቅፍ የመራህ
የነጂዎቻችን እጣ ፤ከኒህ ጋራ ይደመር
በርካሽ የገዙን ሁላ፤ ፍጣሚያቸው አይመር
አሳልፈህ ስጣቸው፤ ለሪህና ላይዛመር፤

ጠሎተን እንኩዋን ባትሰማው፤ አደራ ባርክልኝ ግጥሜን
በተቀረ ርሳኝ ልርሳህ ፤ድምስስ አድርገው ስሜን
አሜን ብያለሁ አሜን
አሜን!

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

2 Comments

 • birhantewolde@gmail.com'
  tewolde commented on November 25, 2017 Reply

  በውቄ …
  ጠሎትህ ከላይ በራማ
  ሳይደርስም ቢቀር ባይሰማ
  ልመናህ ግን ተሰምቷል
  ቅኔህ መሪዎቻችንን
  ግጥምህ ደግሞ ቤት መትቷል

 • lesanejhjhiojllo@yahooo.com'
  ልሳን commented on December 19, 2017 Reply

  ርዳኝ
  ወደ ዶላር ክምር ንዳኝ
  ድህነቴ ለዘላለም፤ አስጎንብሳ ከምትከዳኝ
  የቺስታነት ዘመኔ፤እንደቁመቴ ይጠር
  ከሻኪሶ የወርቅ መስክ፤ድርሻየን ሸርፈህ እጠር
  ወይ ፈረንጁን አራራልኝ ፤save the children ልቀጠር ብቻ ቢሆን ግጥሎትህ ወደ ራማም ይጠጋ ነበር

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...