Tidarfelagi.com

“ግሪን ካርድ” 

ከማይሰበረው እፍታ!...

የአሜሪካ ኑሮዬን ትቼ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩና ኢንቨስትመንት ከጀመርኩ በኋላ፣ ለስራ ጉዳይም ሆነ ቤተሰብ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ወደ አሜሪካ እመላለስ ነበር። ሁሌም አሜሪካ ደርሼ ከአውሮፕላን እንደወረድኩ በኢሚግሬሽን ሰራተኞችና በጸጥታ ሃይሎች የሚደረግልኝ አቀባበል በጥርጣሬ የተሞላ ነበር። ከአሜሪካ የወጣሁበትን ጊዜ ከፓስፖርቴ ላይ በመመልከት፣ ረጅም ጊዜ ከአገር ውጭ እንደቆየሁ ሲያረጋግጡ በጥርጣሬ ነበር የሚያዩኝ። የአሜሪካ ግሪን ካርድ እያለኝ ለረጅም ጊዜያት ከአገር ውጭ መየቆቴ፣ በአሜሪካውያኑ የጸጥታ ሰራተኞች ዘንድ ጥያቄ ይፈጥር ነበር።

“እስከ አሁን የት ነበርክ?… ምን ስታደርግ ነው የቆየኸው?…” ምናምን ምናምን እያሉ በጥርጣሬ ተሞልተው ብዙ ጥያቄዎችን ያቀርቡልኝና ጥብቅ ምርመራ ያደርጉብኝ ነበር። ይህ ግን አንዴ ብቻ አይደለም፤ ወደ አሜሪካ በሄድኩ ቁጥር ይደጋገምብኝ ነበር። ወደኋላ ላይ ግን ይሄ የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ ያሰለቸኝና በእጅጉ ያማርረኝ ጀመር።

የሆነ ጊዜ ላይ፣ “ግሪን ካርዴን መልሼ፣ መገላገል እየቻልኩ ለምን እማረራለሁ?” ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ወደ አሜሪካ ተመልሼ የመኖር ዕቅድም የለኝም። በምፈልግበት ጊዜ የቱሪስት ቪዛ አውጥቼ በነጻነት አሜሪካ መግባትና መውጣት እንደምችል አውቃለሁ። ስለዚህ ግሪን ካርዴን አስረክቤ በፈለግኩት ጊዜ ያለእንግልት ወደ አሜሪካ የምገባና የምወጣ ነፃ ሰው ለመሆን ወስኜ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሄድኩ።

የኢምባሲው ሰራተኞች ግሪን ካርዴን መመለስ እንደምፈልግ ስነግራቸው፣ በከፍተኛ ጥርጣሬና መደነቅ ነበር የተመለከቱኝ። ምክንያቱም ከዚያ በፊት ግሪን ካርድ ልመልስ ብሎ ያመለከተ ሰው ገጥሟቸው አያውቅም። ሰራተኞቹ ነጋ ጠባ ወደ ኢምባሲው ሲጐርፍ የሚያዩት አብዛኛው ባለጉዳይ፣ በአንድም በሌላም ምክንያት ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችለውን ቪዛ ፈላጊ ነው። ለበርካታ አመታት በአሜሪካ የኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሊያገኙት ያልቻሉትን የአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ ለመመለስ መወሰኔን ስነግራቸው ለማመን የተቸገሩት ለዚህ ነበር።

“እርግጠኛ ነህ ‘ግሪን ካርድ’ መመለስ ትፈልጋለህ?…” በማለት በጥርጣሬ ጠየቁኝ።
እርግጠኛ መሆኔን አረጋገጥኩላቸው።

“ቆይ ለምንድን ነው የምትመልሰው?” ሲሉኝ፣ ምክንያቴን ነገርኳቸው።

“ልብ በል… ‘ግሪን ካርድ’ህን ካስረከብከን በኋላ፣ መልሰህ ማግኘት አትችልም!… ይህንን ታውቃለህ?” ሲሉም ስጋታቸውን ገለፁልኝ። ግሪን ካርዱ እንደማያስፈልገኝና ላስረክባቸው የመጣሁትም መልሼ ለማግኘት እንደማልችል እያወቅኩ መሆኑን ነገርኳቸው።

በአሜሪካ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ የተሰጠው ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ፈቃዱን በራሱ ፈቃድ ለመመለሰ ሲፈልግ፣ በአገሩ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ በማምራት የተዘጋጀለትን ራሱን የቻለ ማመልከቻ ‘ፎርም’ መሙላት አለበት። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲም፣ አሰራሩ በሚያዘው መሰረት መሰል ጥያቄ ይዞ ለሚመጣ አመልካች ይህንኑ የማመልከቻ ‘ፎርም’ አዘጋጅቷል።

የኤምባሲው ሰራተኞችም የመኖሪያ ፈቃዴን ለመመለስ መወሰኔን ካረጋገጡ በኋላ ይሄንኑ ‘ፎርም’ መሙላት እንዳለብኝ ነገሩኝ፤ እኔም የተጠየቅኩትን ለማድረግ ተሰናዳሁ።

የሚገርመው ነገር ግን፣ ለታሰበለት አላማ እንዲውል በኤምባሲው የተዘጋጀውንና ለአመታት ፈላጊ አጥቶ የሆነ ጉራንጉር ውስጥ ተጥሎ የኖረውን ይሄን ‘ፎርም’ ፈልገው ለማግኘት ሰራተኞቹ የደከሙት ድካም ነው። ኤምባሲው ግሪን ካርድ ለመመለስ የሚፈልግ አመልካች አጋጥሞት ስለማያውቅ፣ ይሄን ‘ፎርም’ ተጠቅሞበት አያውቅም ነበር።
.
(“የማይሰበረው”፣ ገጽ 167 – 169)

One Comment

  • yonihareg41@gmail.com'
    Yonihareg41 commented on October 21, 2021 Reply

    Good

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...