Tidarfelagi.com

“ጊዜ ቤት” ጊዜ ያልተወሰደበት ፊልም

ከሰሞኑ ያላየኋቸውን የአማርኛ ፊልሞች ለማየት ዓለም ሲኒማ ጎራ አልኩኝ። …… እግር እና እድል ጥሎኝ “ጊዜ ቤት” የሚል ፊልም ላይ ተጣድኩ።

በእውነቱ ከሆነ በጓደለ እየሞላሁም ቢሆን ፊልሞቻችንን ‘ተበራቱ‘ የማለት ችግር የለብኝም። ይህኛው ፊልም ግን ቢብስብኝ ልፅፈው ወደድኩ።

ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ቢሳካ ጥሩ ነበር። (የፊልሙ መግለጫ ላይ ያነበብኩት) ……

ፊልሙ በሁለት በደም በተቃቡ ቤተሰቦች ታሪክ ላይ ያጠነጠነ ነው።

ገና ሲጀምር ሁለቱም ዋና ተዋናዮች ወጣት ሆነው ይታያሉ። ከ9 ዓመት በኋላ ወንድዬውን ከ20 አመት በላይ ያስረጁትና ህፃኑም 9 ዓመት ሆኖት… … እሷን ይረሷታል። (ያውም እስር ቤት ስለታለቅስ የከረመችን ሴት)
“ፍሪዥ ውስጥ ነበረች?” እንዴ?

ዳኛው የህፃኑን እናት ወህኒ ከወረወራት በኋላ ትራስ ይዞ፣ ጥርሱን ነክሶ (ህፃኑን ሊበላው ነው የሚመስለው) ይታይና በምን የታሪክ ሙሊት እንደሆነ ተመልካች ሳይገባው የህፃኑ አባት ሆኖ ያርፋል። …… (በነፍስ የሚፈላለጉ ቤተሰቦች እንደመሆናቸው ከከፍተኛ ጥላቻ ወደ ከፍተኛ ፍቅር ለመቀየር አሳማኝ ሽግግር አያስፈልገውም?)

ህፃኑ ታሞ አሳዳጊው ገንዘብ የሚለምንበት ቦታ ላይ ፀሃፊውና ዳይሬክተሩ ብቻ ማንነቱን የሚያውቁት ሰውዬ ዘንድ ሄዶ “የፈለግከውን ውሰድና ገንዘብ ስጠኝ“ ብሎ ይቆጣል። (አራጣ አበዳሪ ይሆናል ብዬ ጠረጠርኩ። ያስያዘውን ንብረት ባያሳውቁንም) …… በአንድ ትዕይንት ላይ “እመጓ”ን ሲያነብ ያየነው አሳዳጊ መዓት መፅሃፍት ሲሸጥ ይታያል። መፅሃፍ ነጋዴ ሆኖ ነበር? የራሱ ከነበሩ እና የሚሳሳላቸው ከነበር በሰከንድ ሲን ወይ መደርደሪያውን ቢያሳዩን ምን ነበረበት?
እዚሁ ተከታታይ ትዕይንት ላይ ለእህቱ ‘ላልመለስ እችላለሁ‘ የሚል የአደራ ደብዳቤ አስቀምጦላት እሷ አንብባ ሳትጨርስ ግን እሱ አጠገቧ ሆኖ ይታያል። ( ደብዳቤው ለምን ተፈለገ?)

አንድም የቀደመ ትዕይንት ላይ ያላየናት የሰውየው እህት ልክ ልጁ ሲታመም መጥታ በልጁ ፎንቃ እሷና ቤተሰቧ መውደቃቸውን ትደሰኩራለች። ኸረ ጎበዝ ፀሃፊው አክስትየው ያስፈለገችው ድንገት መሰለ

ከ9 ዓመት በፊት ዳኛ ሆኖ የፈረደባት ሰውዬ የልጇን በህይወት መኖር በፃፈላት ቅፅበት ከእስር ቤት የምትወጣው በምን የህግ አግባብ ነው? ልጄን እስካገኝ ድረስ ልቆይ ብላ ተዳብላ እየኖረች ነበር የሚመስለው። ሰውየው ራሱ አስወጣት እንዳንል እሱ ዳኝነቱን ትቷል። ……

የኋላ ታሪኳን በአግባቡ ያላየናት ገፀ ባህሪ ከእስር ቤት ወጥታ ለልጇ ልብስ መግዣ… … መንቀሳቀሻ ገንዘብ ከየት አገኘች?(ኢትዮጲያ ነውና ገንዘብ መሰረታዊ ችግራችን ነው) ከዛ ደግሞ ልጁ አሳ አጥምዶ የሚያመጣበትን ትዕይንት ለማሳየት ብቻ በሚመስል አካኃን ሲራቡ ደግሞ ይታያል። ተምታታብኝሳ!!

ከእስር የተፈታችው እናት ዘው ብላ የፈረደባት ዳኛ ቤት የልጇ አሳዳጊ ዘንድ ትመጣና በምን ታሪክ ስሌት እንደሆነ ባልገባኝ መልኩ በገዛ ቤቱ “ልጄም እኔም አጠገብ ድርሽ እንዳትል” ትለዋለች። እሱም ቤቱን ጥሎ ይሄዳል። ተመልሶ በሌላ ቀንም ልጁ ናፍቆት ሲመጣ ታባርረዋለች። …… እህህህ እሱስ ደግ ሰው ሆኖ፣ ለልጁ ብሎ…… ምናምን ብለን ሰበብ እንፍጠርና ሄደ እንበል። እሷ ረስታው ነው የሰው ቤት መሆኑን?

ልጁ እንደዛ የሚወደውን አባቱን አጥቶ ሳቁ እንኳን ከፊቱ አለመጥፋቱ በምን ስሌት ያሳምናል? አባቱን በርቀት አይቶት ከተደበቀበት ትዕይንት ውጪ በአባቱ መሄድ ሲያለቅስም ሲከፋም አላየንም።

ሸቀሸቀኝ፣ ፈቀፈቀኝ… የሚለው ጎረቤትየው ፊልሙ ውስጥ ያለው ሚና ምንድነው?
……
……
በጣም ብዙ የሚነቀስለት በምንም የማይሟላ ክፍተት ነው ያለው። እንደውም ሲመስለኝ ህፃኑ ዓይን ውስጥ እየገባ ያለ ታዳጊ ተዋናይ በመሆኑ እሱን ለመጠቀም ታስቦ የተሰራ እንጂ… … የታሪኩ ይዘትም ሆነ ሌላው ነገር ትኩረት የተሰጠበት አይመሰለኝም።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...