Tidarfelagi.com

ጉድጓዱና ውሃው

አንዳንዴ እያካፋ…… አዲስአባ ቀላል ደመና ተከናንባ…… እንደ ነጠላ…… ሲያካፋ፣ ፀሐይም…… ፀሐይ ከራ ወበቅና የቀዝቃዛ አየር እጥረት እግሮቼን አሳስሮአቸው ያጋጠመኝ ቦታ ተቀምጬ አገጬን እጆቼ ላይ አስደግፌ ሳስብ፣ ሕሊናዬ በእጅና በእግሩ እየዳኸ፣ እየወደቀ፣ እየተነሳ ወደ ንፋስ መውጪያ ይነዳኛል፡፡ ብጠላውም፣ ተዘርቼ የበቀልኩበትን ብጠላውም የማላውቀው፣ የማልረዳው ነገር ይስበኝና ሕሊናዬ ወደ ንፋስ መውጫ ይወሰዳል……
ግብተ-ህሊናዬ ሲጎተት…… እኔ ስስብ ከመሐል የሆነ ቀዳዳ ይፈጠርና…… እንደ መንፈስ ቀዳዳ ዐይነት ነገር…… የፍርሃት ቀዝቃዛ ሩሕ ያውም እንደ መርፌ የቀጠነች በውስጤ እያፋሸከች ታልፋለች…… እየቆየ ፍርሃቴ እያስፈራኝ ለግብተ-ሕሊናዬ ግፊት እጄን ስሰጥ ከኤልያስ ጋር እንዋኝበት የነበረው ኩሬ በቅዝቃዜውና በኩልነቱ እየተንቦራጨቀ…… እየሰረበ መትቶ ጎድጓዳውን ይሞላዋል…… አያለሁ
ዐይኖቼን ከድኜ አያለሁ……
የደረቁ ቅጠሎች እንደጀልባ ተቀንፈው…… በጠራው ውሃ ላይ እየተንከበከቡ ሲያልፉ……
አያለሁ በዛፎቹ መሐል ሰማይ የታጠበ ጉሎ መስሎ……
አያለሁ ኤልያስ በሙታንታ ብቻ ራቁቱን ሆኖ የኢሕአፓ ወረቀቱን ሲያነብ፣ ፀጉሩ በውሃ ተሳስሮ ፊቱ ጡጦ ጠብቶ እንደጠገበ ሕጻን ሠላም ……
አያለሁ ውሃ በእጆቼ ዘግኜ ስወረውር በነጠብጣቦቹ ውስጥ የሚያልፈው ብርሃን ዕንቁ የረጨሁ ሲያስመስለኝ……
አያለሁ እርግቦች ዛፍ ላይ ለፍቅር ሲወጡ……
ጨቅላዋን ያዘለች ዝንጀሮ ገደል አቅፋ ስታናውዝ…… ባልዋ የቀላ ደረቱን ከፍቶ አብራኩን ሲያክ……
አያለሁ እነዚያ አረንጓዴ ቅጠሎች እነዚያ እልፍ አእላፍ ሐመልማሎች ትርጉሙን የማላውቀው ዝማሬ ከጥንት ከተፈጠሩበት ዘመን ጀምረው የተማሩትን ሲያርከፈክፉት…… እስክስታቸውን አያለሁ……
ወንዙም የወንዙም ድንጋይ…… ዳገቱና ረባዳው፣ ግራጫው ሸጥ እንደትልቅ ጆሮ ተከፍተው ውሃ ውስጥ የሚወድቀውን ገላዬን ሲያዳምጡ
ያውቁኝ ነበርን?……
ቀዝቃዛው ውሃ…… ከልጅነት ቆዳዬ ላይ እንደ ተክለሐይማኖት ዕንባ እርኩስ መናፍስትን እንደቅርፊት ይጥላቸዋል…… ይጥላቸው ነበርን? ወንዙ ውስጥ ያሉ ሰይጣኖች እንደ ጥንቸል ይርበደበዳሉ…… ይርበደበዱ ነበርን?
ኤልያስን አየዋለሁ በማይገባኝ ጉዳይ ቆሞ ሲስቅ……
ውሃ እረጨዋለሁ……
እየሸሸ ይስቃል……
ውሃ እረጨዋለሁ……
በአየር ላይ እንደዘንዶ ተወርውሮ ገብቶ ባሕሩ ውስጥ ይደፍቀኛል፡፡
ዘተፈጥሮ የነበረ…… ዘማማርም፡፡
ውሃው ጠግቦ እንደተኛ ፍቅር ለስላሳ ነበር……
አየር አጥሮኝ ባቃስትም የውሃውን ለስላሳነት አደንቃለሁ፡፡
ኦ! ይኼ ውሃ እንዴት ለስላሳ ነው! እላለሁ፡፡
እላለሁ…… ሁሉ ለምን እንዲህ ለስላሳ አይሆንም እላለሁ፡፡
የልጅነት ኩሸታችን የሰራቸው ለመምቴዎች ወዲያ ጥግ እስከቁርጭምጭሚትዋ የተነከረችው ወይዘሮ ባትዋ ድረስ ቢመጡባት ስርቆት እንደተሳመች ሁሉ አልተንከተከተችም?
ውሃ ቀጂ ብላቴናስ ራቁት ደረቱ ላይ ተስቦ እየተጫወተ የተዘናፈለውን ቁንጮው አየተርገፈገፈ አልሳቀም?
ውሃ የሚቀዱ ሴቶች ሸተት ብለው ያልፉናል፡፡ አሪቅ ገላችንን አፍረው፡፡ ኤልያስ ሁለት ጣቶቹን አፉ ውስጥ ከትቶ ያፉዋጭላቸዋል…… ሲያፉዋጭ ስቀናበት፡፡ ያን ጊዜ በዓለም ላይ ሴቶች የሚፈልጉት አንድ ነገር ቆንጆ ፉጨት ይመስለኝ ነበር…… እስከወገቤ ውሃው ውስጥ ቆሜ አራት ጣቶቼን በአፌ አስገብቼ እኔም እሞክራለሁ፡፡ ትልልቅ ትንፋሽ ይወጣኛል…… ከውሃ ጋር የተደባለቀ…… ለሐጭ በአገጬ ላይ ይወርዳል፡፡
አቤት ሲያፉዋጭ ስቀናበት፡፡
ከላይ ካዙሪቱ ዐረግሬሳ መሬት ለቆ ባንዣበበበት…… በዚያም ጥላ ስር ቸልተኛ ቆቆች አንዱ አንዱዋ ላይ ቆሞ ኩታትዋንም በትኩረት ነክሶ በረከቱን ትፍ ሲያደርግ ሹፈት ተማርንሳ……
እንደገናም እዚያ ገደሉን ተንደርድረው ከመሃል እርከን የቆሙ የእንጆሪ ፍሬዎች ቅላታቸውን ንቀናልና እንዲታወሱን ራሳቸውን ከሾህ ጉያ ነቅለው በለጋ ሳሮች፣ በሚፈልቁ ርጥብ መንገዶች ላይ በምንጭ ውሃ ፈፋ ኮለልታ ወርደው ለውሃ እናት ጌጥ ቢሆኑ…… እንደ ሕይወት አድን አልቃምናቸውም?……
ደሞም እወዲያ ጋ ትንሽ ልጃገረድ የእናትዋን ነጠላ ስታሰጣ እጆችዋን ወደሰማይ ዘርግታ ሳትመልሰው ጭኖችዋ ከድተዋት የተጎሰጎሰ ቀሚስዋ ለቆ ያልደረሰ ሴትነትዋን አይቼ አፌን ለሳቅ አልያዝኩም? እና የደረትዋ የብር መስቀል የፀሀይ ብርሃን አርፎበት ጨረቃስ ወረደች ብንል……
ደሞስ በደረቀ የበጋ ዕለት ካፊያ ከመሬት የሚያነሳው የአፈር ጢስ ሳንባችንን እንደ እስረኛ ይዞት ስናቃትት ገበሬአችን ‹‹እሸት ማታ›› አላለንም?
ሾላዎች ቀልተውና ተከፍተው የውስጣቸውን ቁጫጭ በትንፋሻን አጥበን አልተጎራረስንም……
ይሄ ሁሉ ስጦታ ለምን ይዘነጋል?
በአውሊያ ያበጡ አበቦች በለዘዘ ዕለተ-ቀትር ፊታችን ላይ በውበት ሲፈነዱ…… እነሱን ወለላዎች የመጠጡ ቢራቢሮዎች ጀርባችን ላይ እንደንቅሳት ቢወቀሩ ምኞት አላለምንም?……
ይሄ ሁሉ ቀለም አማረ አላማረ ለምንስ በመረሳት ይታጠባል?
ደስታ አላቂ ነው፡፡ ሐዘንም አላቂ ነው፡፡ ውሸት አልኩ? ውሸት አልኩ እንዴ
አስባታለሁ ያቺን ትንሽ ጊዜ፣ ያቺን ትንሽ ዘመን…… የቆሰለ ባህር ላይ እንደምታንጸባርቅ ንዑስ ጨረቃ፡፡
ሐዘኔ ታሪክ መች ነበረው?
ሐሙስ አስቀይማኝ ወሰንየለሽ ነግቶ ዓርብ በጉጉት አላየሁዋትም?
በጀርባዬ ተንጋልዬ የደመና መልክዓምድር በዓይኖቼ አልቀረጥኩም? ባደከመኝ ቀትር ስርስ ጥላቸው አልጋረደኝም?
በሚያዚያ ነጭ ቀናት ጨረር በቅንድቤ ቀልቤ በሸውራራ ዐይኖቼ እንደሚያውቅበት ሁሉ የትምህርት ቤቴን በሬዱዎች (ነጋሳ እንደሚለው) አግድሜ አላየሁም? አግላይ ትኩረታቸውን ንቄ ያኮረኮረ ደረታቸውን ሳነብ ‹‹እንዴ?›› ብለው አላለፉኝም? የኩሸቴንም ሳቅ የሚጋራኝ ባይኖር እንኳን አብራኬ እንደበሰለ አልመዘንኩም?
ከሰል የመሰለው ሰማይ ላይ እግዜር የሚያሳየኝን ክዋክብቶች ስቆጥር ‹‹በቃህ› ያለኝ ማን ነበር?
ሰቆቃ የቀደደ ቁስሌንስ በጨረቃ ብርማ ጨረር አልሰፋሁም?
በምኞት ቅዠት እየተራመድኩ የገበያችንን ባቢሎን ሳቋርጥ ትርንጎዎች መዓዛቸውን ቆምጣጤዎች ቀለማቸውን መች ነፈጉኝ?
የጠራ ውሃ ባቁዋረበት እንቅልፋም ላሞች በሚግጡበት ሳር ሜዳ ላይ ለስላሳ ካፊያ ውስጥ ባዶ እግሮቼን ቆሜ የሳቅሁትስ?
እጄ ላይ ከያዝኩት የቡሄ ጥቢኛ ላይ በአፌ የተረተርኩት የኮባ ቅጠል አንቆኝ ስስል ጋጋሪዋን መች ተቀየምኩ?
በረመዳን ምሽት የገዳፊ እስላሞችን የቤት ግድግዳ ታክኬ ሳልፍ መረቅ ቢሸተኝ መዓዛውን በሳንባዬ ሳምኩ እንጂ መች ቀናሁ?
ደሞስ በሩፋኤል ሜዳ አደዮች ባሞጠሞጡበት በቢጫና አረንጉዋዴ የካፊያ ቀን በዚያ በተመረቀች ጷግሜ አሪቄን በዘመዶቼ ዐይን ስር ስሮጥ በሙርጤ መፍዘዝ መች አፈርኩ?
ጭር ባለ ቀትር የተበሳጨች ወይዘሮ ስጦዋን የዶሮ ሰልፈኛ ቢተከትክባት ‹‹ያንሳችሁ እቴ! ምጥማጥ ይላክባችሁና…… የተረገሙ…… አንገተቸውን እየጠመዘዙ መጣል ነበር!!›› ስትል እውነትዋን ነበር? ወደ ጓዳዋ ገብታስ የተንጀለጀለ እርጥብ ጡትዋን መዛ ነች ጤዛ ልጅዋ አፍ ውስጥ አላለበችም?
ትንሽ የክፋትና የደግነት ወሰን ተደበላልቆብኝ ልጅነቴን ማንተር ከብዶት……
ትንሽ ልቤ ቢከፋት
ዓይኖቼም እንባ ቢያቀሩ
ትንሽዋ ነፍሴ ብትነጫነጭም
ያገሬ ጠዋት ጎትታ አላነሳችኝም?
……ብቸኛ ቆዳዬ ላይ እኔ ችላ ያልኩ ዕለት ንፋስዋ እንደወላንሳ ክትባት ረጋብኝ አይደለ፡፡ የተደፈሩትን ዐይኖቼንስ የትዝታ ማይዋ በለሆሳስ አጠባቸው አይደለ፡፡
ከዚያ ኩሬዋ መፍሰስ ትጀምራለች…… ኩሬዋ መናድ ትጀምራለች፡፡ ጠራራ ያደከመውን የቀን ሕልሜ ተቆራርሶ ያልቅና አዲስ አባ መሐል እኔና ጉድጓዴ እንቀራን…… ማንም የማያያት ጉድጓዴ እንቀራለን፡፡ ጮሌዎችና ፖለቲከኞች፣ ሌቦች፣ የመብት ነጣቂዎች፣ የሀበሻ ድፍርስ ፈላስፎች፣ የንዑስ ከበርቴ ሸርሙጦች፣ የሚፈልጉትን የማያውቁ ተናጋሪዎች፣ ተቺዎች፣ የማያይዋት ጉድጓድ እንቀራለን፡፡
ከእነዚህ ሁሉ
አንዳንዶቹ ሾልከው ያልፋሉ……
አንዳንዶቹ ጉድጓዱዋ አፍ ዙርያ እንደ ሲሚንቶ ይመረጉና አፈር በመሰለ ጥርሳቸው እየሳቁ ያዩኛል……
አንዳንዶቹ…… ታከው…… በጨዋታቸው መቀመቄን እንደ ጥጥ ሊከድኑልኝ ይለፋሉ……
እንደ ወሎዬው፡፡
ግራጫ ቃጭሎች

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...