Tidarfelagi.com

ጉደኛ ስንኞች

እንዳለመታደል ሁኖ የጎጃሙ ጌታ የራስ አዳል ልጆች አሪፍ ያገር አስተዳዳሪ አልነበሩም። እንደመታደል ሆኖ ደሞ የተዋጣላቸው ባለቅኔዎች ነበሩ። ግጥሞቻቸው ከኑሯችን ጋር በጣም የተቆራኙ ናቸው። ለምሳሌ የግፍ ዘገባ በሰማን ቁጥር የምንቀባበለው።

“የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል”

የሚለውን ገራሚ ግጥም የደረሰው የራስ አዳል የበኩር ልጅ – በለው አዳል መሆኑን ብዙ ሰው አያውቅም።

ነገሩ እንዲህ ነው። የሆነ ጊዜ ላይ ራስ አዳል( ንጉስ ተክለሃይማኖት ) ታመው ቢተኙ: ልጃቸው መርዝ አድርጎባቸዋል ተብሎ ተጠርጥሮ ታሰረ።

( በዚያን ጊዜ የቫይረስና የባክቴርያ ምስጢር ገና ስላልተባነነበት አሜባ ያስተኛው ሁሉ ተመርዞ ነው ይባላል።) እና አያ በለው ወህኒ ቤት ውስጥ ፍዳውን ሲበላ የግጥም ቆሌ ከላይ የተጠቀሰውን ግጥም ገለጠችለት።

ዛሬ ገጣሚውና ግጥሙን ያበቀለው ገጠመኝ ተረስቷል። ይሁን እንጂ የጠፈሩን ስርአት ተደንቀሽ ሳትጨርሺ በምድር ላይ በሚሰራው ግፍ ህዋስሽን ሲያደነዝዘው ይህ ግጥም ወደ አእምሮሽ መምጣቱ አይቀርም። እና እንዲህ ትያለሽ :-

-ሃይለኞች ደካሞችን በሀሰት ወንጅለው የግፍ አይነት ስያዘንቡባቸው-ብልታቸውን ሲያኮላሹባቸው: ጥፍራቸውን ሲነቅሉባችው ለምን አንድየ ጣልቃ ገብቶ አያስጥላቸውም? ለምን በጎ ሰዎችን አብዝቶ አይሰራም? ለምን የክፉ ሰዎችን ልብ አያራራም? ወይም ለምን ለደካሞች ራሳቸውን የሚከላከሉበት አቅም አይሰጣቸውም? ለምን የማእከላዊን ገራፊ እጅ አይጎምደውም? ለምን ማእከላዊን በመብረቅ አያነደውም? ምናልባት ከመንበሩ ላይ ባይኖር ይሆን? እያልሽ ትመራመርያለሽ። ተመራምረሽ ምድራዊ መፍትሄ ትቀይሻለሽ። ወይም ምርመራው የማያዋጣ ከመሰለሽ እንደዘሪቱ ከበደ ” ኦ ምናለፋኝ /መልሱ ከጠፋኝ “ትይና ወደ እምነትሽ ታፈገፍጊያለሽ።
————-

የራስ አዳል ሁለተኛ ልጅ ራስ ሃይሉ ይባላል። ራስ ሃይሉ በጊዜው በብዝበዛ ባካበተው የንብረት የዘመኑ ሚቴክ ሆኖ ነበር። በንግስት ዘውዲቱ ዘመን አድራጊ ፈጣሪ የነበረው ተፈሪ መኮንን ራስ ሃይሉን “ጋማ “ብሎ ወደ ወህኒ ወረወረው። ጎጃምን ወደ ጠቅላይ ግዛቱ የጎጃምን ጠገራ ብር ደሞ ወደ ኪሱ ጨመረው። ራስ ሃይሉ በሰንሰለት ታስሮ ብዙ ስቃይ ደረሰበት።

ይሁን እንጂ እግሩ እንጂ ምላሱና ምናቡ አልታሰረም ነበርና ይቺን ግጥም ገጠመ:-

“ሰው በድየ ነበር እኔም እንደዋዛ
ቁናው ቁናየ ነው ትንሽ ዙሩ በዛ”

በስንኙ ላይ የምናገኘው የመጀመርያው መስመር የበደል ኑዛዜ ሲሆን ሁለተኛው መስመር ይግባኝ ጥየቃ ነው። ራስ ሃይሉ ህዝቤን በድያለሁ ግን የተሰጠኝ ፍርድ ከመጠን በላይ ነው እያለ ነው!!

በታሪካችን ከባለስልጣን ሰፈር እንዲህ አይነት የሞራል ልእልና ማግኘት ብርቅ ነው። ከዚያ በሁዋላ የመጡ ጌቶች ህዝብንእንደዋዛ ይበድላሉ። እንደዋዛ በደላቸውን ይክዳሉ። ሲፈልጉ ዝንብ እንኩዋ አልገደልኩም ብለው ይሸመጥጣሉ። ሲሻቸው በሌላው ላይ ይደፈድፋሉ። ከተጠየቅንም መጠየቅ ያለብን በጋራ ነው ብለው ሊያመጣጥኑ ይሞክራሉ። “በድያለሁ ተመጣጣኝ ቅጣት ይሰጠኝ “የሚል ባለስልጣን የለም። ባጠቃላይ የበደል ታሪክ ቀጥሏል። የፀፀትና ሀላፊነትን የመውሰድ ታሪክ ከስሟል።

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...