Tidarfelagi.com

‹‹ገዳዬ…ገዳዬ…››

(መነሻ ሃሳብ፤ የሞፋሳ (ኬንያዊ ገጣሚ) ‹‹ልጅቷ›› ግጥም)

ፀሐያቸው ጠልቃ በሰው ሀገር መሽቶብኝ ነበር።
ጨልሟል።

የተለመደውን አውቶብሴን ተሳፈርኩ።

አዲስ ነገር የለውም። ሁሌም የምጠብቀው፣ ሁሌም በጠበቅኩት ሰአት የሚመጣው የማይዛነፍ የእለት ውሎዬን የሚደመድመው አውቶብስ ነው።

እንደተቀመጥኩ፣ ሰንደቅ የሚያሰቅል ቁመት ያለው ውብም፣ ሎጋም ኢትዮጵያዊ ወንበር ሲፈልግ አየሁ።

አውቶብሱ ውስጥ ብዙ ክፍት ወንበሮች ነበሩ። ወደ መስኮቴ ዞርኩ እና ፀሎት ብጤ አደረግኩ። ብታውቁኝ ለዚህ አይነት ነገር ፀሎትን ያህል ነገር የማባክን ሰው አይደለሁም ግን… ፀለይኩ።

ፀሎቴ ተሰማ መሰለኝ አጠገቤ መጥቶ ተቀመጠ።

ከዚያ ምን ሆነ?

‹‹ሃ…ይ…›› አለኝ። ዝም ብሎ ‹‹ሃይ›› አልነበረም። ይሄ…አንድ ‹ሃ› እና ስድስት ‹ይ› ያለው ሃይን ታውቁታላችሁ? እሱ ነው! እንደሱ ነው ሃይ ያለኝ።

ዞር ብዬ ሌላ ትንሽ ፀሎት አደረስኩ።

ፈጣሪ በትንሽ ፀሎት ይሄን መለሎ አጠገቤ አምጥቶ ስላስቀመጠልኝ፣ አስቀምጦም እንዲህ ያለውን ሃይ እንዲለኝ ምላስ እና ከንፈሩን ስላቀናጀልኝ ሌላ ጸሎት አደረስኩ።

አስቡት…የመጀመሪያው ፀሎቴ ባይሰማ ኖሮ ይሄ አማላይ፣ ይሄ…ሳያነጣጥር ገዳይ አጠገቤ ይቀመጥ…ተቀምጦስ ሰላም ይለኝ ነበር…?

እንዳልኳችሁ አውቶብስ ተሳፍሬ አይነ-ግቡ ሰው በተሳፈረ ቁጥር፣ ወንበር በፈለገ ቁጥር እንዲህ አይነት ፀሎት የምፀልይ አይነት ሴት አይደለሁም።

የፈለግኩትን ሰው ለማግኘት ቃላትን የማሰናዳ፣
የከንፈር ቀለሜን የማደምቅ፣
አይኖቼን የማስለመልም፣
ጡቶቼን ከካኔተራዬ ገፍትሬ የማወጣ ፣
መቀመጫዬን ያለ አቅሙ የማንቀጠቅጥ ሴትም አይደለሁም።

በሃገሬ ናፍቆት እየተንገላታሁ …ግጣሜን አጥቼ ቁጭ ያልኩ ክፍት ሴት ነኝ።

ልቤን በልቡ ይቀይረኛል በሚል ተስፋ ወንድን በጭኖቼ ክፍተት የማስገባ፣ አለመማረክ የሰለቸኝ፣ ለድሪያ እንጂ ለትዳር አለመፈለግ ያቆሰለኝ፣ የትርጉም አልባ አጫጭር ግንኙነቶች ርዘመት ያታከተኝ ሴት ነኝ።

ልድገመው። የትርጉም አልባ አጫጭር ግንኙነቶች ርዘመት ያታከተኝ ሴት ነኝ።

አልፎ ሂያጆቹን ትቼ ስለዚህ ልጅ ብቻ የማወራችሁ ለዚህ ነው።

ለምን እንደሆነ ባላውቅም በልኬ ተሰፍቶ እዚህ አውቶብስ ውስጥ የተጣለ መሰለኝ። ያልዳነ ቁስሌን የሚያክመኝ ሰው እሱ መሰለኝ። …የበደሌ ካሳ በሚያምር ልጅ መልክ ተሰርቶ የተበረከተልኝም መሰለኝ።

መሰለኝ እንግዲህ…

አውቶብስ ላይ ከተዋወቅን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደውልልኝ ያንኑ ባለ አንድ ‹ሃ› እና ባለ ስድስት ‹ይ› ‹‹ሃይ›› አለኝ።

በተቀመጥኩበት አቁነጠነጠኝ። እንደ ሆነ ነገር ሰራኝ። ፈተነኝ…ይሄ ልጅ ክፉኛ ፈተነኝ።

በሚቀጥለው ቀን አንዱ ፓርክ ተቀጣጥረን ቁጭ ብሎ እየጠበቀኝ ነበር።

ጀርባውን ሳየው የሆነ ነገሬ እንደ ጧፍ ይቀልጥ ጀመር።

..ይመስለኛል እግሮቼን እንዲሄዱ የሚያደርገው ጡንቻዬ ነው። ይመስለኛል አጥንቴ ነው። …ይመስለኛል ሁለንተናዬ ነው። ምክንያቱም ጭርሱን መራመድ ተሳነኝ።

ቀልጬ ከማለቄ በፊት ድንቅፍቅፍ እርምጃዬን ሰምቶ መሰለኝ ወደኔ መጣ።

ፀሐይ ከሰማይ ወርዳ፣ እግር አውጥታ ወደኔ ትመጣ ይመስል የመቅለጥ ፍርሃቴ ይበልጥ ጨመረ።

‹የትኛው አካሌ ቀድሞ አመድ ይሆን ይሆን? › እያልኩ ቆሜ ቀረሁ።

አጠገቤ ሲደርስ አውቶብሱ ላይ ያላየሁትን አዲስ ፈገግታ ፊቱ ላይ ተመለከትኩ።

ሚዛኔ ተመለሰ። እግሮቼ በረቱ።

እንጃ ብቻ… ፈገግ ያሉ አይኖቹ ውስጥ የለመድኩት ነገር ሁሉ ታየኝ።

ፊቱ ላይ አራት ኪሎ ታየኝ። የድል ሃውልት፣ በተርታ ያሉት ጁስ ቤቶች፣ ከጀርባ ያሉት ሻይ ቤቶች ቁልጭ ብለው ታዩኝ።

ፊቱ ላይ ኢትዮጵያ ታየችኝ።

ፈገግታው በሰከንዶች ውስጥ አከመኝ።
ሚዛኔ ሲመለስ ተሰማኝ። እግሮቼ እንሂድ አሉኝ።

እጄን ያዘኝ እና መራመድ ጀመርን።

እየሄድን….እጁን ስለያዘኝ ብቻ ማንም የማይነካኝ፣ ክፉ የማያገኘኝ መሰለኝ።

ሁሉ ሰው ስሜን የሚያውቀው፣ ሁሉ ሰው የሚወደኝ ስፍራ፣ ሃገሬ….ኢትዮጵያ የሄድኩ መሰለኝ።

….አለ አይደል…በአያያዙ ውስጥ የሀገሬን መንገድ ያገኘሁ ያህል ተሰማኝ።

በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ‹‹ምን እንደሆንኩ አወቀው ይሆን?›› ብዬ ዞር ዞር ብዬ አየኋቸው።

‹‹ገዳይ ሰውነት ካለው መለሎ ጋር ሆኜ ላለመሞት እየታገልኩ እንደሆነ አስተውለው ይሆን?›› ብዬ ዙሪያዬን ቃኘሁ።

ቀጥሎ ምን ሆነ?

እልፍ አእላፍ ማታዎች ስንፃፃፍ እና በስልክ ስናወራ ከረምን።

ተፃፃፍን። ፎቶ ተላላክን። አወራን።
ተፃፃፍን። ፎቶ ተላላክን። አወራን።
ተፃፃፍን። ፎቶ ተላላክን። አወራን።

ከዚያ እንደገና ተገናኘን።

እመኑኝ። በሰው ሃገር ሆናችሁ የወንዛችሁን ልጅ- ያውም እንዲህ ያለውን- ስታገኙ ፈገግታው ሃገራችሁ ነው።

ለዚያ ይሆናል ከፈገግታው መላቀቅ ያቃተኝ።
ለዚያ ይሆናል አይኑን አይቼ መጥገብ የተሳነኝ።

አይኑ ውስጥ ወደ ሃገሬ የሚወስደኝ መንገድ አለ።
ምን ብዬ ላስረዳችሁ እንጂ …አባቴ ይሙት… እጄን አያያዙ ውስጥ ማንነቴ ሁሉ አለ።

በተገናኘን ምሽት ያን ጃን ሜዳን የሚያስንቅ ደረቱን ወለል አድርጎ የሚያሳይ ጠበቅም- ሳሳም ያለ ሹራብ ለብሶ ነበር።
ወይ ደረቱ! አቤት ደረቱ! ስለደረቱ አስር ግጥም በአስር ደቂቃ ልፅፍ እችላለሁ ግን የወሬዬ አላማ እሱ አይደለም።

እጅ ተያይዘን አብረን ስንራመድ፣ ስንስቅ፣ ፈገግ ስንል፣ ደረቱ ላይ ስጋደም፣ ደረቱ ላይ ሲያጋድመኝ፣ በአማርኛ ስናወራ መሸና የአበሻ ቤት ሄደን የሀበሻ ቡና በሀበሻ ወግ ጠጣን።

‹‹ቡና እወዳለሁ›› አለኝ።

እኔ ለቡና እስከዚህም አይደለሁም ግን እሺ ብዬ ጠጣሁ። ቶና አይደለም። በረካ አይደለም።

ያን ምሽት ከአቦል ልጅ ጋር ነኝና አምስት ስኒ አቦል ቡና ጠጣሁ።

ስኳር በጨመርኩ ቁጥር፤ ‹‹ስኳር ቡናውን ይገድለዋል…ቡና ያለስኳር ነው መጠጣት ያለበት…ሞክሪው›› ሲለኝ ስኳሩን በእሱ ተክቼ ስንት ስኒ ቡና ያለ ስኳር ጠጣሁ?

ስንቱን ስኒ ቡና ባዶውን ሳይመረኝ አንቃረርኩ?

ተለይቼው፣ ቤቴ ገብቼ ከዚህ ቀደም ስለማላዘወትረው ቡና – በተለይ ስለአቦል ቡና – ማሰብ ጀመርኩ።
በባዶ ቡና ፍቅር ተንገበገብኩ።

በሚቀጥለው እስካገኘው፣ ያለ ልማዴ በየቀኑ ስለ እሱ እያሰብኩ ስኳር የሌለው ወፍራም ቡና ማፍላት፣ መጠጣት ጀመርኩ።

ከዚያስ?

…ከነዚያ ምሽቶች በኋላ በድንገት ስልኬን መመለስ፣ ለመልእክቶቼ መልስ መስጠት አቆመ።
የት ገባ? አላውቅም። ብቻ…ብቻ ጠፋብኝ።

እደውላለሁ- አያነሳም።
እፅፋለሁ -አይመለስም።

አስራ ሶስት ቀናት አለፉ።
አስራ ሶስት እሱን-አልባ ቀናት ኖርኩ።

በአስራ አራተኛው ቀን…

ያ ልጅ… ፈገግታውን፣ እጅ አያያዙን፣ ሳንቃ ደረቱን ይዞብኝ ሲጠፋ…
ያ ልጅ… የሃገሬን መንገድ፣ ኢትዮጵያዬን ይዞብኝ ሲሰወር…
መሻር የጀመረ ቁስሌ መልሶ ማመርቀዝ ሲጀምር….

…በላይ በላዩ ባዶውን እጠጣው የነበረው አቦል ቡና በመአት ማንኪያ ስኳር እንኳን ይመረኝ ጀመር።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • abrahammitku@gmail.com'
    abraham commented on January 5, 2019 Reply

    GOD bless you hiwi……ta ta ta ta ta ta…..
    like like like

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...