Tidarfelagi.com

ጀምጃሚዎች (ቅፅ 2)

የቸኮልየት ሆቴል ባለቤት ጋሽ ካሌብ ባሁኑ ጊዜ ከጎኔ ይገኛሉ። የሆነች: በሳቅና በሳል ማሃል ያለች ድምፅ እያሰሙ አጠገቤ ያለውን ቁሞ-ቀር ሳይክል ይጋልባሉ። ጋሽ ካሌብ ወደ መጀምጀሚያው አዳራሽ የሚመጡት ሰውነቴን ላፍታታ በሚል ሰበብ የጂም ማሺኖች በጥንቃቄ መያዝ አለመያዛቸውን ለመሰለል ነው።

“አልተቻሉም ጋሽ ካሌ” አልኳቸው።

” አንተ ይቺን አይተህ ነው ” አሉ ጋሽ ካሌብ ” በሳምንት ሦስት ቀን ሸራተን እዋኛለሁ። ዋና ስልህ ዝምብሎ ዋና እንዳይመስልህ! ስዋኝ የቸኮለ አምባዛ አይቀድመኝም! እንዲህ እንዲህ እንዲህ..(በቀኝ መዳፋቸው የዝግዛግ ምልክት እያሳዩኝ) እልና ጫፍ ላይ ብቅ ! ። የሸራተን ሆቴል ደንበኛ ሁላ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ኧረ ይሄ ሰው !ገንዳውን አመሰው እያለ ያዳንቃል!”

በተገናኘን ቁጥር ይህንን ካምስቴ በላይ ነግረውኛል። የባለአራት ኮከብ ሆቴል ባለቤት ቢሆኑም የኩራታቸው ምንጭ ሸራተን ገብተው መዋኘት መቻላቸው መሆኑ ደነቀኝ። እኔና ብጤዎቼ ከመርቲ ጣሳ እና ከስሚንቶ የተሠራ ዳምፔል ከማንሳት ወጥተን: በርሳቸው ሆቴል ውስጥ ጂም ለመሥራት በመብቃታችን እናነጅባለን። ቢቀናን ከለታት አንድቀን በንብረት ጋሽ ካሌብን ለማከል እንመኛለን። እሳቸው ደግሞ አላሙዲንን ለማከል መላ እድሚያቸውን ይለፋሉ። አላሙዲን እስኪያክሉ ባላሙዲን የምቾት ክልል ውስጥ ያሳልፋሉ።

ማህበረሰብ ከታች ወደ ላይ የተዘረጋ ጫፍ አልባ መሰላል አይደል? ታችኛው ወደ ላይኛው እንዳንጋጠጠ ኖሮ ኖሮ ይሞታል።

ፊቴን ከጋሽ ካሌብ ወዲህ ስመልሰው- አየሁኝ አንዲት ሰው። ማናት? የማሆይ ገላነሺን ጭንቅላትና የጄኒፈር ሎፔዝን ቂጥ አስተባብራ የያዘች ይቺ ማናት? መርሃባ እንጂ ሌላ ማን ልትሆን ትችላለች?!

የተገናኘን ቀን ያወራነው ትዝ አለኝ።
*******

“ልቦልድ አነባለሁ። ግን ከጥቂቶች በቀር ያገራችን ደራሲዎች የፈረንጆችን ያክል አይመስጡኝም” አለችኝ።

“ቀረብሽ!! ባለም አንደኛ የሚባለው የፈረንጅ ደራሲ: ያገሬ ባላገር ከሚፈጥረው የተለየ ነገር እንደማይፈጥር የተረዳሽ ቀን ይቆጭሻል”

” አቦ ያገርፍቅርንና እውንታን አትቀላቅል!”

“ነገሩ ካገር ፍቅር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም-ለምሳሌ አንቺ ጌም ኦፍ ትሮንስን አድናቂ ነሽ”

” ለምን አልህ??”

“ቅድም ሞባይልሽ ሲጠራ የመጥርያው ዜማ የፊልሙ ማጀቢያ ሙዚቃ መሆኑን አውቂያለሁ”

“እና ከጌም ኦፍ ትሮንስ የሚስተካከል የፈጠራ ሥራ አለን እያልክ ባልሆነ”

“ባይገርምሽ: በፊልሙ ውስጥ የምናያቸው ባህርያት ሺህ ጊዜ ቢራቀቁ ካገራችን የታሪክና የተረት አድማስ አይሻገሩም። እንዲያውም ኢትዮጵያዊ አምሳያ አላቸው። ቲርየን ላንስተር ስንዝሮ ነው። የጠላቶቹን ቆዳ በቁም የሚገፈው ራምሴ ቦልተን ስሁል ሚካየል ነው። ጃንደረባው ሎርድ ቫሬስ ባልቻ ሳፎን ይመስላል። አንዱ ንጉስ ወንድሙን shadow በሚባል አስማት ሲያስገድለው ትዝ ይልሻል? : ታዲያ ይህ እናቶቻችን “ጥላ ወጊ ” የሚሉት አይደለም?”

የግራ ቅንድቧን ከፍ አድርጋ ስትሰማኝ ከቆየች በሗላ:
“የባከነ ትንታኔ ነው! ፊልሙን አላየሁትም” ብላ በረጂሙ ሳቀች።

በእፍረት የቀምቃሚ ጉበት የመሰለ ፊቴን እንዳታይብኝ ያለፍላጎቴ” ፑሽ አፕ ” መስራት ጀመርሁ።

መርሀባ : ከጎኔ ባለው ምንጣፍ ላይ በደረቷ ተኝታ ቀጠለች።

“ዲሲ ውስጥ የሚኖር ጏደኛ አለኝ!! የጌም ኦፍ ትሮንስ አድናቂዎች ማህበር አክራሪ አባል ነው። ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ አባላት ጋር በሳምንት አንድ ቀን እየተገናኙ ይበላሉ ይጠጣሉ ።ብዙ ነገር ያረጋሉ። ይህንን ሞባይል ከነሳውንድ ትራኩ የላከልኝ እሱ ነው”

እፍረቴን ዋጥ አድርጌ መለስሁ።

“ታቂያለሽ!! አንዳንዴ ስለሀገሬ ሳስብ የመከፋፈላችን ምክንያት ከብሄርና ከሃይማኖት ውጭ ሌላ የመቧደኛ ሀሳብ ስለሌለን ይመስለኛል። ለምን በኪነጥበብ ተቧድነን አንሞክረውም? ለምሳሌ’ በፍቅር እስከመቃብር ‘ ስም የሚደራጅ ፓርቲ ባቋቁም ብየ አስባለሁ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው አሰባሳቢ unifier ፓርቲ የሚሆን አይመስልሽም?” አልኳት።

“አይመስለኝም። በፍቅር እስከመቃብር ስም ፓርቲ ብታቋቁም ለወረቱ ብዙ ሰው ይጎርፍልሃል። ከጥቂት ጊዜ በሗላ አባላቱ የፊታውራሪ መሸሻ ደጋፊ እና የፊታውራሪ አሰጌ ደጋፊ ተብለው ይከፋፈላሉ ። የራሳቸውን ባንዲራ ይፈጥራሉ። በየፌስቡኩ መሰዳደብ ይጀምራሉ። ከተመቻቸውም ይደባደባሉ። የመቧደን ዋጋ መከፋፈል ነው።”
********

አሁን ከፊትለፊት ሰፈራችንን በጉራው ያስጌጣት ኢያሱ መርሃባን ለማስደመም መከራውን ሲያይ ተመለኩት። በጀርባው ተኝቶ ግብዳ የብረት ቀንበር ለመግፋት ይሟሟታል። የቤቱ ጣራ ደረቱ ላይ ወድቆበት እርዳታ የሚማጠን እንጂ ስፖርት የሚሠራ አይመስልም።

” ስማ አንት እኩለ-ሌሊት ፊት!” አለ አሰልጣኙ ላሎ” አምሳ ኪሎ weight ማለት ዝም ብለህ ዘው ብለህ ገብተህ እንደ ሰርግ ብፌ የምታነሳው ነገር አይደለም!! ልምድና ትግስት ይጠይቃል”
ላሎ ይህን ሲል ለኢያሱ ደህነት በማሰብ ብቻ አይመስለኝም። ከራሱ በቀር ያንን ብረት ማንሳት የሚችል ጀግና ባካባቢው እንዲኖር አይፈልግም።

“ምን ላርግ ?”

አለ ኢያሱ በላሎ ርድታ ተነስቶ ከሰውነቱ ላይ አቡዋራውን እያራገፈ።

“መጀመርያ ሳይክል አስራምስት ደቂቃ ስራ”

“ከጉርድ ሾላ እዚህ ድረስ በሞተር ሳይክል ነው የመጣሁ”

ስለጉረኝነቱ ብዙ ሀሜቶች ሰምቻለሁ። ላሎ እንደነገረኝ ኢያሱ የደመራ ቀን ጀርባው ላይ ስልክ ቁጥሩ የተጻፈበት ነጭ ካናቴራ ለብሶ ወደ መስቀል አደባባይ ወጥቷል ። ከቁጥሩ ሥር “አረማመዴ ላይ አስተያየት ካለዎት በሚከተለው ቁጥር ይደውሉልኝ” የሚል ፅሁፍ ሰፍሯል።

ኢያሱ አንድ ሰሞን “የተራቆቱ የጎዳና ልጆችን እናልብስ” የሚል የርዳታ ዘመቻ ጀምሮ ነበር። የመንደሩ ሰዎች ትርፍ ልብሳቸውን እያወጡ ሰጡ። እኔ ራሴ የጠበቡኝን ሁለት ጅንሶችና ሦስት ሸሚዞች አበረከትኩ። ኢያሱ ከጥቂት ቀን በሗላ “ልብሱን የማከማችበት መጋዝን መግዣ አዋጡ “ብሎን አዋጣን። መጋዘኑንም “የልብስ ባንክ “ብሎ ሰየመው።

የከጥቂት ጊዜ በሗላ የሰፈራችን የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደ ድሮው ተራቁተው መኖራቸውን ቀጠሉ። እያሱ በበኩሉ በየቀኑ ልብስ እየቀየያየረ መዘነጥ ጀመረ።

“ኢያሱ ከየት እያመጣ ነው ልብስ የሚቀያይረው?” ስል ጠየኩት ላሎን።

“ያው ከባንኩ እያወጣ ነዋ”

(ይቀጥላል)

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...