Tidarfelagi.com

ዶሮ ብቻ ያልሆነው የዶሮ ወጥ

የዛሬ አመት አካባቢ ኬንያ ለስራ በቆየሁበት ወቅት የአመት በአላችን ንኡስ ምግብ፣ የገበታችን ንግስት ዶሮ ፤ከ ‹‹ማዘር ቤት›› እስከ አምስት ኮከብ ሆቴል አንዴ በሩዝ፣ አንዴ በኡጋሊ እየታጀበች፤ ከቀን ላብ አደር እስከ ቁንጮ ፖለቲከኛ አፍ እንደዋዛ በየእለቱ ስትገባ ገርሞኝ ነበር፡፡

ይሄን አይቼ አይቼ፤ በአንዱ ቀን ኬንያዊው የስራ ባልደረባዬ የኢትዮጵያዊያን የተከበረ ምግብ ምን እንደሆን ሲጠይቀኝ ‹‹የዶሮ ወጥ›› ማለቱ ትንሽ አሳፍሮኝ ነበር፡፡

‹‹ዶሮ ብርቃችሁ ነው እንዴ>!›› ተብዬ ከነህዝቤ እንዳልሰደብ፡፡

ግን አልኩት ፤ ‹‹የኛ ምርጥ ምግብ ክሽን ዶሮ ወጥ ነው፡፡ ለአመት በአል ለአመት በአል ልዩ ተደርጎ ይሰራል››

‹‹እ…እኮ ዶሮ…?ይሄ እዚህ በየእለቱ በኡጋሊ የምናጭደው ዶሮ?››
‹‹አዎ ዶሮ ወጥ ነው ግን ዶሮ ብቻ አይደለም››
‹‹እንዴት…?ማለት…?››

ኢትዮጵያን ለማያውቅ ሰው ዶሮ ወጥ ዶሮ ብቻ አለመሆኑን ማስረዳት ቸግሮኝ ትንሽ ካሰብኩ በኋላ፤

‹‹እኔ ሀገር ዶሮ እንዲህ እንደናንተ ሃገር እንደዋዛ ፣ በዘፈቀደ ተካልቦ ተጠብሶ ፤ ተንቀዥቅዦ በሰሃን ከች አይልም፡፡ የኔ ሀገር ዶሮ ወጥ ምግብ ብቻ አይደለም፡፡ ወግ ነው፡፡ ባህል ነው፡፡ ቤተሰብ ነው፡፡ የዶሮ ወጥ ነው እንጂ የሚሰራው ከዶሮ ብቻ አይደለም፡፡››

‹‹ እኮ…እንዴት ማለት….?›› እስካስረዳው በጉጉት ይጠብቀኛል፡፡

‹‹አየህ፤ ዶሮ ወጥ መሰራት የሚጀምረው ዶሮው ሳይገዛ በፊት ነው፡፡ ከሳምንትና አስራ አምስት ቀን በፊት፡፡ ጊዜ ካለህ ዘለግ አድርጌ ልንገርህ…የነገሩን አስኳል እንድታገኘው…››

‹‹አለኝ›› አለኝ ፈጠን ብሎ፡፡

‹‹ ጥሩ እንግዲህ….! የዶሮ ወጥ አሰራር ቀ….ስ….ብሎ የሚከናወን ሂደት ነው፡፡ ልታፈጥነው አትችልም፡፡ ልታንቀዠቅዠው አይቻልህም፡፡ ከቀን ውሏችን ጋር የሚሸመን ግርማ ሞገሳም ክስተት ነው፡፡

በአል ከመድረሱ ሳምንት ወይ አስራ አምስት ቀን በፊት ስለዶሮ መግዛት ሲወራ፣ ሲታቀድ፣ ሲሰላ ይከርምና በአሉ አንድ ቀን ሲቀረው የሚከተለው ይሆናል፡፡

መጀመሪያ፤ እናቴ አባቴ ለዶሮ ወጡ ወጪ የሰጣት ገንዘብ በቂ እንዳልሆነ እየነጨነጨች ትነግረዋለች፡፡

ከዚያ ንጭንጯን እና እኔን ትይዝና ገበያ እንወጣለን፡፡

ከዚያ አንዲት ዶሮ ለመግዛት አስራ ምናምን ዶሮዎችን በቀኝ እጇ ይዛ እየመዘነች ከሻጮቹ ጋር በዋጋ ትነዛነዛለች፡፡

ከዚያ አንዱን ጥላ ሌላው ጋር ትሄድና ጥላው ወደሄደችው ትመለሳለች፡፡

ከዚያ መዝና ወደ ጣለችው ዶሮ ትመለስና እንደገና ትመዝነዋለች፡፡

ከጥቂት ሰአታት በኋላ በምርጫ ማጣት እንደገዛቻቸው በምሬት የምትነግረኝን ዶሮዎች ይዘን ቤት እንገባለን፡፡

ከዚያ ለዶሮ ወጡ ማጀቢያ የሚሆን ቀድሞ የተገዛ ፤ ስድስት ወይ ሰባት ኪሎ ሽንኩርት በቡድን ተደራጅተን መላጥ እንጀምራለን፡፡

‹‹ስድስት ወይ ሰባት ኪሎ….! ለአንድ ወጥ?!›› የስራ ባልደረባዬ ‹‹በያማታል እንዴ!›› አስተያየት እያየኝ ይጠይቀኛል፡፡

‹‹አዎ….››
‹‹ሆ…! ከዚያስ?››
‹‹ከዚያ ሽንኩርቱን ጎላ ድስት ውስጥ ጨምረን ሙቀቱ ‹‹ለዶሮ ስራ›› በተመጠነ ከሰል ላይ ለሰአታት እናቁላላለን›
‹‹ለሰአታት?!››
‹‹አዎ..ለሰአታት….››
‹‹ህም…እሺ…ከዚያስ?››

‹‹ከዚያ መአት መአት ዘይት ይገባበታል፡፡
እ…ል…ፍ.. በርበሬ ይጨመርበታል፡፡
እናቴና የቤቱ ሴቶች የዶሮውን ወጡን ድስት ከበን ያወራነው ወሬና የሳቅነው ሳቅ ይገባበታል፡፡
የትንሹ ወንድሜ ‹‹ቁሌቱን አቅምሱኝ›› ልመና ጠብ ይልበታል፡፡
አባዬ ዶሮውን ባርኮ ሲያርድ ቡራኬው ይታከልበታል፡፡
እስካሁን ዶሮ ወጣችን ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ የከሰል ጭስ፣ የኛ ወሬና ሳቅ፣ የትንሹ ወንድሜ ቁሌቱን አቅምሱኝ ልመና፣ የአባዬ ቡራኬ ገባባት ማለት ነው፡፡

ከዚያ እማዬ እኛን የምትፈትንበት በአል ከሆነ ( በዚያ በአል ከባድ እንግዳ ካልተጠራ እና የዶሮ መስራት ችሎታችን ተለይቶ ካልታወቀ) እኔ፤ ወይ እህቴ፣ ወይ እኛ ጋር የምትኖረው የአክስቴ ልጅ ብቻ አንዷ ተመርጣ፤ ዶሮውን በብልት በብልት ብትንትን አድርጋ ስታበቃ ሎሚ በተጨመረበት ውሃ ሃያ ምናምን ጊዜ ‹‹ቸፍ ቸፍ›› እያደረገች ታጥበዋለች…

‹‹አሁንስ በቃው›› ስትል እማዬ ‹‹ገና ነው ድገሚው›› ትላታለች፡፡
ክንዷን ከደከማትና ንጭንጭ ካበዛች ቅያሪ እንገባለን…

ከዚያ የተበለተው የዶሮ ስጋ ፤ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ የከሰል ጭስ፣ የኛ ወሬና ሳቅ፣ የትንሹ ወንድሜ ቁሌቱን አቅምሱኝ ልመና፣የአባዬ ቡራኬ ያለበት ድስት ውስጥ በወግ በወግ ይገባል፡፡

አሁን ዶሮ ወጡ ዶሮ ሲደመር ይሄ ሁሉ ነገር ሆነ ማለት ነው፡፡

ከዛ ‹‹ይሄ ድስት እንዳይይዝ›› እየተባለ በየደቂቃው ይማሰላል…

ይሄ ሁሉ ሆኖ ካበቃ በኋላ፤ መጨረሻው አካባቢ በቤተሰብ ልክ እንቁላል፣ በአቅም ልክ ቅቤ፣ በእማዬ ፈቃድ ልክ ቅመም ይገባበትና ፤ እንዲያ የተለፋበት ዶሮ ወጥ ሊገለፅ የማይችል ጠረኑን በቤቱ እየረጨ፤ አራስ ልጅ እንኳን በማይያዝበት ጥንቃቄ ከከሰል ይወርዳል፡፡

ያለማጋነን፤ የዛን እለት አብዛኞቹን የኢትዮጵያ ሴቶች ጠርተህ ‹‹ እህስ! ዛሬ ቀኑን ሙሉ ምን ሰራችሁ?!›› ብትላቸው ‹‹እህ! የማንን ሴትነት ለመሳደብ ነው …ዶሮ ነዋ!›› ነው የሚሉህ…

ዶሮ ወጥ መስራት የሴትነት ማእረግ ነው፡፡

የሚገርምህ ነገር ግን፤ ሁሉ ሴት በየቤቷ ዶሮ ወጥ ስትሰራ ውላ ብታመሽም፤ የየቤቱ ዶሮ ወጥ ልክ እንደ እያንዳንዱ ሰው አሻራ በፍፁም አንድ አይነት ጣእም ሊኖረው አይችልም፡፡

ዶሮውን አጅቦ በድስቱ ውስጥ በሚቁላላው ተጨማሪ ግብአት ምክንያት፤ የእያንዳንዱ ቤት ዶሮ ወጥ ቤቱን ቤቱን፣ ሰሪዋን ሰሪዋን ነው የሚለው፡፡

በዚህ ምክንያት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቤቱን ዶሮ ወጥ ጠረን በአፍንጫው መመዝገብ የሚጀምረው ገና ከእናቱ ጉያ ሳይወርድ ነው፡፡ ያቺን ጠረን ስንት ውቂያኖስ ቢያቋርጥ፣ ስንት ክፍለ አህጉር ቢረግጥ፣ ስንት ዘመን ከሀገሩ ቢርቅ እስኪሞት አይረሳትም…›› አልኩ የእናቴን ዶሮ ጠረን ከድሮ እየጠራሁ፡፡

‹‹ህም…ከዛስ….›› አይን አይኔን እያየ ጠየቀኝ፡፡

‹‹ከዛ፤እኩለሌሊት አካባቢ እንተኛለን፡፡
በነጋታው በታላቅ ትህትናና ጥንቃቄ ፤ በእማዬ እጅ ብቻ እየተጨለፈ የሚወጣውን ዶሮ እንጀራችን ላይ እያወጣን ገበታ ከበን ፤እያወራን፣ እየሳቅን፤ ተሰብስበን እንበላለን፡፡

እንግዲህ ወዳጄ፤ ለዚህ ነው ዶሮ ወጥ ከዶሮ ቢሰራም ዶሮ ብቻ አይደለም ያልኩህ….›› አልኩትና ደክሞኝ ወጌን ሳበቃ፤

‹‹እህስ…አሁን ስ ገባህ?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡

የግንባሩ ቋጠሮ ግር እንዳለው እያሳበቀ፤ ‹‹እም…አዎ…ግን ዞሮ ዞሮ ዶሮ ነው አይደል?›› አለኝ፡፡

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...