Tidarfelagi.com

ዳዊት

ዳዊት የታወቀ ታስሮ የተፈታ ሪቮ ነው። (በተማሪ ‘ትግል’ ታስሮ መፈታት ራሱ ‘ችሎታ’ ነው፤ በምን ሂሳብ እንደሆነ ባይታወቅም።) ዝናው በኋላ ከመጡት ከነመኮንን ይበልጣል፣ ከነጥላሁን፣ ከነዋለልኝ ይስተካከላል። የተናገረው ነገር ብዙው መሬት ቢወድቅም፤ በትክክል ማን ዝነኛ እንዳደረገው እንዴት ዝነኛ እንደሆነ ባይታወቅም…… የዝነኝነት ስሙን ብቻ ተጠቅሞ፣ አራግፎ ጠርጎ የፈለገውን የሃሳብ ቂጣ ለተማሪ ያበላል።

ይሄ የፖለቲካ ማሕበራዊ ልምዱና ያለትችት የተደነቀው ስሙ ብዙ አይነት ዝርያ ካላቸው ሴቶች ጋር አገናኝቶታል።

እንደማርታ ደፋር የሆኑ በግራ እጃቸው ቦምብ፣ በከንፈሮቻቸው ፖለቲካ፣ በቀኝ እጃቸው ደ’ሞ ቀሚስ የሚገልቡ አስቀያሚ ሪቮ ልጃገረዶች እግሮች መሃል ገብቶ ወጥቷል ……

እንደ ማኦ ብብት እንደሮዛ ሉክዘንበርግ ዐይንአር የሚሸቱ …… ወይም ቅን ሴቶች …… የአናቱ አፎሮና አንደበቱ የሳባቸው፣ ወይ በዝነኛ ወንድ ደረት ስር ተደርምሰው መሞትን የሚሹ …… ከራሳቸው፣ ከአገራቸው ወይ ከንጉሠ ነገሥት ኃይለስላሴ የተጣሉ …….

ከሁሉም የሴት አይነት የሰበሰበው ተሰብስቦም የጠለለ ልምድ አለው ……
ይሄ ልምድ ቁንጅናና በተለይ ዝርያ እንዲለይ ያደርገዋል።

ፊታቸውን ብቻ በመሰለል በቀላሉ ተገፍተው የሚንጋለሉለትን ያውቃል።

በአንደበቱ የተወጠሩት እንማን እንደሆኑና መቼ መርገብ እንዳለባቸው ያውቃል …….

ዝና የሚያቀልጣቸውን የሴት ዐይኖች ገና ሲያያቸው ያውቃቸዋል ……

ሲዝናናባቸው የሚደሰቱ፣ ‘ዳዊት አርጎኛል’ ብለው ሽንት ቤት በር ላይ ከመጻፍ የማይመለሱትን ገና ሰላም ሲላቸው ያውቃቸዋል ……

በዚህ ሁሉ አልፎ ግንባሩን ሳያጥፍና ሳይጠራጠር ብዙው ሴት ‘ጅል’ ነው ብሎ ያምናል። አንዱ ምክኒያቱ እሱ እንደሚለው በአጠቃላይ ስቱደንት ቦዲ( Student Body) የተባለው አንድ ትልቅ በረት የጅሎች መሰባሰቢያ መሆኑ ነው። ለዳዊት ሴቶቹ የዚህ ትልቅ አክል ንዑስ ስብስብ (Subset) ናቸው።

በአዋጅ ያልተጠቀሰ ፈላጭ ቆራጭ ነው። አመለካከትህ ተወናከረ የሚሉትን፣ ስህተትህን ልጥቀስ፣ ልመዝግብ የሚሉትን ይቀጣል። የእነዚህን ዐይነት ሰዎች ስም ያጠፋል፣ በካምፓስ መኖርን እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል። አልተመዘገበም እንጂ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ‘ረባሽ ናቸው’ ብሎ ካባረራቸው ተማሪዎች የበለጠ እሱና ሽርኮቹ ከካምፓስ አማረው ያስወጡት ተማሪ ቁጥሩ ይበዛል።

ያን ካልቻለ የሕብረተሰቡን ዓይን አፋርነት ተጠቅሞ በራሱ ይሉኝታ ያፈዘዋል። ነቅተናል ቢሉ የሚሉት ቢብስ ‘ይሉኝታም አያውቅ?’ ነው። (ያውም በየዶርማቸው በሹክሹክታ)። አበሻ የሚፈራው ዐይናውጣና ይሉኝታ ነው።
ዳዊትን ከተቹትና ካሙት በኋላ ተመልሶ መጥቶ ግን እንደናዳ ይወርድባቸዋል፣ ለፍላጎቱ ይንበረከካሉ።

ተማሪውን ከትምህርቱ እየለያየ ቤቱ የሚያስገባው፣ እያስገባ የሚያስወጣው በሃሳቡ ረቂቅነት አልነበረም። በአደገበት ይሉኝታ እየተጫወተበት ነው። ተማሪዎች በተደጋጋሚ እየተንጋጉ እሱና መሰሎቹ ለሚሰሩት ተንኮል ሲገዙና ውድ የትምህርት ጊዜአቸውን ሊያፈርስባቸው ነገር/ፖለቲካ ሲጠመጥም ቆመው ይከራከሩታል (ሌላ አገር ቢሆን ይደበድቡታል)።

ከዚህ ሁሉ ተነስቶ ከወጣቶቿ፣ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪ ቂልነት ተነስቶ አገሪቷን ይንቃል። ዛሬም ብቻ ሳይሆን ወደፊትም እንደማይክዱት ያውቃል። ጅልነታቸው እንደማይለወጥ፣ እንደማይሰረዝ፣ እንደማይጠፋ ከአሁን ጸባያቸው ይገምታል። እና ሁልጊዜ ልፍስፍስ ሃሳቡን ‘ወደፊት ታሪክ እንዳይታዘበን’ በሚል ሐረግ ያስረዋል። ዛሬ ጡጦ እንደሚጠቡ ሁሉ የሚሸውዳቸው ወጣቶች አርጅተው ጡጦ መጥባታቸውን እንደሚቀጥሉ ይገባዋል። ወደፊትም ሽበት ከከበበው አፋቸው፣ ከደኸየ ምላሳቸው ፍሬ የማያወጣ ቃል እያዝረበረቡ የእሱን ታሪክ አዳንቀው ይጽፉለታል።

***
እቴሜቴ ሎሚ ሽታ

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...