Tidarfelagi.com

ደስታን በብልቃጥ

‹‹ላግባሽ›› ብሎ ሲጠይቀኝ…
አይኖቼ እንደ ስልሳ ሻማ አምፖል እየተንቦገቦጉ፣ የሰራ አከላቴ እየፋመ፣ ከንፈሬ መርበትበቴን ለማሳበቅ እየተንቀጠቀጠ፣ ሰውነቴ ያለ አግባብ እየተናወጠ…
ይሄ ሁሉ አይሰሙ ደስታ እየተሰማኝ ፤ ቃላቶቼን መጥኜ፣ መፈንደቄን ደብቄ ቀዝቀዝ አልኩና፣ ረጋ አልኩና፣ በሴት ልጅ ወግ፤ ‹‹እሺ…›› አልኩት።

ይወደኝ ነበር።
እንደሚረግፍ አበባ የሚንከባከበኝን፣
ሟሙቼ አልቅ ይመስል የሚሳሳልኝ፣
ሰው አይይብኝ እያለ ከስንቱ የሚፋጅልኝ፣
በአይኖቹ ብቻ፣ በአስተያየቱ ብቻ ፤ ከልክ ያለፍኩ ቆንጆ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ የሚያደርገኝ፣
ብቸኛ ሰው እሱ ነበር።

በጣም ይወደኝ ነበር።
እኔን እያየ በማልናገረው ነገር አለመስማማት እስከማይችል ይወደኝ ነበር።
ስልክ ደውሎ ‹‹እሺ ፍቅሬ፤ ምን እያደረግሽ ነው›› ብሎ ሲጠይቀኝ እንደዋዛ፤ ‹‹አንዷ ቀሚሴ ተበትናብኝ እየሰፋሁዋት ነው›› ብለው ክው ብሎ፤ ‹‹ለምን መርፌውን ብቻሽን አነሳሽው! አልከበደሽም…?›› ብሎ የሚደነግጥልኝ አይነት አወዳደድ ይወደኝ ነበር።
ሶቶ ተያይዘን ጫካ ውስጥ ስንሄድ አንበሳ ቢገጥመን ፤ እንደውም…ጠመንጃ የታጠቀ አንበሳ ቢገጥመን፤ እኔን ለማትረፍ በድፍረት በባዶ እጁ ለመታገል ያህል ይወደኝ ነበር።

እና ታዲያ፤ ለምን አላገባውም?
እንዲህ አድርጎ የሚወድን ሰው እንዴት አለማግባት ይቻላል?
ደግሞ እኔም እወደው ነበር።
ፍፁም እንኳን ባይሆን መውደዴ ፍፁም ስላደረገው ፣ ለነገ ሳልል፣ ፍቅርን ሳልሳሳ፣ ስፍስፍ ብዬ እወደው ነበር።
አሳ ውሃን ፣ ህፃን ከረሜላን፣ ንብ አበባን እንደሚወዱ እወደው ነበር።
እና ታዲያ ለምን አላገባውም?
እንዲህ አድርገው የሚወዱትን ሰው እንዴት አለማግባት ይቻላል?

…እንግዲህ የሰርጋችን እለት ነጩ ዳስ ቦርቀቅ ባለ ቦታ ላይ ዝ…ር…ግ…ት ብሎ ተጣለ።
የሰው ልጅ የሰራው የመጠጥ አይነት ሁሉ …ጥቁሩም፣ ቡኒውም፣ ቢጫውም፣ ቀዩም፣ ነጩም፣ ቀለም አልባውም ፤ በጠርሙስም፣ በካርቶንም፣ በምንም እየሆነ እንደ ሰው ዘንጦ፤ ሺህ ሊሆኑ ጥቂት በቀራቸው ጠረጴዛዎች ላይ ተደረደረ።
እንጀራ እንደሚታጠብ ልብስ ተከመረ።
ጮማ የበዛበት ጥሬ ስጋ ነጭና ቀይ ቀለም ግድግዳ መስሎ ከዳር እስከ ዳር ተሰቀለ።
የተሳሉ ሺህ ቢላዎች የስጋ ግድግዳውን ለሚቆርጡ ሺህ እንግዶች ተዘጋጁ።
ፀሃይ እንኳን ብታየኝ በምትቀናብኝ አኳሃን ደምቄ፣
ከኔ በኋላ ለሚሞሸረሩ ሴቶች ሁሉ የሰርግ እለት ውበት መለኪያ እስከምሆን አምሬ ፣
ከሙሽራዬ ጋር ለሰርጋችን ታላቅ እራት ወደ ቤት ገባሁ።
ጓደኞቼ በቅናትም፣ በደስታም አጅበውኝ በሚዜ ወግ እየዘፈኑ፣ እያጨበጨቡ ተከትለውኝ ነበር።
ጓደኞቹ በ‹‹ለእኔ ባደረጋት››ም፣ በደስታም አጅበውት በሚዜ ወግ እየዘፈኑ እያጨበጨቡ ይከተሉት ነበር።
ያገኘንን ሁሉ እየሳምን ወደ ዳሱ ገባን።
ሺህ አይኖች እኔ ላይ ብቻ አረፉ።
ሺህ አይኖች እሱን ብቻ አዩ።
እልልታው ከልኬት መጠን አለፈ።
ጭፈራው ማንም አይቶት ከሚያውቀው ጭፈራ ሁሉ በለጠ።
ድ.ብ.ል.ቅ.ል.ቁ ወጣ።
በዚህ ሁሉ መሃል፤ ፍቅሬ፣ ሕይወቴ፣ እንደ አሳ ውሃዬ፣ እንደ ልጅ ከረሜላዬ፣ እንደ ንብ አበባዬ፣ አለሜ፤ …ቀኝ እጁን በነዚያ ሁሉ ሰዎች መሃል ሾለክ አድርጎ፣ ግራ እጄን ጭ…ብ…ጥ አደረገኝ።
የእጁን ቋንቋ አውቀዋለሁ።
‹‹አይገርምም…?ተጋባን እኮ!›› ማለቱ ነው።
እኔም መልሼ ‹‹ አዎ…ተጋባን!›› አልኩት- በቃል አልባ የእጅ አጨማመቄ።
እምብርታችን እስኪገለበጥ በልተን፣
ጢምቢራችን እስኪዞር ጠጥተን ፣
የዛን ሁሉ ሰው አይን ከቬሎዬ ላይ እያራገፍኩ ለጭፈራ ተነሳን።
የእልልታው ሞቅታ ሲጨምር፣
የሆሆታው ግለት ሲንር፣
የእናቱን ነጠላ እንደ ጊዜያዊ ተነቃናቂ ነጭ ጣራ በላያችን ላይ አድረገውልን፤
በ ‹‹እንግዲህ ሙሽሪት…
እንግዲህ ሙሽሪት…
መባልሽ ቀረ ወይዘሪት›› ዘፈን ይሄንን ጭፈራ ልኩን አሳየነው።

እኔ ግን፤
ከሺህ ሰው መሃል የታየኝ የእሱ የሚያበራ ፊት ነበር።
ከሺህ ሰው እልልታ በላይ የተሰማኝ የእሱ የለሆሳስ ‹‹እወድሻለሁ›› ነበር።
ከሺህ ሰው እስክስታ በላይ አይኔ የገባው የእሱ እስክስታ የማይችል ትከሻ ንቅነቃ ነበር።
በግርግሩ መሃል ፤ ሳብ እያደረገ…ሳያስጠጣ አንገቴ ላይ፤ ከጆሮዬ በታች ሳም ያደርገኝ ነበር።
‹‹መባልሽ ቀረ ወይዘሪት›› እያለ ሲያቅፈኝ በደስታ ጧ ብዬ ፈንድቼ ቬሎዬን ላበላሽ ነበር።
እያቀፈኝ፣ እየለቀቀኝ፣ የሰው ስልክ ሁሉ ምስላችንን ለመቅለብ ባነጣጠረው የካሜራ ብልጭታ ታጅበን፣
‹‹እንግዲህ ሙሽራው፣ እንግዲህ ሙሽራው
አባ ወራ ነው በተራው›› በሚለው ዘፈን በፍጹም ደስታ ጨፍረናል።
ይበርብኝ ይመስል እጆቹን ጥፍንግ አድርጌ ይዤ በማይሰማ ድምፅ ‹‹እወድሃለሁ›› ብዬዋለሁ።
‹‹አባ ወራ›› እያልኩ በሹፈት ስቄበታለሁ።
በሚርገበገበው የነጠላ ጣሪያችን ስር፤
በስልት ሳብ አድርጌው፣ አንገቱ ስር ገብቼ ‹‹ታድዬ…!አገባሁህ›› ብዬው ነበር።
አንድም ትከሻ ሳይዝል፣
አንዲትም እንጥል ለእልልታ ሳትሰንፍ፣
አያሆሆው ሳይቀዘቅዝ፣
ጭብጨባው ሳይንበጫበጭ፣
የሰርጋችን ደስታ ፤በ‹‹አሻ ገዳዎ›› ታጅቦ፣ በ‹‹ነይ ሙሽሪት›› ደምቆ፣ በ‹‹ይዟት ይዟት በረረ›› ተውቦ….ከሰርጉ የተረፉ ዶሮዎች ንጋትን እስኪያበስሩ ቀጥሎ ነበር።

ግን ምን ያደርጋል!
የተጀመረ ሁሉ ያበቃል እና የእኛም ሠርግ አበቃ።
ሠርጉ አብቅቶ ትዳር ተጀመረ።
ትዳር ተጀምሮ ልጆችን ፈጠረ።
ልጆች ተፈጥረው ፍቅር ለኑሮ እጅ ሰጠ።
ትከሻችን በኑሮ ሸክም ዛለ።
ብርቱ የነበረው ፍቅራችን ሰነፈ።
ስሜታችን ቀዘቀዘ።
ኑሯችን ተንበጫበጨ።
ፍቅር፤ በእለት ተእለት መፍጨርጨር፣ በአስቤዛ ገበያ፣ በልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ፣ በማህበር ቤት መዋጮ፣ በእናቱ ማሳከሚያ፣ በአባቴ ቀብር ማስፈፀሚያ ቡጢ ተዘረረ።
….ያለፈውን ሳስብ…፤ ሆኖልኝ ፤
… ያን የሚንቦገቦግ የፍቅር ስሜት ፣
ያን የማይገለፅ የሠርጋችን ፈንጠዝያ ቅፅበት በብልቃጥ አስቀምጬው፤
ኑሮ ሲፈትነኝ፣
ትዳር ሲያስከፋኝ፣
ፍቅር ሲያንሰኝ፣
ከመሳቢያ ወጣ እያደረግኩ፣ ወይ ባሸተው ወይ ባየው ምንኛ ደስ ባለኝ።
ግን የደስታዬ ዘመን በጊዜ ንፋስ አቅጣጫው ወደ አልታወቀ ስፍራ በርሮ ሄዷል።
ግሩም መአዛ እንደነበረው መልካም ሽቶ በኖ ጠፍቷል።

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • ተዘራ/ከድሬዳዋ/ commented on March 29, 2016 Reply

    ህይወት እምሻው ጎበዝ ድርጊትን በስእልመግለጽየምትቸል ጸሀፈናት አገላለጹን ወደድኩልሽ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...