Tidarfelagi.com

ደህና ብር ስንት ነው?

ይሄ የምሰራበት ድርጅት የሆነ ችግር አለበት ….ከምር!! ፀዳ ፀዳ ያሉ ስልጠናዎችና ስብሰባዎች ሲኖሩ እኔን አይልከኝም …( ፀዳ ያለ ስብሰባ ማለት አጀንዳው ምንም ይሁን ጥሩ የውሎ አበል የሚከፍል ማለት ነው) የዛሬ ወር የአየር ብክልት ምናምን የሚሉ ነጮች መጥተው ካሳንችስ አካባቢ ወደሚገኝ የሆነ ትልቅ ሆቴልሰው ላኩ ተባልን። “በቃ ጉዳዩ በቀጥታ እኔን ይመለከታል” ብየ ስዘጋጅ ሃላፊያችን ጋሽ አሰፋን እንድልካቸው አዘዘኝ። እስቲ ጋሽ አሰፋና የአየር ብክለት ምን አገናኛቸው … እሳቸው የድርጅታችን ካሸር ናቸው።

ቢሆንም አንጀቴ እያረረ እንደታዘዝኩት ጋሽ አሰፋን ላኳቸው። ጋሽ አሰፋ ይሄው አንድ ወር ሙሉ አንዲት ቃል ስለአየር ብክለት ሲያወሩ አልሰማሁም! በተገናኘን ቁጥር ‹‹አይ ምግብ …ቦፌው ብቻ ለዓይ የሚያጠግብ ›› ይሉኛል ….እንደውም መቸ ለታ ነው …
‹‹አብርሃም ሌላ ስብሰባ የለም እንዴ?….. በተለይ የአየር ንብረት ጋር የተያያዘ ጥሪ ከመጣ አደራ እንዳትዘለኝ …. በዛች አበል እንዴት ያለ ሙሉ ልብስ ገዛሁ መሰለህ ›› ሲሉኝ ነበር።

የዛሬ አስራ አምስት ቀን ደግሞ ስነተዋልዶ ጋር የተያያዘ አንድ ስልጠና መጣና ሁለት የድርጅቱን ሰራተኞች ለሶስት ቀን አዳማ እንድንልክ የሆነ ኤን ጅ ኦ በደብዳቤ ጠየቀ። ይሄስ አያልፈኝም ብየ ደስ ሲለኝ ሃላፊየ ኮስተር ብለው ‹‹አብርሽ …ሮዳስንና በየነን ላካቸው›› አለኝ …እንዴ ይሄ ሰውየ ለስነተዋልዶ መሞከሪያ ወጣቶች ላኩ የተባለ መስሎት ይሆን እንዴ …..ሮዳስና በየነ …. ያውም አዳማ …ያውም ለሶስት ቀን ተልከው ታየኝኮ ሲሰለጥኑ።

እዚህ የድርጅቱ ካፌ ውስጥ እንኳን ለምሳም ለሻይም ተዛዝለው ነው የሚውሉት ….ለማንኛውም ሮዳስና በየነ ለስልጠና ተላኩ … ስልጠናው ካበቃ በኋላ ሁለቱም የዓመት ረፍት ጠይቀው ሁለት ቀን ጨምረው ዘና ሲሉ ከርመው እየተፍለቀለቁ መጡ! ስለስነተዋልዶ የሰለጠኑትን ያካፍሉናል ብየ አይን አይናቸውን ባይ …ወፍ የለም! እንደውም አዳማ ያሳለፉትን አስደሳች ጊዜ ይተርኩ ጀመረ …. ፍቅራቸው ከፍ ብሎ መጡ! ጫጉላ ልከናቸው ምን ያድርጉ ….ስብሰባ የጣመረውን ማን ይለየዋል ወገኖቸ እንኳን ግለሰብ የፖለቲካ ግንባር የሚፈጠረው በስብሰባኮነው! ‹‹አብርሽ ሌላ ስልጠና ከመጣ አደራ …በተለይ ከከተማ ወጣ ካለ›› ይሉኛል ባገኙኝ ቁጥር …ወቸ ጉድ! ‹‹ስብሰባን እንደሶደሬ››

ከዚህ ሁሉ በኋላ ትላንት እጣው ለእኔ ወጣ …. (የጭቁኖችን እንባ የሚያብስ ሰማኝ አልኩ) አንድ በአለም ዙሪያ እየዞረ ‹ስራ ፍጠሩ› የሚል ስራ ፈት የጀርመን ድርጅት ባዘጋጀው ስልጠና ላይ እንድሳተፍ ድርጅቴን ወክየ ሄድኩ …. ምነው ልሄድ እግሬን ሳነሳ እግሬን በሰበረው!! ወይ ጥጋብ እናተ ….
ከተማው ውስጥ የቀረ ሃብታም የለምኮ!! ታፍኘ ልሞት ….በዛ ላይ እንዲች ብለው …ተስቷቸው እንኳን ስለሽ ብር አያወሩም ሚሊየን ብቻ ! ነጥብ ብቻ ….ምናምን ነጥብ ምንትስ ሚሊየን ዶላር ይላል አንዱ ….ሌላኛው ቅብርጥስ ሚሊየን ኢንቨስት ማድረግ ይላል ….. እኔ ይሄ የእግር ኳስ የዝውውር መስኮት ምናምን የሚባለው ነገር እዛ አዳራሽ ውስጥ ብርግድ ብሎ የተከፈተ ነው የመሰለኝ ..ተጨዋች ምናምን የሚሸጥበት ዋጋ የሚጠሩ አይነት ….ሚሊየን ዶላር ፓውንድ … ይች ሚሊየን እንዴት ነው የቀለለችው ….እ?

ለሻይ ስንወጣ … ከማን ጋር ልሁን ብየ ወዲያ ብዞር ቦርጫም …ወዲህ ብዞር በወፍራሙ የሚስቅ ሃብታም ያላበው ማጅራቱን አንሶላ በሚያህል ማህረም የሚጠራርግ ሃሃሃሃሃሃ አትለኝም …ሄድ ድድድ ሃሃሃሃሃሃ የሚል …..‹‹ዛሬ ገና አልባሌ ቦታ ዋልኩ›› ብየ ቢጤየን ፍለጋ ሳማትር አንድ ቅጭጭ ያለ አናቱ የከበደው ሚስኪን ላብ አደር ከሩቅ አየሁ ውሃ እየጠጣ … ሂጀ ሰላም አልኩት። በአክብሮት ከመቀመጫው እንደመነሳት ብሎ ሰላም አለኝ (ትህትና የደሀ ሀብት ) ተቀመጥኩ። አንጀት የራቀው ነገር ነው እንደኔ የሚሊየን ወሬ ተጫጭኖት ነው መሰል ፊቱ ላይ ድካም ይነበባል … ስልኩ ራሱ አራት መቶ ብር የምትሸጠው ኖኪያ ነበረች ! ይሄማ ብድር ሁሉ ይጠይቀኝ ይሆናል ብያለሁ በሆዴ!
በቃ ይሄ እንደኔው እግር ጥሎት የመጣ መሆን አለበት ብየ ዘና አልኩ! ወዲያው አንድ አካሄዱም ድምፁም የለበሰው ቀይ ኮትና ቀይ ኮፍያ ጋር ተዳምሮ ‹ሲኖ ትራክ› የመሰለ ቦርጫም ሰው ሁለት ሰዎች ጋር እኛ ወደተቀመጥንበት መጣ …..እንዲህ አለ ወደከሲታው ወዳጀ ለሰዎቹ እየጠቆመ
‹‹ይሄ ነው እከሌ ማለት ….ባለፈው ያንን የሪል እስቴቱን መቶ አምሳ ሚሊየን ብር ያስያዘልን ….ብሎ እርፍ! ኮስማናው ….ኮስምየ …ኮስሚቲ …አልኩ በሆዴ ቀድረ ቀላሉን ሚሊየነር እየተመለከትኩ! ከዛማ የሚሊየን ወጋቸውን ይጠርቁት ገቡ! ወይ ጉድድድ ይሄ ሚሊየን ከምንጊዜው ከመንፈስነት ወርዶ ስጋ ለበሰ …..

ከሻይ መልስ አሰልጣኛችን ፈገግ ብሎ አንድ ጥያቄ ወረወረ……
‹‹ እስቲ ከእናተ መሃል ቢያንስ አንድ ሚሊየን ብር የሌለው እጁን ያውጣ … ›› አሰልጣኙ በዚህ ሊያቆም መሰላችሁ …..‹‹አለማችን በአሁኑ ሰዓት ለአንድ እና ሁለት ሚሊየን ብር ቦታ የላትም …. ደህና ብር ኢንቨስት ማድረግ ይኖርባችኋል በብዛት መስጠትና እጅግ በብዛት መቀበል ይሄው ነው የአለም ወቅታዊ የቢዝነስ ኮንሴፕት …..››

ደህና ብር ?….ደህና ብር ስንት ነው? … የሚያሳቅቅ ያሳቃችሁ እቴ ! ምድረ ጥጋበኛ …. ምንስ ቢሆን ካሳንችስ መሆናችን ተረሳ እንዴ? ….ምንስ ቢሆን ኢትዮጲያ መሆናችን ተረሳ እንዴ? …. እኔ ለረዢም ጊዜ ሚሊየን የማውቀው ሰማኒያ ሚሊየን ነው …ህዝብ !!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...