Tidarfelagi.com

ይድረስ ለኢትዮጵያ -ዎቼ

1. ኢትዮጵያ አንድ (ለፍቅረኛዬ(ፍቅረኛዬ ለነበርሽው))

ኪያዬ፣ ማነው ጎበዝ ሰካራም የሰከረባትን ቅፅበት ይህቺ ናት ብሎ መነገር የሚችል? -ማንም! እኔም ባንቺ ወይንነት ስሰክር የሰከርኩባትን ቅፅበት አላስታውሳትም፡፡ በጣም መስከሬን ግን አውቃለሁ፡፡ አንቺ ግን በኔ ስካር፣ በኔ መንገዳገድ እና መኮለታተፍ ያ የሚያምር ሳቅሽን ትስቂብኝ ነበር አሉ፡፡

አልክድም! በፊት በፊት ወላንሳ ባህሪ ነበረሽ፡፡ ምን እንደነካሽ እንጃ የሆነ ጊዜ ላይ ግን “ሚያው“ አለብሽ፡፡

ኢትዮጵያዬ……. የማንም አረብ፣ የማንም ነጫጭባ በብሩ ጭንሽን ሲበረብር ምን አልኩሽ? ሸርሙጣ ብዬ ሰደብኩሽ? ነሽ ብዬም አላሰብኩ፡፡ እኛ ነን እንደልብ እንዲፈሱ ፈቅደንላቸው የሀገሪቱን አቅርቦተ ሴት ያናጋነው፡፡ አንዳንዴ ሴቶቻችን ስህተቶቻችን ናቸው፡፡ ራሳቸውን የስሜት ወደብ አድርገው እየገነቡ የማንም ዝቃጭ ስሜትና ስሜት ዶላር ማራገፊያ አድርገው እየገነቡ፡፡ አንቺዬ? ለመሆኑ ሽሮ ሲበላ በኖረ አንጀታችሁ እኚያን ነጫጭበች እንደምን ቻላችኋቸው? ለነገሩ፣ ነገሩን አልኩ እንጂ ነገሩን አጥቼው አይደለም፡፡

አይ ኢትዮጵያዬ! ከነጮቹ አንዱ ወደ ሀገሩ ሊወስድሽ ነው አሉኝ ደግሞ፡፡ ስደተኛ ልብ እንዳለሽ አውቃለሁ፡፡ አልፈርድብሽም፡፡ ምክንያቱም “ ኢትዮጵያ ታበፅህ እዴዊሃ ሀበ እግዚኣብሔር“ የሚለው፣ “ ኢትዮጵያ ታበፅህ እዴዊሃ ሀበ አሜሪካ ሆኖ“ የተወለደው ካንቺ መወለድ በፊት ነው፡፡
.
.
ቆይ ግን ምን አጎደልኩብሽ? ምን አሰኝቶሽ ምን አሳጣሁሽ? አልጋ ላይ ነብሴ ነህ ትይኝ አልነበር? ታዲያ ለምነው ጥለሽኝ የሄድሽው? ለምን ነው ጭንሸ የምንም ማሳለጫ የሆነው?

እውነት እውነት እልሻለሁ፣ አንቺ እና ሀገሬ አንድ ናችሁ፡፡ ሁለታችሁም ስማችሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከማይጠቅማቹህ ትዳራላቹህ፤ የራሳችሁን ጥላችሁ የሰው ታባራላችሁ፡፡ የማንነታችሁ ምንነት ጠፍቷችኋል፡፡ እጆቻችሁ ወደ አሜሪካ ተቀስረዋል፡፡ ሀዘናችሁን ውጣችሁ፣ በማስመሰል ፈገግታ ልትሸፍኑት ትሞክራላችሁ፡፡ ብዙ! በጣም ብዙ ነገር ያመሳስላችኋል፡፡

ግን ኢትዮጵያዬ! እንኳን ደስ አለሽ ልልሽ እወዳለሁ፡፡ ስንት ዓመት የቅልውጥና ፎርም( ዲቪ) ስትሞዪ ያልደረሰሽ፣ እድል በአንድ ነጭ ስለተሳካልሽ፡፡ እባክሽ የገንዘብ ባልሽንም አመስግኝልኝ ፤
1) በየዓመቱ ዲቪ ስትሞዪ፣ ተወድዶ የህትመት ዋጋውን ካናረው የወረቀት ብክነት ስለታደገን፡፡
2) በቃ አንደኛውን ምስጋና ደግመሽ አመስግኝልኝ፡፡

…. ግን እንዴት እንደናፈቅሽኝ ብታውቂ፡፡ የሌላ መመነት ሐጢያት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ከሆነም ለኔ ሳይሁን ለአሁንሽ ይመስለኛል፡፡ ግን እጮኛዋ የሞተባት ሴት በማግባቱ ኀጢያተኛ ላይባል ይችላል፡፡ ታውቂያለሽ ሞቻለሁ! ኢትዮጵያዬ ሙች ሞቻለሁ!! አንቺ እራስሽ ስታስቢው ኢትዮጵያ የምትባል `ሀገር` ጠፍታ ባንዲራዋ ምን ህልውና ይኖረዋል? እንደ ባንዲራዋ ነኝ፣ በሌለች በወደመች ሀገር ላይ የተሰቀልኩ፡፡ የተሰቀልኩት እራሱ እንደ ባንዲራ ሳይሆን እንደ ወንጀለኛ ነው፡፡

ግን ግን አደራሽን ባልሽን እንዳትተይው፡፡ መቼም ሀገሩ ሰዶምና ገሞራ ነው፡፡ እና … አደራሽን፣ `ሌዝቢያን` እንዳትሆኝበት፡፡ ያው ማለት የፈለኩት፣ ለማለት የፈለኩትን እምደሆነ ይገባሻል መቼም፡፡

ግን ኢትዮጵያዬ… ምን ባይደላሽ፣ ምን ባይመችሽ፣ የጠበቅሽው ደስታ ውጤቱ ሀዘን ቢሆን፣ ስጋሽ የስጋት ቤት ብትሆን… እኔ ዘላለም አፍቃሪሽን አስታውሺኝ፡፡ ሁሌም ስጠብቅሽ እኖራለሁ፡፡ በጠራሽኝ በማንኛውም ጊዜ አጠገብሽ እገኛለሁ፡፡ ያልኩሽ እንደሚሆን ደግሞ እርግጠኛ ነኝ!

-አፍቃሪሽ!!!!

2. ኢትዮጵያ ሁለት ( ለሀገሬ)

ስላንቺ በዚህች ገፅ ለመፃፍ መሞከሬአንቺን መድፈር እንደሆነ ባውቅም፤ ማንም ከደፈረሽ በላይ መድፈር እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ላንቺ ያለኝን ስሜት ስም መስጠት አቅቶኛል፡፡ ዜግነትሽን ቀይርሽ፣ ዜግነት ልታሳጭን ልታሳጭን እንደሆነ ባሰብኩ ጊዜ እፈራለሁ፡፡ ምለ ጊዜ ቀጥ ብሎ በቆመ፣ ለጥ ብሎ በተኛ እላለሁ( ይሄ ሲሆን ላለማየት)

እጅሽ ምዕራብ ድረስ በመዘርጋቱ፣ የጥቂቶቻችንን የልፋት ውጤት መቀበል አልቻለም፡፡ ቢደርስሽ እንኳ የሚወስዱት ሌሎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዬ! እንደ ፍቅሬ የምንም ነጫጭባ የወሸመሽ፡፡ ከራስሽ ወገኖች መሆን አልቻልሽም፡፡ ማንነትሽ ምዕራብ ምዕራብ ይገለማል፡፡ ለኛ ሲሆን ድንግል ትሆኛለሽ፣ ለነሱ ጊዜ ግን እልል ያልሽ አለሌ፡፡ እኛን ስታይ ለማኝ፣ ለነሱ ጊዜ ለጋስ ነሽ!!

ነዋሪዎችሽ የነወረ አኗኗር መኖር ከጀመሩ፣ መዓት `ነዋሪ አልባ ጊዜያት` አለፉ፡፡ አንቺም ነውራቸውን ደግፈሽ፣ በግሎባላይዜሽን ቢላ ታርደሽ፣ በራስሽ ደም ዘይትነት መጠበስ ለምን እንደመረጥሽ እንጃ!!

ሕዝቦችሽ አንችን አይተው ሀሞታቸው ፈሰሰ፡፡ ልባቸው ልብ አጣ፡፡ እጃቸው ለስራ ሳይሆን እርስ በእርስ ለመተናነቅ በጉጉት ተዘረጋ፡፡

Dv እና Dstv ልጆችሽን የነሳሽ እናቴ ሆይ! አሁን አሁንማ አንቺም እንደልጆችሽ ዲቪ ሞልተሸ የምትሄጅ እየመሰለኝ መሸበር ጀምሬያለሁ፡፡ ከዛ ዜግነቴ ምን ይሆናል? ማንነኝ እላለሁ? ምንስ እሆናለሁ?

ልጆችሽ ላይ ያጠላው ፍርሀት፣ የወረሳቸው ራስን ማጣት፣ ያማራቸው ስደት፣ እንዲነሳላቸው እና እንዲነሳልሽ ምኞቴ ነው፡፡ አንቺና ፍቅሬን በብር የሚሸጥ የሚለውጣችሁ፣ ዜግነት የሚሳጣችሁ፣ የወደዳችሁትን የሚያስተዋችሁ፣ ለባርነት የሚጋብዛችሁ፣ ተጠቅሞ የሚጥላችሁ ሰውና ግለሰብ የሚጠፋበት ጊዜ እስኪመጣ ሁለታችሁም ለኔ አአንድ አካል አንድ አምሳል ናችሁና አንድ ቻው፣ አንድ ስንብት እንካችሁ፡፡ ሁለታችሁንም አንድና ዘላለማዊ በሆነ ፍቅር አፈቅራችኋለሁ፡፤ በሕይወት ብትኖሩም ባትኖሩም የማይበሰብስ የመቃብር ሳጥናችሁ ሁሌም ከልቤ ይኖራል፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቃችሁ!!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...