Tidarfelagi.com

ያድዋ ስንኞች

የቅዱስ ቫላንታይንን በአል ምክንያት በማድረግ ስለ አድዋ ጦርነት እንጽፋለን፡፡

የቀድሞ ሰዎች የቃልና የዜማን ኃይል አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ሁሌም ወደ ጦርሜዳ ከመሄዳቸው በፊት አዝማሪ እና አረሆ ይመለምላሉ፡፡ ባድዋ ጦርነት ብዙ አዝማሪዎች ማሲንቆ ታጥቀው ዘምተዋል፡፡ አንዳንዶች ለውለታቸው ከድል በኋላ ማእረግና መታሰቢያ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከኒህ አዝማሪዎች መካከል ጣዲቄ የተባለችው ስመጥር ሴት፤ አዲሳባ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሠፈር በስሟ ተሰይሞላት ነበር፡፡ በኀይለሥላሴ ዘበን የቸርቺል ጎዳና ሲነጠፍ፣ በቦታው የነበረው የጣድቄ መታሰቢያ ሳይደመሰስ አልቀረም ፡፡ አሁን፤ “ ያዝማሪ አጣዲቄ ሉባንጃ ግባ የቸርቺል ትምባሆ ” ውጣ እላለሁ ፡፡ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ታትሞ በሚወጣው ”ከአሜን ባሻገር “በተባለው መጽሐፌ ጣዲቄን ከትቢያዋ ላስነሣት ሞክርያለሁ፡፡(ይቺ አረፍተነገር እንደ ማስታወቂያም እንደ ጉራም ትመዝገብልኝ)በጊዜው፤ከጠላት ጎን ተሰልፈው ተናዳፊ ግጥም ወደ ወገን ጦር የሚወረውሩ አዝማሪዎችም ኣልጠፉም፡፡ ለምሳሌ አንዱ የጀኔራል ባራቴሪ ኣዝማሪ የጣልያንን ሠራዊት ታላቅነት በማካበድ የሚከተለውን ተጎርሯል፡፡

ዥኔራል ባራተሪ
ዥኔራል ባራተሪ
ማን ይችልሃል ያለ ፈጣሪ
ባንዳው አዝማሪ እንደገመተው ሳይሆን ቀርቶ የጥልያን ጦር እንደማሽላ እንጀራ ተፍረከረከ፡፡ ኩሩው ጄኔራል ባራቴሪም ተማረከ፡፡ በምርኮው ማግስት ዳግማዊ ምኒልክ ድንኳን ተይዞ ቀርቦ ምን አባቱ አቅብጦት እንደተዋጋ ሲጠየቅ በቁጣ የተሞላ ምላሽ ሰጠ፤ ንጉሡም ” ቁጣ ትናንት የጦርነቱ ቀን ነበር እንጂ ዛሬ ምን ይረባል “ብለው ስቀው አሰናበቱት ፡፡
በድሉ ማግስት የዘመኑ ጥቁር ሆሜሮች የጦርነቱን ውሎ በቅኔ ዘግበውታል፡፡ አንዱ የሚከተለውን ብሏል፡፡

ሰላም ለአፉከ ለፈጣሪ ዘየአኩቶ
ዘኢይትናገር ስላቀ ወኢይነበብ ከንቶ
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ማህቶቶ
ኀልቀ ማንጀር ወስእነ ፍኖቶ
ዤኔራል ባራቴሪይ ሶበ ገባ ደንገጸ ኡምበርቶ

ትርጉሙ እንደሚከተለው ግድም ነው፡፡
ሰላም ላንደበትህ፤ ለሚያቀርብ ለእግዜር ምስጋና
ዘበት፤ ስላቅ ፤ ከንቱ ወሬ፤ መናገርን መች ያውቅና
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፤ የኢትዮጵያ መብራት ፋና
ተጨነቀ ማጆር፤ እግሩ ዛለ በጎዳና
ደነገጠ ኡምበርቶ፤ በባራቴሪ ምርኮ ዜና ፡፡

ቅኔይቱ ከወገቧ በላይ ውዳሴ ከወገቧ በታች ዜና እወጃ ናት፡፡ በቅኔይቱ ማጆር ተብሎ የተጠቀሰው አምባላጌ ላይ ወድቆ የተሰለበው ማጆር ቶሌዚ ሲሆን ”ደነገጠ “የተባለው ኡመበርቶ የጣልያኑ ንጉሥ ነው፡፡ ባለቅኔው ስለ ጣልያን ሁኔታ ነቄ ነበር ማለት ይቻላል፡
“ያድዋ ድል የብሄርብሄረሰቦች ድል ነው” ይላል የሰባተኛ ክፍል ይሁን የስምንተኛ ክፍል የሲቪክስ ማስተማርያ መጽሐፍ፡፡ እውነት ነው! ያም ሆኖ፤ብሄርብሄረሰቦችን ባንድ ወታደራዊ ሥርዓት ጠምዶ ወደ ድል የመራቸው ዋናው የጦር አዝማች ምኒልክ ነበር፡፡በጊዜው ለዋናው የጦር አዝማች የውዳሴ ግጥሞች ጎርፈዋል፡፡ አንድ የሸዋ ኦሮሞ አዝማሪም እንዲህ ብሎ እንደ ዘፈነ ተመዝግቧል፡፡

Mootin baar gamaa ce’ee
Daanyoo faranji reebe.

አዛማጅ ትርጉም በስለሺ፤
ንጉሥ ወንዙን ተሻገረው
ዳኘው ፈረጅኑን ወገረው፡፡

ባድዋ ጦርነት ብዙ የወገን ወታደር አልቆ ሜዳ ላይ ቀርቷል ፡፡ ይህን በትካዜ ያስተዋለ አዝማሪ፤
የዳኘው ኣሽከሮች ፤እነሞት አይፈሬ
ርግፍ ርግፍ አሉ፤ እንደ ሾላ ፍሬ
ብሎ አንጎራጉሯል፡፡

እንደ ሾላ ፍሬ ቀይ ለብሰው ፤ከረገፉት አንዱ ኣሠላፊ ገበየሁ የተባለ ወታደር ነበር፡፡ (ቸሩሊና ዴልቦካ የተባሉ የታሪክ ጸሀፊዎች አሠላፊ ገበየሁን ከስመጥሩ ፊታውራሪ ገበየሁ ጋር እያምታቱ ጽፈዋል፡፡ ቼሩሊ፤“ አሠላፊ ”የተባለውን ማእረግ “አሳላፊ” ብሎ በመረዳት ፊታውራሪ ገበየሁ የንጉሡ አሳላፊ (cup-bearer ) ነበር በማለት ስቷል ፡፡ በአድዋ ጦርነት ሁለት የተለያዩ ገበየሁዎች እንደነበሩ የምንገነዘበው በጸሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ የተመዘገበውን የጦር አለቆች ኣሰላለፍ ስናይ ነው ፡፡ ) ለማንኛውም አሠላፊ ገበየሁ በጦር ሜዳ ከወደቀ በኋላ ያልታወቀ አዝማሪ ያንጎራጎረለት አንጀት የሚበላ ግጥም Folk-literature of the Oromo .. በተባለው መዝገብ ተካቷል፡፡ ታድያ፤ እኔ እንጉርጉሮውን መነሻ አድርጌ የራሴን ግጥም ብጽፍ ማን ይከለክለኛል?

አሠላፊ ገበዮ!
እንደ እግዜር ስጋጃ ፤ምድሩ ላይ ተሰፍተህ
እንደ ብረት ቁና አፈር ላይ ተደፍተህ
“ጓዶች ወዴት አሉ?” ብለህ ስትጣራ
ጓዶች ተመለሱ ከንጉሡ ጋራ
“ሚስቴ ወዴት አለች ?”
ብለህ ስትጣራ
ሚስትህ ወዲያ ቀረች
በሞትህ በማግስቱ ለሌላ ተዳረች
ይልቅ “እናቴ ሆይ !” በማለት ተጣራ
የናት ኀዘን ዶፍ ነው፤ ቶሎም አያባራ፡፡

ይችን ወግ ለመጻፍ መነሻ የሆኑኝ መጻሕፍት ከታች ቀርበዋል፡፡

  • ተክለጻድቅ መኩሪያ (አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት)ሜክስኮ ቡክ ኮርነር
  • Enrico Cerulli, Folk-literature of the Oromo of Southern Abyssinia
  • Del Boca, Angelo. Gli Italiani in Africa Orientale La caduta dell’Impero Editori Laterza, 1982.
Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...