Tidarfelagi.com

በዘመን ሂደት ያልተፈታ ችግር

“በዘመን ሂደት ያልተፈታ ችግር፤ በዘመን ሂደት የችግር ካንሠር ይሆናል።”

ለአንዲት ሐገር ዘመንን የሚዋጅ፣ ትውልድን አንደአዲስ የሚቀርፅ ጥበብ ያስፈልጋታል። ሐገርን ወደኋላ የሚጎትት የማይጠቅም አስተሳሰብ በአዲስና በተሻለ አስተሳሰብ መለወጥ ከዜጎች የሚጠበቅ ተግባር ነው። ያረጀውን ማደስ፣ የሌለውን ጥበብ መፍጠር፣ ያልነበረውን መልካም ተሞክሮ መቅሰም ከተማረ ትውልድ የሚጠበቅ ልዩ ተግባር ነው። በዘመን ሂደት፣ በትውልድ ቅብብል የማይጠቅምን ፖለቲካ ማራመድ ለፖለቲከኛውም፣ ለሕዝቡም ለሐገሪቷም የሚያመጣው በጎ ነገር የለውም። ከዛ ይልቅ የማይድን ቁስል ሆኖ ሁሌ በበሽታው የሚያሰቃይ ገዳይ በሽታ ይሆናል። አንድ ከማድረግ ይልቅ የሚነጣጥል፤ መሰብሰብን ትቶ የሚበትን፣ ከማዋሃድ ይልቅ የሚለያይ ርዕዮት ዓለም ማራመድ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። ሐገርን ሊገነባ፣ ትውልድ ከፍ ከፍ ሊያደርግ የሚችል ጥበብ ለሐገራችን ያስፈልጋታል። ይሄን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ለዚህ የሚመጥን ጭንቅላት መፍጠር ግድ ይለናል። አስተዋይ ጭንቅላት አንድም ከመጽሐፍ ማሕፀን በንባብ ምጥ የሚወለድ፤ አንድም ትናንትን በማስተዋልና የኋላ ታሪክን ተጠቅሞ በበጎ እሳቤ በመለወጥ እውን የሚሆን ነው።

አንድ ያልታወቀ ፀሐፊ፡-

‹‹በዘመን ሂደት ያልተፈታ ችግር፤ በዘመን ሂደት የችግር ካንሠር ይሆናል።›› ይለናል።

አዎ! አንዳንድ ቁስልን ገና በእንጭጭነቱ ማከም እየተቻለ ውሎ ያድርና ቁስሉ አመርቅዞ ወደካንሰር ይለወጣል። ወደካንሰር ያደገን ቁስል ማዳን አይቻልም። ዳፋው ሁልጊዜም በቁስሉ ህመም ሲሰቃዩ መኖር ብቻ ነው። ማስታገሻ እንጂ መፈወሻ መድሐኒት የለውም። ሕመምን በቶሎ ማከም መቻል ከብልህ ሰው የሚጠበቅ አዋቂነት ነው። ቢቻል ሕመሙ እንዳይከሰት ቀድሞ መጠንቀቅ ነው። ጥንቁቅነት ከልባሞች የሚመነጭ ቅድመ መከላከያ ነው። ጥንቁቅነት ፍራቻ አለመሆኑን የሚረዱት አስተዋዮች ብቻ ናቸው።

የሐገራችንም ችግር እየተመላለሰ የሚደቁሰንና አዙሪት ሆኖብን ወደፊት አላንቀሳቅስ ያለን ችግራችንን ተነጋግረንና ተወያይተን ፍቱን የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥ አለመቻላችን ነው። አጀንዳችን መጋጨት እንጂ መግባባት አይደለም። አጀንዳችንን እንዲያስማማንና ሁላችንን እንዲጠቅም አድርገን ስላልቀረጽን ዘወትር እርስበርስ እንጠፋፋለን። ፖለቲካችን፣ ሕገመንግስታችን፣ ፖሊሲያችን፣ ሕጎቻችን፣ ደንቦቻችን በደንብ ያልተፍታቱና ሁሉን አካታች ባለመሆናቸው የችግሮቻችን ምንጭ ይሆናሉ። ፖለቲካውን የሚዘውሩት ፖለቲከኞችም፣ ሕጉን የሚተረጉሙት ተርጓሚዎችም፣ ደንብና መመሪያውን የሚያስፈፅሙት ባለስልጣኖቻችንም በአድልኦ አስተሳሰብ፣ ለአንድ ወገን ብቻ በመወገን ያዛቡታል።

ፍትህ ሲጎድል፣ አድልኦ ጣራ ሲደርስ ተደሳችና ተከፊ፣ ተጠቃሚና ተጎጂ፣ ቀን የሚወጣለትና ቀን የሚመሽበትን የህብረተሰብ ጎራ ይፈጥራል። ይሄም የተረኝነት ፖለቲካ ስር እንዲይዝ ያደርጋል። ተረኝነት እኔ ብቻ ልጠቀም ባይነት ነው። ወረፋው ደርሶኛልና እኔ ደግሞ ልብላ የሚል የራስወዳድ ፖለቲካ ነው። ለሁላችንም የሚሆን፣ እኩልነት የሰፈነበት፣ ከአድሎ ነፃ የሆነ አገልግሎት የምንሰጥበትና የምናገኝበትን ሥርዓትና ባሕርይ ማምጣት አልቻልንም። ሞራላችንን በእውነትና በፍትህ ንፁህ መስመር አልገነባንም። ብዙዎቻችን ሃይማኖታችንም ይሁን ዕውቀታችን የለብለብ በመሆኑ ወደትክክለኛው መንገድ አልመራንም። በዚህም ምክንያት ራሳችን በፈጠርነው ችግር እንደቆሳለን። እኛው ባመጣነው በሽታ እንታመማለን። ተንጋለን እየተፋን በራሳችን ላይ እንከፋለን። እርስበርስ ተጠላልተን እንገፈታተራለን። ላለመስማማት እንኳን አንስማማም። ልዩነቶቻችንን ለማክበር ሕሊና አልፈጠርንም። ብዝሃ ሃሳብን የሚያስተናግድ ልቦና አልገነባንም። ምን ይሻለን ይሆን….???

እርካብና መንበር የተባለው መፅሐፍ በመግቢያው ላይ ታሪካችን የድንቁርናችንና የኋላቀርነታችን ምንጭ መሆኑን እንዲህ ሲል ይናገራል፡-

‹‹ሐገሪቱ አሁን የምትገኝበት ድንቁርና እና ችጋር፤ ሠላም ማጣትና ኋላቀርነት ምክንያቶች ሁሉ የሚቀዱት ከእርሱ “ታሪክ” ከሚባለው ጥልቅ የትላንት ባሕር ውስጥ እንጂ ከሌላ ከየትም ሊሆን አይችልም። ከዚያው ነው በረከታችን ከመሆን ይልቅ መርገምት ሆኖ ከተጣባን ዕድሜ ጠገቡ የመከራችን ኩሬ በአንድ ቃልም “ከታሪካችን” ተብሎ ይጠቃለላል።›› ይለናል።

እውነት ነው! ተጨባጭ ሃቁ ይሄን ያሳያል። ለሠለጠነ ማሕበረሰብ ታሪክ አስታራቂ እንጂ አጋዳይ አይደለም። የታሪክ አጠቃቀማችን ጥበብ የተሞላው ባለመሆኑ እንድንጠላላ ገፊ ምክንያት ሆኗል። ታሪካችን እያጋጨን እዚህ አድርሶናል። ከታሪካችን መማር ያልቻልን በመሆናችን ታሪካችን ራሱን ይደጋግማል። የአርባዓመቱ ታሪክ ምኑም ምኑም ሳይለወጥ ዛሬም ላይ ተመልሶ እውን ሆኗል። ትናንት የተጣላንበትን ዛሬም ደግመን እየተጣላንበት ነው። ትናንት የተገዳደልንበትን ዛሬም እየተፋጀንበት ነው። ቢያንስ ከኪሳራችን እንኳን ትምህርት መውሰድ አልቻልንም። እኛን በመከፋፈል አጀንዳ እየቀረፁ የሚያጫርሱን የውጪ ሃይሎችም ቢሆኑም እንኳን እንደህፃን ልጅ በቀላሉ እያታለሉን ነው። Easy come! Easy go! ሆነን አረፍነው ጎበዝ።

ቻንቴሌ ሬኔ የተባለ ሰው እንዲህ ይላል፡-

‹‹ሁላችንም እዚህ ያለነው አዲስ ታሪክ ልንሠራ እንጂ ታሪክ ልንደግም አይደለም።›› ይለናል።

ሐቅ ነው! ጎበዝ… ታሪክህን ተማርበት እንጂ የጠብ ምንጭ አታድርገው። ብልህ ሰው ከታሪክ ተምሮ አዲስ ታሪክ ይሠራል። ሠነፍ ሰው ግን የተሠራውን ታሪክ ጥላሸት እየቀባ፤ መጥፎውን ታሪክ እየደጋገመ ራሱንም ሐገሩንም ያደክማል። ከታሪክህ መልካም መልካሙን ዝገን የዕለቱ መልዕክት ነው።

‹‹ታሪክህ ታሪኬ የሚያጋድለን ምነው?

ከቶ ለምንድነው?

ከትናንቱ ውድቀት መማሩን ያልቻልነው?

ይሄ ሁሉ የሆነው…

ታሪክ መድገም እንጂ!

አዲስ ታሪክ መስራት አቅም ብናጣ ነው!!››

ቸር አዲስ ታሪክ!

________________________

እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)

ሐሙስ ግንቦት ፳፱ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...