Tidarfelagi.com

የ‹‹ፌዴራሊስቶቹ›› ኅፀፅ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰርክ የምትታይ፣ ከዚህ ቀደም ደግሞ እንዲሁ ችግር ሲፈጠር ተደጋግማ ብቅ የምትል ቅጥፈት/ዝንፈት አለች። እሷም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችን ‹‹ፌዴራሊስት››ና ‹‹አሀዳዊያን›› አድርጎ የመክፈል ሙከራ ናት። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ‹‹ፌዴራሊስት›› ነኝ ማለት የተራማጅነትና የሞራል ልዕልና መገለጫ ተደርጎም ይቀርባል። እነዚህን ሁለት ጉዳዮች አፍታተን እንያቸው።

ፌዴራሊስትና አሀዳዊያን፡- ሀሳዊ ምደባ

ምናልባትም ‹‹ፌዴራሊስት ነን›› የሚሉ ሰዎች ቃሉን የኮረጁት ከአሜሪካው የሕገ-መንግሥት ዕድገት ውዝግብ ሊሆን ይችላል። ያኔ ክርክሩ የነበረው ልል የሆነውን የኮንፌዴራል ግንኙነት እንዲቀጥል በሚፈልጉና(ፀረ-ፌዴራሊስት ሊባሉ ይችላሉ) ግንኙነቱ የበለጠ የተዋሀደ የፌዴራል መንግሥት እንዲፈጠር በሚሹ ፌዴራሊስቶች መካከል ነው። በእኛ አገር አለ የሚባለው ልዩነት በተቃራኒው የፌዴራል ሥርዓት ያስፈልጋልና አሀዳዊ ሥርዓት ይመስረት የሚል ተደርጎ ነው የሚቀርበው። በእርግጥ ይሄ ክፍፍል መሬት ላይ የማናገኘው ‹ምናባዊ› የተንኮል ፈጠራ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አገር እንመሠርታለን (ፌዴራሊዝም ከመገንጠል በመለስ ያለ መፍትሔ በመሆኑ ‹‹እገነጠላለሁ›› እያሉ ፌዴራሊስት መሆን አይቻልም) ከሚሉ ጥቂት የተወሰነ ድጋፍ ያላቸው ከሚመስሉ ፓርቲዎች ውጭ ፌዴራሊዝምን የማይቀበል በቁምነገር የሚወስድ የፖለቲካ ማኅበር የለም።

በተለምዶ የአንድነት ሃይል ተብለው የሚታወቁት እንደ ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ ግንቦት ሰባት፣ ኢዜማ… የመሰሉ ፓርቲዎች ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ለማደራጀት የተሻለው አማራጭ ነው ብለው በይፋ የተቀበሉ ናቸው። በተለይ የሽግግሩ ዘመን አቧራ ከሰከነ በኋላ ፌዴራሊዝም ከሞላ ጎደል የፖለቲካ ልሂቃን የሚስማሙበት ሀሳብ እየሆነ መጥቷል። ለፌዴራሊዝሙ ያላቸው ድጋፍ ለይስሙላ ነው የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል። ይህን መሰሉ ትችት ዋነኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በፕሮግራማቸው የጻፉትን በቃለ-መጠየቆቻቸው የሚሰጡትን ሀሳብ ውሸት ነው ከማለትና ሊሆን የሚፈልጉትን የራስን እውነት ከመፍጠር አይተናነስም።

ይህ ማለት ግን ሁሉም የፖለቲካ ማኅበር አሁን ያለውን ዘውጌ ተኮር የፌዴራል መዋቅር ይቀበላል ማለት አይደለም። አሁን ያለውን ሥርዓት አምርረው በመተቸት የሚታውቁ ፌዴራሊስቶች አሉ። እንደውም ይህ የፌዴራል መዋቅር ቁልፍ የውዝግብ ማዕከል መሆኑ እሙን ነው። ትክክለኛው ክፍፍል ያለው ፌዴራሊዝሙ እንዳለ ይቀጥል በሚሉ (ሃያ ሰባት ወርቃማ የፌዴራል ዘመናት አሳልፈናል የሚሉና ስላልተገበረ እንጅ በትክክል ቢተገበር ፌዴራሊዝሙ ወርቅ ነው የሚሉ ሁለት ክፍሎች አሉበት)ና ፌዴራሊዝሙ መሻሻል አለበት በሚሉ ኃይሎች መካከል ነው። ውዝግቡን በኅብረ-ብሔራዊና መልካዓምድራዊ ፌዴራሊዝም መካከል ነው ብሎ መመንጸርም(ፍሬም ማድረግ) ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ስለዚህ ‹‹ፌዴራሊስትነት›› ለሁሉም የሚገባ ማዕረግ እንጅ አንዳንድ ፌዴራሊስቶች ስተው ወይም ቀጥፈው እንደሚያቀርቡት ለእነሱ ብቻ የተገባ መጠሪያ ሊሆን አይችልም። ፌዴራሊዝም ምን ይሁን ምን የማያውቀው መንገደኛም ‹‹ይሄ ፌዴራሊዝም›› እያለ ሲያለቃቅስ ብትሰሙት እየወቀሰ ያለው ባለፉት ዓመታት በዘውጌ ማህበረሰቦች መካከል የዳበረው መጠራጠርና ግጭትን እንጅ፤ ‹‹አሃዳዊነት››ን እየሰበከ የማይሆንበት ዕድል ከሚሆንበት ይበልጣል።

ለመሆኑ አሀዳዊ መሆን ሀጢያቱ ምንድን ነው?

የፌዴራሊስትነት ማዕረግ የኛ ብቻ ናት ከሚሉት አንዳንዶቹ ያንን ሲሉ አሀዳዊ የመንግሥት ሥርዓት መደገፍን የዘውጌ ማንነቶች መድፈቅን ከመደገፍ የሚያምታቱ፤ ከተራማጅነት መጉደል አድርገው የሚያቀርቡ ናቸው። እውነታው ግን ይሄ አይደለም። የፌዴራል ሥርዓትን ከአሀዳዊ መንግሥት መምረጥ በመሠረቱ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓትን ከፓርላሜንታዊ ሥርዓት ከመመርጥ የተለየ አይደለም። (የ4ኛ ክፍል የሥነ-ዜጋ መጽሐፍን ይመልከቱ) ሁለቱም ሥርዓቶች በዓይነተ-ብዙ መልኩ ሊተገበሩ የመቻላቸውን ያህል የራሳቸው የሆነ በድክመትም ሆነ በበጎ በኩል የሚጠቀስ ባህርይ አላቸው። በስፋት እንደሚነዛው አሀዳዊ አስተዳደር የባህልና የቋንቋ መብቶችን የሚደፈጥጥና በጥብቅ የተማከለ ተደርጎ የሚቀርበው በአንድ በኩል፤ ፌዴራል ሥርዓትም በአንጻራዊነት የተማከለ ሊሆን አይችልም የዘውጌ-ባህላዊ ፍትህን ያሰፍናል ብሎ በጅምላ ግምት መውሰድ በሌላ በኩል መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የሚጋጭ ነው።

በዚህ ረገድ የፌዴራል ሥርዓት ከአሀዳዊ መንግሥት የሚለየው ዋናው ነጥብ ለክልል መንግሥታት በሚሰጠው የሥልጣን መጠንና ሥፋት ሳይሆን ለክልሎች የሚሰጠው ሥልጣን አስተዳደር በሄደና በመጣ ቁጥር በማይቀይረው መልኩ ክልሎችንም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱን በሚገዛ ሕገ-መንግሥት የሚቀመጥ በመሆኑና ይህንንም ሕገ-መንግሥት የማሻሻል ሂደት ከሞላ ጎደል በጋራው መንግሥት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑ ነው። የፌዴራል አወቃቀር ለክልል መንግሥታት በሚሰጠው ሥልጣን ንፉግና የጋራውን መንግሥትን አፍርጥሞ ሊያዋቅር የሚችልበት ዕድል አለ። የሕንዱን ፌዴራል ሥርዓት በዚህ የሚያሙት ምሑራን አሉ።

የአሐዳዊ መንግሥት ምሣሌና ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው የፈረንሳይ መንግሥት ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሥልጣንን ለአውራጃ መንግሥታት(ሎካል ጋቨርመንትስ) የሰጠና የሚታወቅበት ማዕከላዊ የተዋሀደ መንግሥትም የተዳከመ ሆኗል። እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ መንግሥታትም ለተወሰኑ ክፍሎቻቸው ምናልባትም አንዳንድ ፌዴራል ሕገ-መንግሥቶች ከሚሰጡት ላቅ ያለ ሥልጣን የሰጡ ቢሆንም በመሰረቱ የመንግሥት መዋቅራቸው አሐዳዊ ነው።(የሁለቱን ሥርዓቶች በተለያየ መልኩ አዳቅለው የሚጠቀሙ ሥርዓቶች በተግባር እየተፈጠሩ ሲሄዱ በሁለቱ መካከል ሁሉም የሚስማማበት መሥመር ማበጀት እያሰቸገረ እየመጣ ነው።)

የዘውጌ ብዝሐነትን ከማስተናገድ ጋር በተያያዘም ቢሆን ፌዴራል መሆን ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ አድርጎ መውሰድ ተገቢ አይደለም፤ ፌዴራል አለመሆንም ከዚሁ የሚጣራስ አድርጎ መወሰድ እንዲሁ። እንደሚታወቀው ፌዴራሊዝም ከዘፍጥረቱ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዘውጌያዊ ብዝሐነትን የማስተናገድ ዓላማ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ሥርዓት አልነበረም። ፌዴራሊዝም በተቃራኒው ብዝሀነትን ለማክሰምና አቅልጦ የማጥፋት(አሲሚሌሽን) መሣሪያ ሆኗል፣ ሊሆንም ይችላል።

በሌላ በኩል አሐዳዊና በጥብቅ የተማከሉ የነበሩ የኢትዮጵያ ሥርዓቶች ዘውጌያዊ ብዝሐነትን በማስተናገድ ረገድ መውደቃቸው በብዙ አገራት ተመራጭ የሆነውን አሐዳዊ የመንግሥት ሥርዓትን ያለ ግብሩ ሊያስወነጅለው አይገባም። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ፌዴራል ነኝ በምትለው ኢትዮጵያ የተፈጸሙ ሀጢያቶች መነሻው ‹‹ፌዴራሊዝሙ›› ነው ብሎ በሰፊ ብሩሽ መለደፍ ተገቢ አይደለም ብሎ የሚከራከር ሰው የመንግሥቱ ኃይለማርያምና የንጉሡ መንግሥታት ሀጢያት ሁሉ ምንጭ ፌዴራል ሥርዓትን አለመቀበላቸው ነው ብሎ ሊከራከር አይችልም። ለምሣሌ ኢትዮጵያ አሀዳዊ መንግሥት መሆኗን የሚያውጀው የደርግ ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያ ብሔረ-ብዙ ሀገረ-መንግሥት ሆና መቆየቷን፣ ስለ ብሔረሰቦች እኩልነትም በመግቢያው ያስቀመጣል። በዝርዝር አንቀጾችም የብሔረሰቦች እኩልነት፣ የቋንቋቸው መከበርና የተወሰነ የራስ-ገዝነትም በግልጽ ይፈቅዳል።

ለማጠቃለል ፌዴራሊስትና አሐዳዊ የሚለው ክፍፍል አሐዳዊ የሚለው ቃል ባልተገባ መልኩ መቆሸሹን መሠረት በማድረግ ሆን ተብሎ አሁን ባለው የፌዴራል ሥርዓት ላይ ውኃ የሚያነሳ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎችን ለማሸማቀቅ (አንዳንዴም በመሳት) ሲቀርብ በብዛት ይሰተዋላል። የፌዴራል ሥርዓት ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ አገር ለማስተዳደር፣ ብዝሐነትንም ለማስተናገድ የተሻለ ነው ከሚሉት ሰዎች አንዱ በመሆኔ አሁን ባለው የፌዴራል ሥርዓት የማነሳቸው ጥያቄዎች ሳያዳናቅፉኝ ፌዴራሊስትነት ይመለከተኛል። ፌዴራሊስት ነኝ ማለት ግን ተራማጅነትንና ከፍ ያለ የሞራል ባለቤትን አያስገኝልኝም። ከአሐዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ይልቅ ለኢትዮጵያ የሆነ ዓይነት ፌዴራል ሥርዓት ይሻላታል ብዬ አምናለሁ ማለት ብቻ ነው። ከፓርላሜንታዊ ይልቅ ፕሬዝዳንታዊ፤ ከአብላጫ የምርጫ ሥርዓት ይልቅ ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ይሻላል እንደማለት ዓይነት ነገር።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...