Tidarfelagi.com

የጦርነት ነገር…

የጦርነት ነገር…
(አ.አ)

ስሜ ሲያጥር፣ የግለሰብ ሳይሆን የከተማ፣ሊያውም የመዲና ስም እንደሚሆን ካወኩ ሰንብቻለሁ። ይብላኝ እንደ «ብስራት ዳኛቸው» ዐይነት ስም ላላቸው።ምን ብለው ሊያሳጥሩት ነው ሃሃ ይሄ ስም ቢኖረኝ፣ ስሜን ከማሳጥር ቁመቴ ቢያጥር የምመርጥ ይመስለኛል

ድህነትን በቀኝ፣ ፀረ ሰላም ሃይሎችን በግራ እየተዋጋችሁ ያላችሁ የቅድስቲቱ ሀገር ልጆች እንዴት አረፈዳችሁ። የዛሬ ርዕሳችን ደስ አይልም። ስለ ጦርነት ነው።ጦርነት ምኑ ደስ ይላል? እንደ ኒቼ ያለው ሾጤ ፈላስፋ ግን ጦርነትን ያፈቅራል። ጦርነትዬ እንዳለ፣ ወታደር መሆን እንደተመኘ ሳይሳካለት አብዶ ሞተ። እኔ ቀድሞም እብድ ነበር እላለሁ (ከነ ምርጥ አእምሮው)

እጅግ ከሚገርመኝ ታሪክ ልጀምር።
አፄ ቴዎድሮስ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት፣ በእሱና በደጃች ብሩ መካከል ጦርነት ሆነ።በጦር ሜዳው መሃል ይሄ ተፈፀመ። የቴዎድሮስ እና የብሩ ወታደር ጎን ለጎን ወድቀዋል።የቴዎድሮስ የሆነው ይሄን ጠየቀ፣ «አንተ የማነህ? »
«የደጃች ጎሹ ነኝ» አለ ሌላኛው።
የቴዎድሮስ፣ «እንግዲያስ ማንን እፈልጋለሁ» ብሎ እየተጎተተ ቀርቦ አፍንጫውን ቀጥቅጦ ገደለው።
ኢማጅን የኢትዮጵያ ሕዝብ (ሃሃሃ) እኚህ ሁለት ሰዎች አይተዋወቁም።በሌላ አጋጣሚ ቢገናኙ ምን አልባት ምርጥ የህይወት ዘመን ወዳጆች ይሆኑ ይሆናል? እስቲ ስለሟቹ እናስብ? ሟቹ ሚስት ነበረው? ማታ ይመጣል ብሎ፣ እቅፉን የሚናፍቅ የአራት ዓመት ልጅ ይኖረው ይሆን? ሞቱን ስትሰማ ሚስቱ ምን ብላ አለቀሰች? እናቱስ? አባቱ የልጃቸው አሟሟት ሲሰሙ ምን አሉ? ሌላም፣ ሌላም…

እሱስ ስሙ እንኳን ላልተጠራበት የሁለት ሰዎች ጠብ መሰዋቱ ተገቢ ነበር? ገዳዩ ከገደለው በኋላ ምን ተሰማው? ፣ ይሄ «ጀግንነቱ» ስሙን እንኳን አስመዝግቦ ላያስቀርለት፣ድርጊቱ ማንን ፈየደ?

ሰብዐዊነት የሚረክስበት ሰፊ ሜዳ ነው ጦር ሜዳ። ለነኒቼ ወታደር መሆን ትልቁ ፕሮፌሽን ቢሆንም፣ትልቁ ሰዋዊ ስህተት መሆኑ ይሰማኛል። አልበርት አንስታየን፣ ስራዎቹ «The world as i see it» ተብለው በተሰበሰቡበት መፅሐፍ ላይ፣ስለ ወታደር እንዲህ ፅፎ ነበር፤
«He has only been given his big brain by mistake; a backbone was all needed» ሃሃሃ ብሎ መሳቅ ይቻላል።

ጦረኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ተመልከት፣ ሕወሓት እንኳን በአስራ ሰባት ዓመት ትግሏ 54,000 ሕዝብ ነው ያስጨረሰችው። አስበው። አምሳ አራት ሺ! ችግሩ ይሄ ሁላ ሕዝብ አልቆም ድሉ አልተገኘም። በነዚህ ሰዎች ደም፣ ከተነሳችበት ዓላማ ግቡን አልመታም።እንዲህ ዜሮ ውጤት ላለው ነገር ሰው ለምን ይዋጋል?

በቀንድ ከብቶች ዓለም፣ መዋጋት ሁለት እንስሳት ፊት ለፊት ሆነው የሚያደርጉት በግንባር መላተም ነው።as simple as that! በአዕምሯዊያኑ ዓለም ግን፣ መዋጋት በሰይፍ መሞሻለቅ ነው። በመደፍ መተላለቅ ነው። በጅምላ ጭራሽ መሰሪያ መጠፋፋት ነው።የመሳሪያ እና የጣር ድምፅ ቅልቅል ነው።ታዲዮስ ታንቱ ስለ አርበኞች ሲፅፍ፣ «ቡም…ቡም…ድም…ድም…» አድርጎ እንደሚያልፈው ቀላል ተግባር አይደለም። ከዛ ደግሞ፣ ከእንስሳት ሁሉ ውብ ተደርገን መፈጠራችን ይሰማናል። George Carlin «These are z creatures we feel superior to» ብሎ ጨርሶታል።

ጦርነት የሰው ልጅ የውርደት ክታብ ነው።ይህ ቆሻሻ ታሪኩን፣ታሪክ ፀሐፊዎች አስውበው ይፅፉታል።ገጣሚያን ስሜት በተሞሉ ቃላት ያኮፍሱታል።

ታሪካችን ሙሉ ጦርነት ነው። እንደ አፄ ልብን ድንግል ዐይነቱ ጦርነት ጠፋ ብሎ አምላኩን «ጦር አውርድ» እያለ ሲፈታተን ቆየ አሉን።ወደ ሰማይ ጦር እየወረወረ የኦሮሞችን አምላክ ለመነ ብለው ተረኩልን። ግራኝን አዘዘበት፣ የአስራ አምስት ዓመት እልቂት!! (የጦር አውርዱን ትረካ በግሌ እንደ አፈ ታሪክ ነው የማየው)
የድሮ ሰዎቻችን በምንድነው ያልተጣሉት? በስልጣን፣ በቂም፣ በመሬት፣በሃብት፣ በሴት ተጣልተዋል፤ተዋግተዋል። «የድሮ ሰዎች በጡት መጠን፣በባሪያ ሽሚያ፣በከብት ብዛት፣በጭኮና በጫማ ሲጣሉ ኖሩ እንጂ ዲሞክራሲ ሊያበጁ አልተጣሉም»ይላል አዳም ረታ። ለዲሞክራሲም ቢሆን መጣላት አያስፈልግም።ከጥል ቂም እንጂ ዲሞክራሲ አይወለድም!

ወንድም ከወንድሙ፣አባት ከልጁ፣የባል ወገን ከሚስቱ ጎራ ለይተው ተከታክተዋል።ሀገሪቱም አንጋፋ war zone ሆና አለች። ይሄው ሱስ ሆኖብን፣ ዛሬ ራሱ ከድህነት ጋር እየተዋጋን ነው ይሉናል።ቃሉ፣ብልፅግና መፍጠርን ሳይሆን ከድህነትን ጋር ሲጠዛጠዙ መቆየትን ነው የሚሰብከው።

የአውሮራው መፅሐፍ ገፀባህሪ ሃይላይ፣ «የሰላሳ ዓመት ጦርነት፣ የሰላሳ ዓመት ድህነት ነው» ይላል። እኛ ስንት ዓመት ተዋጋን፣የስንት ዓመት ድህነት አለብን…

በህግ መግደል ወንጀል ነው።በሃይማኖት ኃጢያት ነው። በጦር ሜዳ ጀግንነት ነው።ብዙ የገደለ፣ብዙ ይጀግናል።ጥቂት ምክንያት እላዩ ላይ ጣል ይደረግበታል… ነፃነት፣የሀገር ፍቅር፣ ባንዲራ…ወዘተ ከዛ መሳሪያ ትሰጠዋለህ።ቀጥሎ ሬሳ መቁጠር ነው።ማስጠላቱን በውብ የጀግንነት ግጥም ትሸፍነዋለህ፣ በሀገር ፍቅር ስሜት ትጋረደዋለሁ። ሰብዓዊ ውርደት ብሔራዊ ኩራት ይሆናል።

አዎ እንስሳት ይጨካከናሉ። ህይወታቸውን የማስቀጠል ጥያቄ ሲመጣ እርስ በእርስ ይበላላሉ። ሰውም ያን ያደርጋል።በሚኒሊክ ዘመን፣ አንዷ የጎረቤቶቿን ሰባት ልጆች በልታለች። ሌሎች እንስሳት ሰፊ የእርስ በእርስ መጨራረስ እንደ ሰው ተግተው አይፈፅሙም።ሀገራት ለትምህርት እና ለጤና ከሚመድቡት በላይ ለጦር ሃይላቸው ብዙ ይበጅታሉ።ለበላይነት ይጨራረሳሉ።ጠብ አጫሪዎቹ ይፈጡርታል፣ጠብ የማይልላቸው ገብተው ይፋጁታል!

ተዋጊዎቹን ወጥቶ አደር ይሏቸዋል። ካም ኦን፣ የውትድርና ስራ ወጥቶ ማደር አይደለም። እንደዛ ቢሆንማ፣ ይሄን ፅሁፍ እንደጨረስኩ ነው ሄጄ ውትድርና የምመዘገበው። በእውነቱ፣ ወጥቶ አደር የሚለው ቃል፣ ከስራው ይልቅ «ዱር ውዬ»ለሚለው ቃል ይቀርባል። በቀጥታ ጥሩት፣ የምን ማድበስበስ ነው። ወታደር ወጥቶ አደር አይደለም፤ገድሎ አደር ነው።ሊሞት አይደለም የሚገባው። ሊገድል ነው። ለሀገሩ ሊገድልላት ነው።ለጌታው ሊገድል ነው። ላላወቀው ሰበብ፣ በቅጡ ላልተረዳው ምክንያት መሰሉን ከሜዳ ሊጥል ነው።

ከዚህ በላይ ስለ ጦርነት መፃፍ እንደ አፄ ልብነ ድንግል ጦርነት የመናፈቅ ይመስላል።ባይሆንም ልመኝ፣
ሰላም በምድራችን ላይ ይስፈር!!
አዲስ አበባ ነኝ።
ይቅርታ ምህፃረ ቃሉ አሳስቶኝ ነው፤አገኘሁ አሰግድ ነኝ

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

One Comment

  • afrocanart@gmail.com'
    Sisay commented on August 17, 2018 Reply

    ሸጋ አተያይ፤ ለዛ የተሞላ ትረካ – በርታ!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...