Tidarfelagi.com

የጣልኩብሽ ተስፋ

ከአምስት አመታት በፊት የሐረር ከተማን በጎበኘሁበት ወቅት ያደረብኝን ተስፋ እና ስጋት “ካሜን ባሻገር “ በተባለው መፅሀፌ ውስጥ በሚከተለው መንገድ አስፍሬው ነበር፤

“ ከጁገል በር ላይ ቆሜ ሳያት ፤ሀረር ተስፋና ስጋት አግዛ ታየችኝ፤ የምን ተስፋ ? የምን ስጋት? ባንድ ወቅት ስለ ስለሀረር አንድ ቀልድ ሰምቼ ነበር፤

ጥቂት ሰዎች ተሰብስበው አቶ መለስ ዜናዊ ዘንድ ይመጡና “ሐረር ከተማ ውስጥ ቆሞ የሚገኘው የነፍጠኛው የራስ መኮንን ሀውልት ፈርሶ በቦታው የኢሚር አብዱላሂ ሀውልት ይቁም ፤ የሚል አቤቱታ ያቀርባሉ፤ መለስ ፤ ትንሽ አሰብ አደረገና” የራስ መኮንን ሀውልት ማፍረስ አትችሉም፤ ነገር ግን በራስ መኮንን ሀውልት ላይ አሚር አብዱላሂን ማፈናጠጥ ትችላላችሁ፤ “ ብሎ መለሰላቸው ይባላል፤

ቀልዱን እንደሰማሁት ይህ የሐረርን ህዝብ እምነት እንጂ የመለስ ዜናዊን እምነት የሚያንፀባርቅ አይደለም አልሁ፤ የሐረር ህዝብ ራስ መኮንን እና ኢሚር አብዱላሂን ባንድ ፈረስ ማስኬድ ችሉዋል፤ በከተማው ውስጥ የሁለቱ ሰዎች መታሰቢያዎች ይታያሉ፤ ኩታ ገጠም ድንበር ያላቸው ቤተክስያኖችና መስጊዶች ተቃቅፈው የሚኖሩባት ሆደ ሰፊ ከተማ ናት -ሐረር፡፡ ዩኒሴኮ ይህንን የከተማዋን ልዩ ችሎታ አድንቆ “ የመቻቻል ከተማ “ የሚል ማእረግ አጎናፅፉዋታል፡፡

ይህ በጎ የሆነ የህዝብ ባህል ከባለስልጣኖች አላማ ጋር ሲላተም አየሁና ስጋት ገባኝ ፤ ወደ ሐረሪ ብሄራዊ ሙዚየም ጎራ ስል በትልቅ ፍሬም የታጠረ የፎቶ ማህደር ውስጥ ተቀምጦ የሚጎበኝ ምስል አየሁ፤ የጥንታዊ ህንፃ ምስል ነው፤ ከምስሉ ራስጌ “ በምኒልክ ወረራ ወቅት ወደ ቤተክርስትያንነት የተቀየረው የቀድሞ የረዑፍ ባሻ መስጊድ “ የሚል ለቁጭት የሚጋብዝ ማስተዋወቂያ ተፅፎበታል፤ በወረራው ወደ መስጊድ የተቀየረ የተባለው የመድሃኔአለም ቤተክስርትያን ሀገር አማን ነው ብሎ በብጫ አጥር ተከብቦ ከከተማው እምብርት ላይ ቁጭ ብሉዋል፤ ከቤተክርስትያኑ ፊትለፊት የጨለንቆ ሰማእታት ሀውልት እንዲቆም ተደርጉዋል፤ የምኒልክና የአብዱላሂ ሰራዊት የተዋጉበት ጨለንቆ ከሀረር ብዙ የሚርቅ መንደር ሆኖ ሳለ” የጨለንቆ መታሰቢያ” ቤተክስያኑ ደጃፍ ላይ እንዲቆም የተደረገበት ምክንያት ምን ይሆን? ያስገባሪን መታሰቢያና የገባሪን መታሰቢያ በቅርብ ርቀት ማፋጠጥ ለህብረተሰቡ የተዘጋጀለት ወጥመድ እንዳይሆን ስጋት አለኝ”

( ከአሜን ባሻገር ፤ 2008 ፤ ገፅ 155)

አሁን የሚሆነውን ቁጭ ብየ ሳይ በደበበ ሰይፉ ግጥም ውስጥ ያሉ እኒህ ስንኞች ይመጡብኛል፤

የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞ ጠፋ “

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...