Tidarfelagi.com

የጉራጌ ሕዝብ ከ158 ዓመታት በፊት

ሰማዩም ምድሩም የኛ ነው የሚሉን ኦነጋውያን የሚይዙት ቅጣምባሩ ጠፍቷቸዋል። ከሰሞኑ ደግሞ ባሰራጩት በምስል የታገዘ ዜና በጉራጌ ምድር ከ158 ዓመታት በፊት ተቋርጦ ነበር ያሉን የገዳ ስርዓት ማስጀመራቸውን ነግረውናል። እንዲህ አይነት ዜና ሲሰማ ዝም ማለት ተገቢ ባለመሆኑ ከ158 ዓመታት በፊት የጉራጌ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር ስለነበረው ግንኙነት፣ የነበረውን የውስጥ አስተዳደር ታሪክና ገዳ የሚባለው የወረራና የዘመቻ ስርዓት ወደ በአካባቢው በደረሰበት ወቅት ስለተከተሉ ሁኔታ ሳነብ ከተማርሁት የሚከተለውን ጀባ ብያለሁ።

የጉራጌ ምድር ከጥንት ጀመሮ የኢትዮጵያን መንግሥት ያቆሙ ዋናዋና የጦር መሪዎችን ያፈራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አውራጃ ነበር። ተመዝግቦ ከምናገኘው ታሪክ ብንነሳ እስከ ሞቃድሾ ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት ባስተዳድሩት ዐፄ ዐምደ ጽዮን [እ.ኤ.አ. ከ1314 ዓ.ም. – 1344 ዓ.ም. ድረስ የነገሡ] ዜና መዋዕል ውስጥ ጉራጌ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር ቅርብ ቁርኝት የነበረው ሕዝብ እንደነበር ተጽፎ እናገኛለን። በዘመኑ የጉራጌ አውራጃ የውስጥ አስተዳደር ይመራ የነበረው በጉራጌ ተወላጅ አበጋዞች ነበር።

ጉራጌ አውራጃውን ከራሱ በተወለዱ አበጋዞች ያስተዳድር የነበረው ኦሮሞ በገዳ መተዳደር ከመጀመሩ ቢያስ ከ208 ዓመታት በፊትና ኦሮሞ ደቡብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅና መካከለኛው ኢትዮጵያን መውረር ከመጀመሩ ከ200 በላይ ዓመታት በፊት ነበር። የኦሮሞ ብሔርተኛው ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን “The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia” በሚል ማሳተመው መጽሐፉ ገጽ 158 ላይ እንደጻፈው ኦሮሞ በገዳ መመራት የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1522 ዓ.ም. እንደሆነና የመጀመሪያው ገዳ “ገዳ መልባ” እንደሚባል ነግሮናል። ጉራጌ ግን ኦሮሞ ገዳ ከጀመረበት ከ1522 ዓ.ም. በመቶዎቹ በሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ቆዬት ብዬ የማቀርብላችሁ ከገዳ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላው የራሱ የውስጥ አስተዳደር ሥርዓት ነበረው።

የጉራጌ ምድር ክርስትና ቀድሞ በሰፊው ከተሰበከበትና ከጸናበት የኢትዮጵያ አውራጃዎች አንዱ ነበር። በወቅቱ የተጻፈው ድርሳነ ዑዔል ይህንን ያረጋግጣል። ከድርሳለ ዑራኤሉ በተጨማሪ ራሳቸው የጉራጌ ተወላጆችም ይህንን ታሪክ ጽፈዋል። የጨቦ ኡዳደ እየሱስ ሕዝብ ታሪክ ጸሐፊው አቶ ምስጋናው በላቸው “የጨቦ ኡዳደየሱስ ሕዝብ አጭር ታሪክና ባሕል” በሚል በመጋቢት 1985 ዓ.ም. ከጀርመን በጻፉት የታሪክ መጽሐፋቸው ገጽ 66 ላይ እንደጻፉት አይመለል በሚባለው የጉራጌ ምድር የሚኖረው «ክስታኔ» የሚባለው ሕዝብ መጠሪያ «ክስተነ» ከሚል ከቦታው ቋንቋ የመጣ መሆኑንና ትርጉሙም ክርስቲያን ማለት እንደሆነ ነግረውናል። አይመለል የመጀመሪያዎቹ ክስታኔዎች ወይንም ክርስቲያኖች የሰፈሩበት ምድር ነው።

ክስታኔ፣ ጉራጌ በመባል በወል ከሚጠሩት የቤተ ጉራጌ ማኅበረሰቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን ሶዶ ጉራጌ እየተባለም ይጠራል። የክስታኔ ሕዝብ ቋንቋ ክስታኒኛ ይባላል። አቶ ምስጋናው በላቸው በመጽሐፋቸው ገጽ 63 እንደነገሩን በጨቦ ምድር ብቻ ከግራኝ ወረራ በፊት 40 ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት የነበሩ ሲሆን ከወረራው በኋላ የተረፉት ግን 13 ስደተኛ ታቦቶች የተዳበሉበት ታሪካዊው የዋሻ ሥላሴ ቤተክርስቲያንና በወንጭት ደሴት ላይ የነበረው የቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ብቻ መሆናቸውን ነግረውናል። አቶ ምስናጋው ጨምረው እንደጻፉት የዋሻ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የተሰራ መሆኑን ከጉራጌ ታሪክ አዋቂ አባቶች አገኘሁት ያሉትን ታሪክ ነግረውናል። ይህ የጉራጌ ሕዝብ ክርስትናን ከተቀበሉ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገዶች መካከል መሆኑን ያሳየናል።

ጉራጌ የኢትዮጵያን ሰለሞናዊ መንግሥት በሸዋ ምድር ካቆሙ የኢትዮጵያ ዋና ዋና ነገዶች መካከል ቀዳሚው ስለመሆኑ ሌላው ማስረጃ በዐፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት የተጻፈው ድርሳነ ዑራዔል ነው። በዘመኑ ድርሳነ ዑርዔል እንደተጻፈው እግዚአብሔር መስፍንነት ከጉራጌ፥ ከመንዝና ከወረብ እንዳይወጣ ለአጼ ናዖድ [የንግሥና ዘመናቸው እ.ኤ.አ. ከ1494-1508 ዓ.ም. ድረስ ነው] ቃልኪዳን ገባለት ይለናል። ይህ በድርሳነ ዑራዔሉ ከገጽ 311-315 ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን ሙሉው ቃል እንዲህ ይነበባል፤

“ወእምድኅረ ፡ ዝንቱ፡ወሀቦ ፡ ለናዖድ ፡ እግዚእነ ፡ኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ኪዳነ ምሕረት ፡ ከመ ፡ ኢይጥፋእ ምስፍና ፡ ወምልክና ፡ በምድረሸዋ ፡ ወመንዝህ ወበሀገረ ፡ ጐራጌ ፡ ዘይብልዎ ምድረ ፡ ወረብ ፡ ወምሁር።”

ትርጉም፡

“ከዚሀ ፡ በኋላ ፡ ጌታ ኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ከምድረ ፡ ሸዋ ፡ምሁርና ፡ምድረ ፡ ወረብ ፡ ከሚባለው ከጐራጌ ፡ አገር ፡ ከመንዝም ፡አገዛዝና ፡ መስፍንነት ፡ አንዳይጠፋ ፡ ለናዖድ ፡ ቃል ፡ኪዳን ፡ ሰጠው።”

በድርሳኔ ዑራዔሉ እንደተገለጠው የጉራጌ ሕዝብ በዘመኑ የኢትዮጵያ መስፍን ሆነው እንዲሾምላቸው ከተወሰነላቸው ሶስት የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነበር። በዚህ መልክ እስከ መካከለኛው ዘመን የማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ዋልታ የነበረው ጉራጌ ከግራኝ ወረራ በኋላም ለኢትዮጵያ ቤተመንግሥት በጣም ቅርብ ነበር። ከግራኝ ወረራ በኋላ ዋናኞቹ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ራሶች ጉራጌዎች ነበሩ።

ከግራኝ ወረራ በኋላ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን ከነበራቸው አራጊ ፈጣሪ ጉራጌዎች መካከል በዐፄ ያዕቆብ [ እ.ኤ.አ. ከ1597 ዓ.ም. – 1603 ዓ.ም.፤ እንዲሁም ከ1604 ዓ.ም. -1607 ዓ.ም. ድረስ የነገሡ] እና በዐፄ ዘድንግል [ እ.ኤ.አ. ከ1603 ዓ.ም. – 1604 ዓ.ም. ድረስ የነገሡ) ዘመናት የነበሩትን ራስ ዘሥላሴን ለአብነት መጥቅስ ይቻላል። የጉራጌ ተወላጁ ራስ ዘሥላሴ ዐፄ ዘድንግል “መልከ ሐራ” በሚል ያቋቋሙትን የንጉሥ ሠራዊት ይመሩ ነበር። ዐፄ ሰርጸ ድንግል እ.ኤ.አ. በ1597 ዓ.ም. ከሞቱ በኋላ ደግሞ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያን የገዙት ራስ ዘሥላሴ ነበሩ ማለት ይቻላል።

ራስ ዘሥላሴ በዐፄ ሰርጸ ድንግል ዘመን «ቁርባንና ሚዛን» የተባለው ደምብያ የሰፈረው ሰራዊት መሪ ነበር። ዐፄ ዘድንግል ለወታደሩ አመጽ ምክንያት የሆነ ገባሩን ነጻ የሚያወጣ አዋጅ አውጀው ነበር። ይህ አዋጅ ወታደሩንና ገባሩን ወይም ዜጋውን እኩል ያደረገ አዋጅ ነበር። በዚህ ምክንያት ራስ ዘስላሴና ቁርባንና ሚዛን የተባለው ሰራዊት በንግሡ ላይ አምጾ ደምብያ ውስጥ ባርጫ ከተባለ ስፍራ ዐፄ ዘድንግልን ገደሉት። ጣሊያናዊው የታሪክ ተመራማሪ ኮንቲ ሮሲኒ ያሳተመው በዘመኑ የተጻፈው ታሪከ ነገሥት መንግሥት በጉራጌው በራስ ዘስላሴ እጅ ገብቶ ነበር ይላል። ኮንቲ ሮሲኒ ያሳተመው ታሪከ ነገሥት ውስጥ የሚገኘው ይህ ታሪክ የሚከተለውን ይመስላል፤

“ወበውዕቱ ፩ዓመት ተጻልዕዎ ሐራሁ ለሐጼ ዘድንግል እለ ይብልወሙ ቁርባን፥ወሚዛም ወእርስ ዘስላሴ በምክንያተ ዝንቱ አዋጅ ዘአንገረ ውእቱ እንዘ ይብል ሰብእ ሐራ ፤ ወገብራ ምድር። እስመ ዓመፁ ኩሉ ዜጋሆሙ ወቀተልዎ በኵናት ማዕከለ ደምብያ ዘውእቱ ባርጫ [1604 ዓመተ ምህረት] ። […] ወእምድኅረ አዘዘ እራስ ዘሥላሴ ከመ ያንስእዎ ለሐጼ ዘድንግል ወአንሥእዎ ወወሰድዎ ውስተ ደሴተ ዳጋ ወቀበርዎ ህየ። ወነበረት መንግሥት በዕዴሁ ለጉራጌ ራስ ዘሥላሴ።” [ ምንጭ፡ Conti Rossini, C. (1893). Due squarci inediti di cronica etiopica. Rendiconti della reale accademia dei Lincei. C/asse di scienze morali. storiche e. filologiclre; Page 807.

ትርጉም፡

በአንድ ዓመት ውስጥ ቁርባንና ሚዛን የተባሉት ወታደሮች እንዲሁም ራስ ዘሥላሴ “ሰው ነጻ ነው፤ምድር ገባር ነው” በሚለው አዋጅ ምክንያት ዐፄ ዘድንግልን ተጣሉት። ዜጎች [ንጉሡን ደግፈው አመጹ]። በደምብያ መካከል ባርጫ ውስጥ በጦር ወግተው ገደሉት። ከዚህ በኋላ ራስ ዘሥላሴ ዐፄ ዘድንግልን እንዲያነሱት አዘዘ፤አንስተው በዳጋ ደሴት ቀበሩት። መንግሥት በጉራጌው በራስ ዘሥላሴ እጅ ነበረች።
ከዚህ የምንረዳው በዘመኑ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት አራጊ ፈጣሪ የነበሩት የጉራጌ ተወላጁ ራስ ነበሩ።

ወደ ውስጥ አስተዳደሩ ስንመጣ የጉራጌ ሕዝብ አውራጃውን የሚያስተዳድረው ከተወላጆቹ በሚመረጡ አበጋዞች ነበር። የጨቦ ተወላጁ አቶ ምስጋናው በላቸው የጉራጌ ሕዝብ አካል የሆነውን የጨቦ ሕዝብ የውስጥ አስተዳደር በሚመለከት “የጨቦ ኡዳደየሱስ ሕዝብ አጭር ታሪክና ባሕል” በሚለው መጽሐፋቸው ከገጽ 85-89 የሚከተለውን ጽፈዋል፤

“አበጋዙ የሕዝቡ ጠቅላይ አስተዳዳሪ ሆኖ እንደ አባት የሚታይ መሪ ነው። አበጋዙ እንደኃላፊነቱ ሥፋትና የሥራው ክብደት ከእጩነት አስንቶ እስከተሾመበት ድረስ በጥልቅ ተጠንቶ የሚመረጥበት ሁኔታ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። ይህም የሚሆነው በየሁለት ዓመት ግፋ ቢል በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ነው። የአንድ አበጋዝ የአገልግሎት ዘመኑ ለሁለት ዓመት ብቻ ሲሆን በዚሁ ሁለት ዓመታት ውስጥ ዳኝነቱና ተወዳጅነቱ ከፍ ያለ ምስክርነት ካገኘ ያለ ምንም ተቃውሞ አንድ ዓመት ተመርቆለት ለሶስት ዓመታት ያስተዳድራል። ድጋሚ መመረጥ የለም። . . .

አበጋዝ ሲመረጥ በጊዜው ሥልጣን ላይ ያለው የአመራር አካል ሥልጣን ከመልቀቁ ከብዙ ወራት በፊት አበጋዝ መመረጥ የሚገባው ሰው ስም ከየጎሣው በሚስጥር ይጠየቃል። አበጋዝ መሆን ይችላል ተብሎ ከየጎሳው ከየአካባቢው የተጠቆመውን አዛውንት የእያንዳንዱን ሁኔታ ማለት ባሕሪው፣ ተቀባይነቱና የማስተዳደር ችሎታውን በሚስጥር አጥንቶ አበጋዝ ይሆናል ብሎ ያመነበትን ለጠቅላላው የሕዝብ ጉባኤ ያቀርባል።

ሕዝቡ ካመነበት በኋላ የሹመቱ ሥነ ሥርዓት የሚፈጸምበትን ቀን ራቅ አድርጎ ይቀጥራል። ቀጠሮው ራቅ የሚለው በሕዝቡ ጥያቄ ሆኖ እንደተለመደው በሥርዓተ ሹመቱ ቀናት ሕዝቡ በፈቃዱ የሚደሰትበትን የእርድ በሬዎች፣ የሚበላና የሚጠጣውን ከየጎሳውና ከየአካባቢው አጠራቅሞ ለማምጣት እንዲመቸው ብሎ ነው። የተሿሚው ጎሳ አብዛኛውን ያቀርባል።

በስርዓተ ንግሡ ቀን አበጋዙ በሻሽ ጥምጥም ዘውድ ሰሠርቶላቸው፣ የአበጋዙ ባለቤት በፀጉራቸው ጉንጉን ዘውድ ተሠርቶላቸው አበጋዙ በሠንጋ ፈረስ፣ ባለቤታቸው “እቴ” ተብለው [እቴጌ ማለት ይመስላል] በሰጋር በቅሎ ላይ ተቀምጠው በጎሳቸው እጀብና ሆታ ሰንበት ወራቡ ሲደርሱ እዚያ ተሰብስቦ የሚጠብቃቸው ሕዝብ በዘፈንና በእልልታ ይጠብቃቸዋል። ሰንበት ወራቡ የመጀመሪያ ሥርዓተ ንግሥ የሚፈጸምበት ቦታ ነው። እዚያ ቦታ ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ አበጋዙና “እቴ” የሚቀመጡበት በሦስት ድርብ የተሰራ የእንጀራ መደብ ይዘጋጃል። እንጀራ ላይ የሚቀመጡበት ምክንያት እነሱ በሚያስተዳድሩበት ክልል ጥጋብ እንዲሆን ተመኝተው ነው ተብሎ ይታመናል።

ተሿሚዎቹ የክብር ሥፍራቸውን ከያዙ በኋላ በገንዙና በአባጅልባዎች አማካኝነት ሕዝብ በተሰበሰበበት ሥርዓተ ንግሡ ይፈጸማል። ወዲያውኑ ቃለ መሐላ ሲፈጸም ወይፈኖች፣ በሬዎች ታርደው ፈንጠዝያው ይቀጥላል። ይህ የደራ ድግስ በየደረጃው እየተበላ አምስት ቀን ይቆያል። በአምስተኛው ቀን አበጋዙና “እቴዋ” ዋሻ ሥላሴ ቤተክርስቲያን እንደዚያ ታጅበው ሄደው የመጨረሻ ሥርዓተ ንግሥ ከተፈጸመ በኋላ አበጋዙ ወደ ጅሎት ቦታው ተመልሶ አገልግሎቱን ከፈጸመው አበጋዝ መንበሩን ይረከባል። አንዴ አበጋዝ ሆኖ የተመረጠ አዛውንት መንበሩንና አስተዳደሩን በፍቅርና ራሱ ቃለ ቡራኬ ሰጥቶ ለአዲሱ አበጋዝ ሲያስረክብ በትረ መንግሥቱ [በእጁ ይይዘው የነበረው ዘንድ] ለክብሩ ሲባል በእጁ ይቀራል። የአገልግሎቱ ዋጋም ዕድሜውን ሙሉ አበጋዝ ተብሎ መጠራት ሆኖ ይኸው የማዕረግ ስሙና የሚይዘው አንድ ነበሩ።”

የጉራጌ ሕዝብ የውስጥ አስተዳደር በዚህ መልክ የተገለጸውን ይመውላል። አበጋዞቹ በሕዝብ ፊት ሥርዓተ ንግሥና ከፈጸሙ በኋላ የሥርዓት ንግሥናው ፍጻሜ የሚሆነው አበጋዙና እቴዋ በጥንታዊው ዋሻ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የመጨረሻውን ሥርዓተ ንግሥት ከፈጸሙ በኋላ ነው። በዚህ መልክ አውራጃውን ሲያስተዳድር የኖረው የጉራጌ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት የተቋረጠው በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ነው። በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ከማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት የተቋረጠው የጉራጌ ሕዝብ በተለይም የጨቦ ክስታኔና ምሑር ሕዝብ በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ክሥታኔና ምሑር የነበረውን ቋንቋውን በአባገዳዎች ተገዶ እንዲተውና ኦሮምኛ እንዲናገር በመገደዱ ብዙ ስቃይ እንደደረሰበት አቶ ምስጋናው በመጽሐፋቸው አትተዋል። አቶ ምስጋናው በመጽሐፋቸው ገጽ 50 ላይ እንደጻፉት ኦሮሞ በገዳ ስርዓት እየተመራ የጉራጌን ምድር ሲወር የነበረውን ጥፋት እንዲህ ይገጹታል፤

“በዚህ ጊዜ [ኦሮሞ ወደ ግራጌ ምድር በተስፋፋበት ወቅት ማለታቸው ነው] ስለ ቋንቋ የነበረው እምነት ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ” የሚል ሆነ። ትርጉሙም ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” ማለት ነው።”

እንግዲህ! ኦነጋውያን በጉራጌ ምድር ከ158 ዓመታት በፊት ነበረ ያሉትን ገዳ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ያሉት ገዳ የሚባለው የወረራ ስርዓት ሳይመሰረት የራሱ የውስጥ አስተዳደር የነበረውን የጉራጌ ሕዝብ “ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” እያሉ አባገዳዎች የጉራጌን ሕዝብ ያጠፉበትን፣ ከርስቱ ያፈለሱበትን የወረራና የጦርነት ስርዓት መልሰው ለመትከል ነው። አባገዳዎች ወደ ጉራጌ ምድር ብቻ ሳይሆን ወደ ምዕራብ፣ መካከለኛውና ደቡብ ኢትዮጵያ የተስፋፉት “ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” እያሉ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት እየፈጸሙ ነው። ኦነጋውያን በጉራጌ ምድር መልሰው ሊተክሉ እየፈለጉት ያለው የገዳ ስርዓትም “ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ” እያሉ አባገዳዎች ዘር ያጠፉበትን፣ ባላመሬቱን ከርስቱ ያለፈሉበትን የወረራና የዘር ማጥፋት ስርዓት ነው።

የጨቦ ተወላጁ አቶ ምስጋናው በላቸው በመጽሐፋቸው ገጽ 66 እንደነገሩን አባገዳ አካባቢውን ከወረረው ጀምሮ የነበረው ስቃይ፣ ጭቆና መከራ ተወግዶ በጨቦ ምድር ፍቅርና ሰላም የወረደው ዳግማዊ ምኒልክ ሲደርሱላቸውና ከአባገዳ ባርነት ሲያላቅቋቸው እንደሆነ ጽፈዋል። «የሰላሙ ዘመን» ያሉት የዐፄ ምኒልክ ፀሐይ በጨቦ ምድር መውጣት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የጨቦ ካሕናት ከዐፄ ምኒልክና ራሶቻቸው ጋር እየዞሩ በኦሮሞ ወረራ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የጥንቱን ወንጌል የማስፋፋት ተግባራቸውን በመቀጠል እስከ ዳር አገር ድረስ እየዞሩ ክርስትና መነሳት የሚፈልገውን ክፍል እንዳጠመቁና ከመሐል ኢትዮጵያ እስከ ኖኖና ጡቁር ምድር ድረስ በመሄድ አዳዲስ አማኞችን ያጠምቁት የጨቦ ቄሳውስት እንደነበሩ አውስተዋል።

ባጭሩ የጉራጌ ሕዝብ ለሺ ዘመናት የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ዋልታ የነበረ፣ የራሱ የሕዝብ አስተዳደር ስርዓት የነበረው ሰራተኛ ሕዝብ እንጂ ገዳ የሚባል ከዲሞክራሲ ጋር የስናፍጭ ቅንጣት ታህል ግንኙነት የሌለው የወረራ፣ የጦርነት፣ የመስፋፋት ዘመቻና የዘር ማጥፋት የተካሄደበት ስርዓት ባለቤት አልነበረም!

One Comment

  • www.silesangawe@gmail.com'
    ስለሺ ፍቃዱ commented on January 28, 2022 Reply

    ዋው

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...