Tidarfelagi.com

የገደለ አባትሽ የሞተው ባልሽ (ክፍል አራት)

“ጎዳኧው? ጥርስ ነው ያወለቅከው?….. እንደው ምን ተሻለኝ ይሁን?” በሩን የከፈተችልኝ እማዬ ናት።
“እማዬ ደግሞ ትንሽ ጫፍ ካገኘሽ መምዘዝ ነውኣ?…. እኔ ከማንም አልተጣላሁም።”

“አዪዪ…. ተዋ! ከሰው ካልተጣላህ በቀር በምንም ምክንያት አሚ እንዲህ እሳት አትለብስም?” ወድያው ድምፅዋን ሾካካ አድርጋ “ምንድነው ነገሩ? ፍቅር ምናምን ብጤ የጀመረችውን ሰው ነው የደበደብከው?” ማወጣጫዋ ናት። አሚ ሌላ ህይወት እንዲኖራት ትመኛለች። ሴት ልጅ ሳታገባ 28 ከሆናት በእማዬ ቋንቋ “ፈንጅ ረግጣለች።” እሷን ምንም አትላትም። የፈረደብኝ እኔን ባገኘችን ቁጥር በመስቀለኛም በቀጥተኛም ንዝንዝዋ ልታወጣጣኝ ትጥራለች።
“እማዬ ምንም የለም። ማንንም አልደበደብኩም። እርምሽን አውጪ ፍቅር ፍቅረኛ የሚባል ነገር የለም።”
ወደሳሎኑ ስንገባ ምሳ ቀርቦ ጋሼና አሚ ተቀምጠዋል። ባቢ ትምህርት ቤት ነው። ሰላም ብያቸው ተቀመጥኩ። ሁሉም ፀጥ ብሎ የሚሰማው እንጀራው ከወጥ ተለውሶ ሲጠቀለል የሚሰማው የልውስ እስእስእስ ብቻ ነው። እሷ ስታኮርፍ ቤቱ አብሯት የሚያኮርፈው ነገር አለው። ቤተኞቹም……… እማዬ አስሬ ያልከረከራትን ጉሮሮዋን ታፀዳለች። ጋሼ ደግሞ በግንባሩ ያየኛል።
“እህ ምንድነው ይሄን ያህል?” አልኩኝ ቢጨንቀኝ
“ምን እንደሆነማ አሳምረህ ታውቃለህ። እኔ ባንተ ምክንያት ትምህርት ቤት መጠቋቆምያ መሆን አለብኝ። አንተ አንድ ሰው በደበደብክ ቁጥር ለሳምንት የተማሪው ምላስ ላይ መክረም ምርር ነው ያለኝ። ጋሼ አንድ በለው…… እህህህ እኔ ከጓደኞቼ ጋር ያለኝን ግጭት ራሴ መፍታት አያቅተኝም። ያንተን እርዳታ አልጠየቅኩህም።”

ጋሼ በቀሰስተኛ አኳኋን የማታየው አይነት በሚመስል ወንበሩን ስቦ ተነሳና እግሩን አየር ላይ እያንሳፈፈ ሲሄድ
“እህህ ጋሼ የሰው አፍንጫ ሰብሮ እኮ ነው የመጣው… ” ጋሼ በአይመለከተኝም ትከሻውን እስክስታ እንደመስበቅ አድርጎ ወደመኝታ ቤቱ ገባ። እማዬም ብትሆን የተደብዳቢውን ማንነት እስክታጣራ እንጂ እንደማትሳተፍ ግልፅ ነው። እህሉ ላይ ያደፈጠች መስላ ጆሮዋን አቀሳስራለች።
“ኧረ ነካ ነው ያደረግኩት።”
“እኮ ነካ አድርገህ አፍንጫውን ከሰበርክ ብትመታው ትገድለው ነበራ ። ደሞ አታፍርም ነካ ነው ያደረግኩት ትላለህ?”
“አስካል? አስካል? መድሃኒቴን የት ነበር ያኖርኩት?” ጋሼ ነው። መድሃኒቱ ጠፍቶበት አይደለም። ዘወር በይ ማለቱ እንጂ።
“ስትፋቀሩ በአንድ ቆርኪ ገላችንን ካልታጠብን ማለት…… ስትጣሉ መንቧለል… ” እማዬ እያጉረመረመች ተነሳች። ጋሼ ስለጠራት መናደዷን በኛ የተናደደች ታስመስለዋለች።
“የምሬን ነው አሮን በጣም ነው ያበዛኧው ”
“እሺ ይቅርታ ። ቆይ እኔ ካልጠበቅኩሽ…… ”
“እንዳትጨርሰው እሺ… እየተደባደብክ ከአለም ክፋት ሁላ ትጠብቀኛለህ? ”
“ሰው በተቀባበት ነው።”
“የምትጠቅመኝ መሰለህ? በራሴ መጋፈጥ እንድችል ስትተወኝ ነው የማልጎዳ ጠንካራ የምታደርገኝ። ስንቴ ልንገርህ? ”
“ይቅርታ አልኩኮ አሚዬ ”
“ሁለተኛ ደግሞ ምንም ነገር ብነግርህ… ” አለች ድምፅዋን ቀንሳና ቁጣዋ በርዶ
“ለስንት ቀን?”
“እኮ ታያለህ! ”
“አንቺ ግን አፍንጫው ተሰብሮ ስታዪው አሳዝኖሽ ነው ወይስ አማሎሽ ነው እንዲህ ሲኦል ሆነሽ የጠበቅሽኝ”
“እሱን የት አይቼው ጓደኞቹ ናቸው የነገሩኝ። እሱማ ካሁን በኋላ ሲያየኝ ሁላ የጎማ ጭስ እንደሸተተው እባብ አይቀለባበስም ብለህ ነው? ለራሱ ፈሪ ነው።” ቆጣዋ እኮ እስከዚህ ነው። በሰከንድ ውስጥ ምንም እንዳላደረግኩ ሁሉ ትሆናለች።
“ይልቅ ሰርኬን ላስተዋውቅሽ እስኪ ዛሬ እንውጣ? ”
“ሃሃሃ አሮኔ ደግሞ እስከዛሬ ያስተዋወቅከኝን ሁሉ ቆይ አንተ ራሱ ስማቸውን ታውቀዋለህ? መልካቸውን ሁላ ካስታወስክ እቀጣለሁ። ሃሃሃ ስታገኛቸው የት ነበር የማውቃት ምናምን ብለህ ሳይሆን ይቀራል የምታልፈው? ተሳስተህ ብቻ አንዷን ያስቀየምካትን ድጋሚ ጠብሰህ ሰልባህ መሽኛ ሁላ እንዳትነሳህ ሃሃሃሃ ”
“እንዴ መቀባት ? ወሬኛ…! ደሞ እሷ ናት ካልተዋወቅኳት ያለችኝ።”
እነጋሼ ሳቃችንን ይጠብቁ ይመስል ተሽቀዳድመው ወደሳሎን መጡ።
“ባቢ ወላጅ አምጣ ተብሏል ትምህርት ቤት እና እሱ ካልሆነ ማንም አይሄድልኝም ብሎሃል። ጠዋት እንድትሄድለት።” ጋሼ ነው።
“ምን አድርጎ ነውሳ?” ብዬ ከመጠየቄ አሚ ቦፈፈች
“የክፍሉን ልጅ ሲስም ተይዞ።” አለ ጋሼ። ሁሉም አውካካ
“እና ለምንድነው እኔን የመረጠው? እንደለመደው አንዳችሁ አትሄዱም ነበር? ”
“ሃሃሃሃ እሱን ብትጠይቀው አይሻልም እሱን?” እማዬ ናት። ሽንቆጣ ስትሆን የምትናገርባት ሸርዳጅ ድምፅ አለቻት።
“ይሄ በ10 አመቱ ስሞ ወላጅ ያስጠራ 20 ሲሞላውኮ ጉድ ሊያፈላ ነው።” አልኩኝ።
” ያልዘሩት አይበቅል። በአጎቱ ወጥቶ ነዋ…… ” እማዬ
የቤተሰቤ የትዝታ ክር እንደዚህ አይነት ቅፅበቶች ላይ ይንጠለጠላል። ቤተሰብ ሲባል ሽው የሚለኝ ቅፅበት ይሄ ነው። እህል የተበላበት ትሪ ሳይነሳ ፤ የበላንበትን እጃችንን ሳንታጠብ ፣ የእማዬ የወጥ ሽታ የደባለቀው ሳቅና ተረብ………
*** *** *** ***

“ይሄ ጭስህ ገና መአት ያመጣብሃል።” ትለኛለች ጆሮዬ ስር ተለጥፋ ሰርኬን ላስተዋውቃት ብዬ እራት ብጋብዛት። “ቆንጆ ናትኮ ግን ከምር… ”
“ዝም ስትል ነዋ! ” እላታለሁ ጥርሴን ገጥሜ በፉጨት ድምፅ
ብዙም ሳይቆይ የጦፈ ክርክር ውስጥ ገቡ። የኔዋ ናት እንጂ ደግሞ የምትገርመው በደቂቃ ውስጥ ዛር እንዳለበት ተንዘረዘረችኮ ደሞ ባላስጠነቅቃት…
“ሀገር መሰረቱ ግለሰብ ነው። ጠንካራ ግለሰብ ማፍራት ያልቻለች ሀገር ጠንካራ ህዝብ የላትም። እንደህዝብ የተገነባ ድልዳል የሌላት ሀገር ደግሞ መልከአ ምድሯ ብቻ ነው የሚተርፋት እሱንም ስግብግብ ግለሰቦችና መስቃላ ስብስቦች ካልተቀራመቱት…… ” የኔዋ ጉድ ናት ይህን ባይዋ
“ሀገር ከግለሰብነት ታልፋች። በግለሰብ ሜንታሊቲ ሀገር መገንባት አንችልም።” ሰርኬ ናት
እዚህ ሀገርማ እኔ ሳልሰማ ሴቱን ሰብስቦ ያጠመቀው አለ። ደግሞ እንዲህ ባለ መንፈስ ውስጥ ስትሆን ለምሰጣው ይረዳት ይሆን አላውቅም የምታጨሰው ጉድ አላት። እኔንም ሲጋራዋንም………… ለኮሰችው

በነገራችን ጎን እኔ ከነአካቴው ሲጋራ አጭሼ አላውቅም። አንድ አይናለም የምትባል የእማዬ ጓደኛ ናት ጭስና አክሱሜን አቋልፋው የሞተችው።

የገደለ አባትሽ የሞተው ባልሽ (ክፍል አምስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...