Tidarfelagi.com

የገደለ አባትሽ… የሞተው ባልሽ (ክፍል፦ ሁለት)

አሚዬ ከእህቴም በላይ ናት።…… አባቷ ወንድሜን ከገደለው እለት ጀምሮ እሷ የኛ ቤተሰብ አካል ሆናለች… የወንድሜ ምትክ.……

የሚያውቀን ሁላ ለዓመታት ከእንጀራው ጋር አብሮ ስማችንን አላመጠው፣ ጎረቤት ከተጣጡት ቡናቸው ጋር ስማችንን አብረው አድቅቀው… አፍልተው ጠጡት… እንዴት ከገዳያቸው ጋር ይወዳጃሉ? ሰው ጠላቱን እንዴት በጉያው ይሸሽጋል?…… ጉንጫቸው እስኪዝል አኘኩን……

የትዝታ ገመድ የተንጠለጠለው የሆነች ቅፅበት ላይ አይደል? …… ሀዘንም ሆነ ደስታም… ያቺ ቅፅበት የሰከንዶች ወይ የደቂቃ ትዕይንት ትሆናለች።.… ቅፅበቷን ያጀቡት እያንዷንዷ ስሜት… ጠረን፣ ድምፅ፣ ምስል፣ … እድሜህን ሙሉ ያስፈግግሃል ወይ ደግሞ በስቃይ ያስነክስሃል… …

የስቅለት ቀን ነበር። የሰፈራችን ሴቶች ነጠላቸውን ተከናንበው ከስግደት እየተመለሱ… ፣ የአውደ ዓመት ጠረን፣ ወከባ……… የጊቢው በር ፊትለፊት ከአብርሽ ጋር ቆመናል።… መንታ ወንድሜ ነው። በ4 ደቂቃ ታላቄ…

«ይዣት የሆነ ቦታ እብስ ልበል? » ይለኛል። በአማላይ ፍቅር የነቀለ ሰሞን ነበር።

«ታውቃለህ ሼባው ያወቁ ቀን ንሰሃ ሳትገባ ነው የሚያሰናብቱህ»

የአማላይ አባት ከብቸኛ ልጃቸው ከአማላይ ቀጥሎ የሚኮሩበት በደነፉ ቁጥር ወደ ሰማይ የሚተኩሱት ሽጉጥ አላቸው። ክብር ከነፍስ የሚበልጥባቸው ሀገር ሰፈሩ የሚያውቃቸው ኩሩ ናቸው። ወንድሜ በከፉ ቀን ልጃቸውን እስካየበት ቀን ድረስ እኔም እንደሰፈራችን ወጣቶች ሁሉ የማከብራቸው በሱቃቸው በኩል ሳልፍ ከአንገቴ ጎንበስ ብዬ ሰላምታ የምሰጣቸው ሰው ነበሩ። ከወራት በፊት አንድ ምሽት የሰፈራችን ቅያስ ላይ አብርሃም አማላይን ሲስማት ካየሁት በኋላ ከማክበሬ ልቆ የሚያስፈሩኝ ሰው ሆኑ። አማላይ አንድም በአባቷ ሽጉጥ ሁለትም በኮስታራነቷ ሁሉም የሚቋምጥላት ማንም ደፍሮ የማያናግራት ነበረች። አብርሽም ከሷ ጋር በፍቅር መንጎዳጎድ እስከጀመረ ድረስ በድብድብ ሰፈሩ ያጨበጨበለት ፣እስር ቤቱን በዓመት አንዴ ካልጎበኘ የሚከፋው ወመኔ ነበር። አማላይ ካማለለችው ወዲያ ከጋሼ ጣውላ ቤት ከጋሼ ጋር መስራት ሲጀምር ያልገረመው የለም።…

« ባክህ ለራሴ አልጨነቀኝም። እሷ በጣም ፈርታለች። ማርገዟን ካወቁ ያብዳሉ.…… ያውም የኔን ልጅ።»

«አንተ ግን ምን እያሰብክ ነበር? »

«ባክህ እያሰብኩ አልነበረም። ከሷ ጋር ስሆን ከሷ ውጪ ምንም ማሰብ አልችልም…… » ስለእሷ ማውራት ከጀመረ ከሰማሁት እስከሚቀጥለው ስቅለት ያወራል። እኔ ሀሳብ ሆኖብኛል።… እሱ ምንም ድንቅፍ ያለ ነገር እንደሌለ ሁሉ ነው አባት ስለመሆኑ… ስለአማላይ ውበት… መሰጥ ሲል ስለፍቅር ፍልስፍና የሚፈላሰፈው …… ………

«መጣች! » አለ ድምፁ ሁሉ እየተቀየረ…… ነጠላዋን ለብሳ አጠገባችን ስትደርስ የፊቱ ፍካት አማላይን ያየ ሳይሆን አምላክን ያየ ነው የሚመስለው…

«አንቺ ወንድሜን ምን አድርገሽው ነው እንዲህ የተጃጃለው በናትሽ? » አልኳት ሰላም ስትለኝ።

«እሱ ምን እንዳደረገኝ ይጠየቅ እንጂ… »

ትቻቸው ልገባ ትንሽ እንደተራመድኩ አባቷን በአንድ እርምጃ የትዬለሌ እየመተሩ ወደእኛ አቅጣጫ ሲምዘገዘጉ አየኋቸው…… አፈጣጠናቸው የሚቀፍ ነገር አለው።

«አብርሽ? አ ብ ር ሽ?…… » ጮህኩበት

ምንም ከመራመዳችን በፊት እሳቸው አጠገባችን ደርሰዋል።

«አንድ ልጄንማ ለመንደር ወመኔ… በጭራሽ! እኔ ኮለኔል አባተ የተከበርኩ…… »

አብርሽ አማላይን ከልሏት ቆሞ ማውራት ጀመረ።

« ኮለኔል… በልብ እንጂኮ በማዕረግ አይፈቀርም! »

«እኔ ኮለኔል ለክብሬ እሞታለሁ።» ሽጉጣቸውን አውጥተው ወደላይ ተኮሱ። የሽጉጡን ድምፅ የሰሙ ሰፈርተኞች እማዬን ጨምሮ እየተሯሯጡ ወጡ። ሁሉም ሊያረጋጋ በየፊናው መለመን ያዘ። ሽጉጣቸውን ወደ እርሱ አነጣጠሩት። ሴቶቹ ይጮሃሉ።

«እኔ አብርሃም ለፍቅሬ እሞታለሁ።…… » ደም ስሩ ተገታተረ ። ከአማላይ በፊት የነበረው አብርሃም ሆነ። « በሉኣ… ይተኩሱ! »… …. ሁለቴ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ ፣ አብርሃም ሲወድቅ፣ እማዬና አማላይ አብርሃም ላይ ሲከመሩ፣ እኔ ኮለኔልን ሳንቅ፣ ፖሊስ በቦታው ሲደርስ… ይሄ ሁሉ የሰከንዶች ክስተት ነበር።……
……… እሪታው አካባቢውን አመሰው። ፖሊሶቹ ሲገላግሉኝ እና ኮለኔልን አስረው ሲወስዷቸው በደመነፍስ አብርሽ ጋር ደረስኩ። እየጠበቀኝ የነበረ ይመስል እጄን ቀምቶ ወደራሱ አስጠጋኝ። « ልጄን… ልጄን… አማላይ… » ……ማለት የፈለገውን መጨረስ አልቻለም። የሰፈሩ ሰው ከመሬት አፋፍሰው አነሱት። አማላይ ነጠላዋ በአብርሃም ደም ተለውሶ ከላዩ ላይ አልነሳም ብላ ለሰፈርተኛው አታከተች።… እማዬ መሬቱ ላይ ደንዝዛለች……

……………

የደቂቃ ቅፅበት ነበር።… የበዓል ሁከት፣ ነጠላ የለበሱ ሴቶች፣ የጠላ ሽታ፣ የስቅለት ዕለት… ከአብርሽ ደም ጋር የተቦካ ትዝታ አለው።……

አማላይ ከሬሳ ሳጥኑ አጠገብ አልነሳም ብላ ለያዥ ለገናዥ አስቸገረች… ጋሼ የልጄ ገዳይ እሷ ናት ካልገደልኳት ብሎ ሁከት አስነሳ። እማዬም ለዓይኔ አልያት አለች። እኔስ? … እኔ ዞረብኝ።

«አስወጡልኝ ይህቺን ልጅ… ለልጄ በቅጡ ላልቅስለት አስወጡልኝ! » እማዬ እሪሪሪ አለች።

«ይግደሉኝ!… ይግደሉኝ እንጂ የትም አልሄድም! ይግደሉኝ ከፈለጉ… » አማላይ በሲቃ በተሰባበረ ቃላት ጋሼ ላይ አፈጠጠች። በጣም ጮክ ብላ ስለነበር ሁሉም ፀጥ አለ። ጋሼን ጨምሮ።……

የገደለ አባትሽ የሞተው ባልሽ (ክፍል ሶስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...