Tidarfelagi.com

የገቢዎች ነገር እና 40/60

በጥዋት አልጋዬ ውስጥ ሆኜ እየተብሰከሰኩ ነው። የቤት ኪራይ መክፈያዬ ደርሷል……ኤዲያ! ” መቼ ነው ግን የራሴ ቤት የሚኖረኝ?” ።ትላንት በጉጉት ስጠብቀው የነበረው የ40/60 እጣ እንደወጣ በዜና አይቻለሁ…እጣ ውስጥ የተካተቱት መጀመሪያውኑም መቶ ፐርሰንት የከፈሉ ብቻ እንደሆነም ተነግሯል……የወጣው እጣ አንድ ሺ እንኳን አይሞላም። መቶ ፐርሰንት የከፈሉ ገና ከአስር ሺ በላይ ሰዎች ይቀራሉ ። በተኛሁበት በአእምሮዬ የሚመላለሱ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው……
1ኛ…ቆይ ግን ይሄን ነገር መጀመሪያ ስንመዘገብ “በወር 2500 ብር እየቆጣባችሁ ከቆያችሁ እጣ ውስጥ ትገባላችሁ” ብለውንም አልነበር?
2ኛ…. ምዝገባው ሲጠናቀቅ 140 ሺ ናችሁ ብለውን አሁን ከየት መቶ ነው 170 ሺ ያለፍነው?
3ኛ..ያኔ ስንመዘገብ “ባለ አራት መኝታ” የሚባልስ ነበር እንዴ?!
5ኛ. እጣ የሚወጣው ለባለመቶ ፐርሰንት ከፋዮች ብቻ ከሆነ ለምን ስሙን 40/60 ይሉታል? መቶ ዜሮ ቢሉት አይሻልም?!
6ኛ.ቆይ ግን መንግስት እንደማይሰራ እያወቀ የዚህ ሁሉ ሰው ገንዘብ ሰብሰቦ በአራት አመት አንድ ሺ ብቻ ቤቶችን ከሰራ ለምን የአክሰስ ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተከሰሱ?አቦ ተዋቸዋ! ወይ ክሳቸው ይቋረጥ ወይ መንገስትም በተመሳሳይ ክስ ይከሰስ!እሳቸውስ ከዚህ የከፋ ነገር ምን አደረጉ ?!
7ኛ.ሚስቴን ግን በጥዋት ተነስታ የት ሄደች?
እሁዴን እማ እንዲህ ክፉ ክፉውን ውን እያሰብኩ አላበላሽም! ግን ደግሞ ተረጋግቼ ሳስበው (ትንሽ ጽንፈኛም ሆኜ ሳሰላው)….እንደ ድንገት የመጨረሻው እጣ እንኳን ቢወጣልኝ(እቁብ እንኳ ሁሌም መጨረሻ ነው የሚወጣልኝ)….መቼ ነው የሚደርሰኝ?…….. ባለፉት አራት አመታት 1000 ቤት ከተሰራ በዚሁ ስሌት እኔ የሚደርሰኝ
X=the number of years that the government takes to build one house
Y=individuals registered for 40/60
4X=1000houses
X=1000hoses/4=250houses
173000=the number of people waiting
17300/250=the number of years that is needed to finish the last house =692years

ይሁና! 692 አመት ምን አላት?!…..እዚህች ችስታ ሀገር ስትኖሩ “ፖዘቲቭ ቲንኪንግ” ያስፈልጋል።ማድረግ ያለብኝ ኢሃዲግን ማማረር ሳይሆን ቁጠባዬን በአግባቡ እየቖጠብኩ አምላኬ የማቱሳላን እድሜ እንዲሰጠኝ ብቻ መለመን ነው። ምናልባት አምላክ ልመናዬን የማይሰማ ቢሆን እና የማቱሳላን እድሜ ቢነፍገኝ እንኳን እጣው በሚወጣበት ሰአት ለወራሾቼ ስለሚተላለፍ በታሪክ “የመጀመሪያው ለልጅ ልጅ ልጅ.ልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ልጁ” የወደፊት ኑሮ በማሰብ ገንዘብ የቆጠበ አስተዋይ ሰው በሚል ወደፊት ጊነስ ቡክ ላይ ስሜ ይሰፍራል ማለት ነው።

እንደውም በዚሁ ፖዘቲቭ ቲንኪንግ በመነቃቃት መንግስት ያለፉትን አራት አመታት አንድ ሺ ቤት ቢሰራም ትላንት የመንግስት ተወካይ “በቅርቡ የሚጠናቀቁ 20 ሺ ቤቶቸ አሉ” ስላሉ እና በሚቀጥለው አመት ይጠናቀቃሉ በሚል ሌላ ፖዘቲቭ ቲንኪንግ መንግስት በየአምስት አመቱ 21 ሺ ቤት ነው የሚሰራው ልበል……በላይኛው ስሌት መሰረት 173ሺኛው ቤት የሚጠናቀቀው ከ34 አመታት በኋላ ነው ማለት ነው፡አንዲ ማኛ በ2043 ዓ.ም የቤት ባለቤት ሆነች ማለት አይደለም!? ይሁና ! በ70 አመቴ ሜቄዶንያ ካልገባሁ ብዬ እነ ቢንያምን ከማስቸግር ቢዘገይም የራሴ ቤት መግባቴም ጥሩ ነው። አረ እንደውም በጣም ፖዘቲቭ ቲንኪንግ መጣልኝ!…..እንደውም መንግስት በየአመቱ አስር አስር ሺ ቤት እየሰራ ይቀጥላል ብዬ ልመን….ፓ!..በዚህ ስሌት የመጨረሻው ቤት ከ17 አመት በኋላ ተሰርቶ ያልቃል ማለት ነው።በለው! አንዲ ማኛ በቅርቡ ማለትም በ2027 ዓ.ም ባለሶስት መኝታ ቤቷን በእጇ አስገባቻ!…..17 አመት ምን አላት??! የደርግስ 17 አመት አልፎ የለ……! ትንሽ ግን ችግር አለ!..ባለሶስት መኝታ የተመዘገብኩት አንዱን መኝታ ለእኔና ለሚስቴ አንደኛውን ለዋኑፊ አንደኛውን ለቤቢሹ ብዬ ነበር……ቤቱ ሲደርሰኝ ዋኑፊና ቤቢሹ ወይ ኮሌጅ ወይ ስራ ስለሚሆኑ ልፋቴ ከንቱ ነው የሚቀረው! ….ኤዲያ !
ከአልጋዬ ዘልዬ ወጣሁ!በመስታወት ፊቴን አየት አደረኩት …ጺሜ አድጓል…..ወደ “ሚሊየነሩ” ጸጉር አስተካካይ ደንበኛዬ ካስሽ ጋር ደወልኩ።”አንድ ሰው ብቻ ነው የሚቀድምህ ሌላ ወረፋ የለም “ሲለኝ ሄድኩ።አንድ ሼባ እያስተካከለ ስለደረስኩ ወረፋዬ እስከሚደርስ ከጸጉር ቤቱ ፊት ያለችው ሌላዋ “ሚሊየነር” የጀበና ቡና ሻጭ ጋር ቡና አዝዤ ቁጭ አልኩ።እነኚህ ሁለት ምንዱባኖች ሰሞኑን የገቢዎች ባስስልጣን “እለታዊ ገቢያቹ ነው”ብሎ ባሳወቃቸው መርዶ ቆሌ ርቋቸው አሬራ እንደጠጣ በግ ፈዘዋል። ….ለጸጉር ተስተካካዮች ዘወትር ፍልቅልቅ እያለች ቡና ታመጣልን የነበረችው “ዜድ” (ዘውዲቱ ነው ስሟ እኛ ግን “ዜድ” ነው የምንላት)፡ ለወትሮ በገባች በወጣች ቁጥር ከካስሽ ጋር በመነቋቆር እንዳላዝናናችን ዛሬ አንድም ቃል ሳትናገር እንደ ቀብር አስፈጻሚ ኩስትርትር ብላ ቡናውን ፊት ለፊቴ አስቀመጠች……
“ደረጃ ለ “መሆን እኮ ይሄን ያል ከባድ አይደለም ዜድ! ባይሆን ዜድ ሪፖርት ብታወጪ ነው አልኩ!”። ማንም አልሳቀልኝም።
….”በቀን የአርባ ሰው ጸጉር ታስተካክላለህ” ተብሎ በገቢዎች የተፈረደበት ካስሽም ድሮ የባጥ የቆጡን እያወራ “አረ ካስሽ ቸኩያለሁ” እያልነው እንኳን ከአንድሰአት በላይ ሲያሽሞነሙነን እንዳልነበረ አሁን የገቢዎችን ቁጥር ለመሙላት ነው መሰል በፊት ቅርጽ ለማውጣት ብቻ ከሚፈጅበት ደቂቃ ባነሰ ሙሉ ጸጉር አስተካክዬ ጨረስኩ ብሎ ገዋኑን እያራገበ “ተረኛ ግባ!” አለ። ሲያስተካክላቸው የነበሩት ሼባ ከሽበታቸው እና በቅጽበት በተካሄደባቸው የግብር ይውጣ አጨዳ ጋር ተዳማምሮ አናታቸው የአሜሪካን መጤ ተምች የጎበኘው የበቆሎ ማሳ መስሏል።
“…ተረኛ ግባ እንጂ ሰአቴን አትፍጅ!” አለ…ደንበኝነታችን ከጀመረበት ቀን አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ “ተረኛ” ብሎ ሲጠራኝ! ….”እኔን ተረኛ!?”…… ከፋኝ …ቆይ እኔ አይደለሁ የቀን ገቢህ 2000 ብር ነው ያልኩት!
“ጸጉር ነው ጺም !?”አለ በቁጣ ።ጸጉሬንም መስተካከል ፈልጌ የነበረ ቢሆንም …..ከኔ በፊት ባየሁት አስከፊ አጨዳ መነሻ በፍርሃት “ጺም “አልኩኝ… ምላጭ አነሳሱ እራሱ ያስፈራል…..
“.ቆይ ግን እነኚህ ሰዎች ግን አብደዋል እንዴ! ሆሆይ….ቆይ በምን ተአምር ነው በቀን 40 ሰው ታስተካክላለህ የሚሉኝ!?” አለ…በመስታወት አየት ሳደርገው ለእኔ ያውራ ለራሱ ያውራ ግራ አጋቢ ነው ….የሰሞኑ የነጋዴ ሙድ ስለሆነ..ዝም አልኩኝ….
“እንደ ሰይፉ ፋንታሁን አይነት መላጣዎችን እንኳን በቀን 20 ማስተካከል ይቻላል እንዴ?!” አለ ድጋሚ።አሁንም ቀና ብዬ በመስታወት ሳየው ከራሱ ጋር ያውራ ከእኔ ጋር ግልጽ አይደለም ….
“ለምን በቀጥታ ሄደህ አዲሱ የገቢዎች ሃላፊ የሆኑትን አቶ ከበደ ጫኔን አታናግራቸውም!?” ልለው አሰብኩና ትዝ ሲሉኝ ዳይሬክተሩ ሙሉ መላጣ ናቸው……እሳቸው ጸጉር ቤት የሚፈጅባቸውን ግዜ ካሰቡት እንደውም 80 ሰው ሊያስደርጉበትም ይችላሉ።ዝም አልኩ።ገና ተስተካክዬ መቀመጤም ሳይታወቀኝ “ጨርሰሃል!” አለኝ።በፍርሃት ፊቴን በመስታወት አየት አደረኩ….ሳያማክረኝ የአፍንጫዬን ጺም(ሙስታሸ) አስቀርቶ ቻርሊቻፐሊንን መስያለው።በዚህ ሙዱ መናገር ስለማይቻል…ዋናውን ሂሳቤን ከፍዬ እንደተለመደው ካስሽ “የቀን ገቢ” ብሎ ለገቢዎች ያስታወቃትን “አስራአምስት ብር” በቲፕነት ጨምሬ አመስግኜ ወጣሁ…..።
እናንተ ግን……
ይመቻችሁ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...