Tidarfelagi.com

‹‹የድሬ ሰው ነፍሴ››

 

የሚያንገረግበውን የድሬ ሙቀት መብረድ ጠብቄ አመሻሹን ሻይ ልጠጣና በእግሬ ወዲህ ወዲያ ልል ከሆቴሌ ወጣሁ። 
ለብ ባለው ንፋስ እየተደሰትኩ፣ ቱር ቱር በሚሉት ባጃጆች ካለጊዘዬ ላለመቀጨት እየተጠነቀቅኩ ከተዘዋወርኩ በኋላ ለሻይ አንዲት ትንሽ ቤት ቁጭ አልኩና ምን ይምጣልሽ ስባል ‹‹ቀጭን ሻይ›› ብዬ አዘዝኩ።

ቀልጣፋው አስተናጋጅ ደቂቃ ሳይሞላ ሻዬን አመጣልኝ።
ምን ያደርጋል….? የብርጭቆው ግማሽ በቀጭን ሻይ፣ ግማሹ ደግሞ በስኳር ክምር ተሞልቷል። እኔ ደግሞ ሻይ በስኳር ከጠጣሁ አመታት ተቆጥረዋል።

‹‹….ውይ….›› አልኩኝ እንዳየሁት።
‹‹ምነው?›› አለ ልጁ ሻዩን አተኩሮ እየተመለከተ። በረሮ ወይ ሌላ ነፍሳት ያገኘሁበት መስሎት ሳይደነግጥ አልቀረም።
‹‹ስኳር አልፈልግም ነበር…አባቴ›› አልኩኝ ፈራ ተባ ብዬ።
‹‹እ?››
‹‹ያለ ስኳር ነው ምጠጣው››
‹‹ምን ? ሻይ?››
‹‹አዎ…ባዶ ሻይ ነው ምጠጣው››

ግራ በመጋባት አየኝ።
‹‹ምነው ?›› አልኩት ዝም ብሎ ሲያየኝ።
‹‹ሻይ ለስኳር እንጂ ለምን ይጠጣል…? ከየት ነው የመጣሽው?››

ከት ብዬ ሳቅኩ።

የምሩን ነው ለካ!
‹‹ካዲሳባ ነው…ባዶ ሻይ አታመጣልኝም? ለዚኛውም እከፍላለሁ…››

ምናይነቷ ንክ ናት በሚል አየኝና ሻዩን ይዞ ሄደ። ብዙ ሳይቆይ ሌላ ቀጭን ሻይ፣ አሁን ግን አለስኳር አመጣልኝ።

ጠጥቼ ስጨርስ የሁለት ሻይ ሂሳብ ልከፍል ተዘጋጅቼ ሂሳብ ጠየቅኩ።

‹‹እንዴ! ለምን ላስከፍልሽ? ባለስኳር አልጠጣም አልሽ…ባዶ ሻይ ጠጥተሸ…ለሙቅ ውሃ ላስከፍልሽ እንዴ? ›› አለኝ።

በደግነቱ አፈርኩና ‹‹ግን እኮ አንተ አላጠፋህም…እኔ መንገር ነበረብኝ…ስኳር አልፈልግም ብዬ››
‹‹ብትይስ ኖሮ! ለሙቅ ውሃ አናስከፍልም አልኩሽ እኮ!›› አለ ጣደፍ ብሎ።
‹‹እና ዝም ብዬ ልሂድ?›› አልኩ ሃፍረቴ እየናረ።
‹‹ ውይ….! በቃ ከደበረሽ ነገ ነይና ቁርስ ምናምን ብዩ..አሪፍ ፈጢራ ምናምን አለ ›› ብሎኝ፣ መጨናነቄን ከቁብ ሳይቆጥረው ሲጠሩት የነበሩ ሌሎች ተስተናጋጆች ጋር ሄደ።

የዋሁ የድሬ ሰው፣ ጣጣ ፈንጣጣ የማታውቀው የድሬ ሰው! ደስታህን እንጂ ክፉህን አያሰማኝ!

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...