Tidarfelagi.com

‹‹የዞረ ድምር››

(መነሻ ሃሳብ- ሴክስ ኤንድ ዘ ሲቲ ተከታታይ ፊልም)

ደንበኛ ፍቅር በጀመርን በአራተኛው ሳምንት ይመስለኛል፣ በሰበብ ባስባቡ ሲያከላክለኝ ቆይቶ በመጨረሻ ቤቱ ይዞኝ ሄደ።

– የወንደ ላጤ ቤት ነው እንግዲህ…ያልተነጠፈ አልጋ አየሁ፣ ያልታጠበ ካልሲ ሸተተኝ ምናምን ብለሽ እንዳትተርቢኝ አለ እጄን ይዞ የአፓርትማውን ደረጃ ስንወጣ።
– አዬ…እሱማ የሚጠበቅ ነው። ያው እንደፈረደብን ገብተን ማፅዳት ነው እንግዲህ…ወንድ ልጅ ፍቅረኛ የሚይዘው ወይ የሚያገባው በሰራተኛ መኖር ሲሰለቸው ነው ምናምን እያላችሁ ትቀልዱብን የለ…አልኩት እጁን ከእሱ በላይ ጥብቅ አድርጌ እየያዝኩ።

ሳቀና ዝም ብለን ደረጃውን መውጣት ጀመርን። ሶስተኛ ፎቅ ላይ ስንደርስ ወፍራም ጭኖቼ እርስ በርስ እየተፋተጉ ሰላም ነሱኝ። ትንፋሼ ተቆራረጠ። ሆዴን ቁርጠት ብጤ ሲጀማምረኝ እጁን ለቅቄ አለከለክኩና ፤
– ወይኔ….! ቦርጭ የሚባል ነገር ለምን እንደሌለህ አሁን ገና ገባኝ…ውይ…በየቀኑ ይሄን ስትወጣ አይመርህም? አልኩ።
– ይለመዳል…አየሽ ለዚህ ብላ ነው እሷም አራተኛ ፎቅ ቤት ያስገዛችኝ….ነይ ይልቅ አሁን…አንድ እኮ ነው የቀረን….አለና እጄን ይዞ ሰውነቴን እንደመጎተት ጀመረ።

ከየት መጣ በማልለው አኳሃን ድካሜ በኖ ጠፍቶ በብስጭት መተካቱን ሳያውቅ ይጎትተኝ ጀመር።

ምን አበሳጨኝ?

‹‹ለዚህ ብላ ነው እሷም አራተኛ ፎቅ ቤት ያስገዛችኝ›› ብሎ ዛሬም፣ ከተዋወቅኩት ጀምሮ እንደሚያደርገው በቀን አስር ጊዜ ስሟን ለማንሳት ሲንደረደር፣ በሌለችበት የቀናችን አካል፣ ባልዋለችበት የውሏችን አጃቢ ሊያደርጋት መሞከሩን ሳውቅ ነው የተበሳጨሁት።
‹‹እሷ›› ከሶሰት አመት የጋለ ፍቅር በኋላ ከመንፈቅ በፊት ‹‹የተለያት›› የ‹‹ቀድሞ›› ፍቅረኛው ናት። ‹‹የተለያት›› እና ‹‹የቀድሞ›› የሚሉትን ቃላት በጥርጣሬ የምጠቀማቸው በቂ ምክንያት ስላለኝ ነው።
ከተዋወቅኩት ጀምሮ እንደ ጥላ ተለይታው አታውቅም። በአካል አይደለም። ከአፉ የማትነጠል መንፈስ ናት። በደም ስሩ የተሰራጨች በሽታ ናት።

ሲጀምር….፣ ያለ ከልላይ አንጎሉ ውስጥ ስለምትመላለስ ስሟ በየሰአቱ ከአፉ ዱብ ይላል።
የመጀመሪያ ሰሞን ሲያነሳት በጥሩ ነገር ስለማያነሳት የሚያሳስበኝ ነገር ያለ አልመሰለኝም ነበርና ረገብ ብዬ ነበርኩ። በፍቅር ካላነሳት፣ በጥላቻ ከጠቀሳት ምን ቸገረኝ? አይውደዳት እንጂ ከጠላት ምን አስጨንቆኝ? እያደር ግን የከረረ ጥላቻ ከከረረ ፍቅር የሚቀዳ ስሜት መሆኑን እየተረዳሁ ስመጣ ይከነክነኝ ጀመር። ጥላቻም እኮ ስሜት ነው…ከመንፈቅ በላይ ለተለያት ሴት ምንስ አይነት ስሜት ቢሰማው የኔን ቦታ ይዛለች እና ልረበሽ አይገባም?

– ቤላ ብትሆን እንዲህ ላላት ሰው ረጋ ብላ መልስ አትሰጥም ነበር። ትሰድበው ነበር….
– ቤላ ብትሆን ለአስተናጋጅ ይሄን ያህል ቲፕ አትተውም
– ይሄ የእባብ ቆዳ የሚመስል አስጠሊታ ልብስ ሲቀፈኝ! እንደዚህ አይነት ልብስ ማን እንደሚወድ ታውቂያለሽ? ቤላ!

እያለ ስሟን በየአረፍተነገሩ ይሰነቅራል። በየወሬው ይከተዋል። በየቦታው ይበትነዋል። ለሄደ ሰው የማይሰጥ ቦታ ይሰጣታል። የጠላት መስሎ ስሟን ከስሜት ማማ ላይ ይሰቅላል። ያነሳታል። ብዙ ጊዜ ያነሳታል።

ሲቀጥል…፣ በማናቸውንም ነገር ከእሷ ጋር ያነፃፅረኛል። ያወዳድረኛል። በእሷ ልክ ይለካኛል።

ሊያሞግሰኝ ሲፈልግ እንኳን ለብቻዬ አያሞግሰኝም። ለብቻዬ አያቆመኝም። እሷን አስደግፎ ያየኛል። እሷን ያጣጣለ መስሎ አጣምሮ ያነሳናል። ያነፃፅረናል። ያወዳድረናል።
ለምሳሌ ..
– ፐ! ቢራ ትጠጪያለሽ? ደስ ስትይ! ቤላ ቢራ አትወድም ነበር….በስፕራይት እንኳን እየዘገነናት ነው የምትጠጣው…እያለ…
ለምሳሌ…
– ክትክት ፊልም ስለምትወጂ እንዴት ደስ እንደምትይኝ! የሆንሽ ባድ አስ ነገር እኮ ነሽ! ቤላ እኮ ሁለት ሰዎች ቦክስ ከጀመሩ ሮጣ ጉያዬ ውስጥ ነው የምትገባው…ስስ ነገር ናት… እያለ…

እንደ ገና ሲቀጥል፣ ከሙሉ ቤተሰቧ ጋር አሁንም ይደዋወላል። ይገናኛል።
የት ነበርክ ማታ ? ስልክ ብደውል አታነሳም ስለው
– ኦ…ማታ ከሚኪ…ከቤላ ወንድም ጋር ክዊን ኦፍ ሼባ ሄደን ኳስ እያየን ነበር ይለኛል።
ነገ ምሳ እንብላ ስለው
– ውይ…ነገ ቀብር መሄድ አለብኝ። የቤላ የአክስት ልጅ ሞተ እኮ ይለኛል።
የወደፊት ቤተሰቦቹ እንደሆኑ ሁሉ ተንከባክቦ ሊያቆያቸው የሚፈልግ ይመስል በየቀኑ ይደውልላቸዋል። ለቅሶ ይደርሳል። ሰርግ ይታደማል። ልደት ይሄዳል። የፌስቡክ ፎቷቸው ላይ በላይክ ያሽቋልጣል።

አንዱን ቀን የቤላ እህት ልጅን ልደት (ያውም የሶስት አመት ልጅ ልደት) እሄዳለሁ ብሎ ሲነሳ ግልፍ አለኝና
– አንተ ግን አይደብርህም እንዴ…ከኤክስህ ቤተሰብ ጋር እንዲህ መቀራረብ አግባብ ነው? አልኩት
የገዛውን ስጦታ መጠቅለሉን ቆም አደረገና፣
– እኔ እና እሷ ብንለያይ ከጥሩ ሰዎች ጋር መቆራረጥ አለብኝ? ሲቪል ሁኚ እንጂ..ይሄ የድንጋይ ዘመን አይደለም አለኝ።

በድንጋይ መውገር ነበር።.

ለሁሉም በስንት ጉትጎታ በሰበብ ባስባቡ ሲያከላክለኝ ቆይቶ በመጨረሻ ቤቱ ይዞኝ መጥቷል። ብስጭቴን ዋጥ፣ ድካሜን ቻል አድርጌ የአፓርተመንቱን በር እስኪከፍት ቆሜ አየዋለሁ።

ተከፈተ።
ወይ የወንደላጤ ቤት!

ሚስት የቀረው የሞቀ ባለትዳር ቤት ነው የሚመስለው። ሁሉ ነገር በአግባቡ የተሰደረ፣ በስርአቱ የኔን የሴቷን ቤት የሚያሸማቅቅ ሙሉ እና ምቾት በሚነሳ መልኩ ፅድት ያለ ውብ ቤት ነው።

-በስመአም አንተ!…እንዴት የሚያምር ቤት ነው ያለህ ! አልኩ በሩጫ ቀረሽ እርምጃ ሁሉንም ክፍል በወፍ በረር እያየሁ። ከሳሎን ትልቁ መኝታቤት፣ ከትልቁ መኝታቤት ወደ ትንሹ መኝታ ቤት፣ ከትንሹ መኝታ ቤት ወደ መታጠቢያ ቤት፣ ከመታጠቢያ ቤት ወደ ኩሽናው እየገባሁ።

ኩሽናው!
ምግብ ሊሰራባቸው ቀርቶ ከተሰቀሉበት ወርደው የማያውቁ የሚመስሉ ድስቶችና መጥበሻዎች (በቅርፅና በስፋት የተለያዩ) ግድግዳ ላይ በማራኪ መልኩ ተሰቅለዋል። እነ ሻይ ማጥለያ እና ማማሰያ እና የስለት ደረጃቸው የሚለያዩ ቢላዎች (የቱ ወንደላጤ ነው ሻይ ማጥለያ አስታውሶ የሚገዛ ገዝቶም በስርአት የሚያስቀምጥ?) ከስቶቩ አጠገብ በተዘጋጀ ሰፊ ሰሃን መሰል ብርጭቆ ውስጥ ተቀምጠዋል። አጠገባቸው የዳቦ መጥበሻ ማሺን (ቶስተር) እና የኤኬክትሪክ ውሃ ማፍያ ጀበና በወጉ ተቀምጠዋል። ዳቦና ፍራፍሬ የያዙ የሳጠራ ሰሃኖች ከእነሱ አጠገብ ይታዩኛል።

ህም!

– አረ ሳሎን ነይና ቁጭ በይ…አለኝ ኩሽና ውስጥ ፈዝዤ ቆሜ እንደቀረሁ

አፌን ዝገት ዝገትና ቤላ ቤላ እያለኝ ወደ ሳሎን ተመለስኩና አንዱ ሶፋ ላይ ዝርፍጥ ብዬ ተቀመጥኩ።

– ወደድሽው? አለኝ አጠገቤ ካለው ሶፋ ላይ ቁጭ እያለ
– እህ…አልኩ
– ምንድነው እህ? አለኝ
– አይ…ከጠበቅኩት በላይ ነው…ማለቴ የተደራጀ ቤት ነው…ምንም የወንድ ቤት አይመስልም….አረ የሴትም አይመስልም…ገርሞኛል….አልኩ በተቀመጥኩበት እየተቅበጠበጥኩ
– ሃ…ታዲያ አሪፍ አይደል መደራጀቴ…? ስራሽን አያቀለውም እንዴ ?

ዝም አልኩትና ቴሌቪዥን የተሰቀለበትን ግድግዳ ማየት ጀመርኩ። ከስንት አይነትና ከምን ቀለሞች ድብልቅ እንደተሰራ ሊገባኝ ባይችልም ውብና ቀዝቃዛ ግራጫ ነው። የሚያምር የእራት ቀሚስ ሊሆን የሚችል ውብ ቀለም።

– ምንድነው የምታዩው? አለኝ
– የግድግዳውን ቀለም…በጣም ያምራል…በጣም ዩኒክ ነው…
– እ…..አዎ…ግን ለሱ ክሬዲት መውሰድ አልችልም….አለ ከሶፋው ላይ እየተነሳ…
– እ? ለምን?
– ቤላ ናት የመረጠችው…ሻይ ላፍላልሽ ቆይ….

እሱ በሻይ ላፍላልሽ ሰበብ ወደ ኩሽና ሲያመልጥ በተቀመጥኩበት ብርድ ብርድ ይለኝ ጀመር። ይህች ሴትዮ ለምን አትተወኝም?

ተነስቼ ወደ ኩሽና ሄድኩኝ።

በኤሌክትሪክ የሻይ ማፍያው ውስጥ ውሃ ሲሞላ ደረስኩ።

– እኔ ምልህ…?
– እ….
– ይሄን ቤት ያስገዛችኝ ቤላ ናት ብለኸኝ ነበር…
– እ? አዎ….(ሶኬቱን እየሰካ)
– አሁን ደግሞ ቀለሙም እሷ ናት የመረጠችው አልከኝ…
– አዎ…ምነው…? (ወደ እኔ እየዞረ)
– ምነው? ሁሉም ነገርህ ነበረች መሰለኝ…ይሄን ቤት ያሟላችው እሷ ናት አይደል…የወንድ ቴስት አይመስልም….
– ቤቲዬ፣ ሶስት አመት አብረን ነበርን….አሁን ግን አልፏል….እንቁላል ልጥበስልሽ?

አንጀቴን በጥሶ እየጠበሰ እንቁላል ልጥበስልሽ ይለኛል?
አልፏል ነው ያለው? እሷ ያስገዛቸው ቤት ውስጥ እየተንጎራደድኩ፣ እሷ በመረጠችው ጀበና ሻይ እያስፈላሁ፣ እሷ ባሰናዳቸው ሕይወት ውስጥ እየተመላለስኩ አልፏል?

– አልፈልግም…አልራበኝም….

ሻዩን ጠጥተን በግድ እራት ካበላኝና አባብሎ ካሳመነኝ በኋላ ለማደር ተስማማሁ።

ለፍቅር ድግስ እርቃኔን አልጋ ውስጥ ገብቼ በአንሶላው ልስላሴ እየተደመምኩ (ቤላ ከየት ይሆን የገዛቸው በሚል ከፍተኛ የቅናት ስሜት ስገዘገዝ) ፣ ገላውን ታጥቦ ከቤቱም ከእሱም ጋር የማይሄድ ሰውነቱን ውጥርጥር አድርጎ የያዘ፣ እጅጌውና አንገቴው የተበላ ቢጃማ አድርጎ ወደ አልጋ መጣ።
– ምንድነው የለበስከው..?አልኩት ኮስተር ብዬ
– ቢጃማ ነዋ….!
– ቢጃማ መሆኑንማ አይን አለኝ አያለሁ..ቴዲዬ በጣም ጠቦሃል እኮ…በዛ ላይ ተበልቷል…
– አልጠበበኝም ይልቅ እንተኛ….ናፍቀሽኛል…እ?
– እንዴ…እያየሁት..አጣብቆሃል እኮ …በዛ ላይ ምንድነው ያ ደረትህ ላይ ያለው ፅሁፍ? .እንዴት ይሄን ለብሰህ ትተኛለህ…የህፃንነትህ ነበር እንዴ? ሃሃሃሃ….
– ኡፍ ቤቲ ደግሞ! ሁሉ ነገር ላይ አስተያየት መስጠት አለብሽ…ቤቴ አይደለም? የፈለግኩትን መልበስ አልችልም?

አረ ቁጣ!

– ጠቦሃል እንዴት ይመችሃል ብዬ ነው…ምነው ትልቅ ነገር አደረገከው?
– አንቺ ነሽ ትንሹን ነገር ትልቅ ማድረግ የምትወጂ…
– እንዴት?
– ኡፍ በናትሽ ጭቅጭቅ ጠላሁ….መተኛት እንችላለን?

ብስጭትጭት እያለ አልጋ ውስጥ ለመግባት ሲመጣ ጥብቆ ቢጃማው ላይ ያለውን ፅሁፍ ማንበብ ቻልኩ።

‹‹ቤስት ቦይፍሬንድ ኢን ዘ ወርልድ›› ይላል።

በሞቀ አልጋ ውስጥ ያለው ሰውነቴ በረዶ የተጋገረበት ያህል መንዘፍዘፍ ጀመረ። ክፉኛ መንቀጥቀጥ ጀመርኩ። የቤላ የቅንጦት ኮምፈርት ሊያሞቀኝ ሲገባ ይበልጥ አስበረደኝ።
– እንዴ ቤቲዬ ምን ሆንሽ…በጣም ቀዘቀዝሽ እኮ….! አለኝ ደንግጦ እያቀፈኝ…
– አልችልም ቴዲ…
– ምን ሆነሽ ነው…የበላሽው ነገር አልተስማማሽም? አለርጂ ነው? ወይኔ አረ በጣም ትቀዘቅዣለሽ ምን ጉድ ነው…ነይ እስቲ እቀፊኝ…

ከአልጋው ተስፈንጥሬ ወጣሁ።

– እንዴ ምን ሆነሽ ነው….ይበልጥ ይበርድሻል…. አለኝ ተነስቶ ሊያቅፈኝ እየሞከረ።
– አትቀፈኝ….አልኩና በፍጥነት ልብሶቼን መልበስ ጀመርኩ
– እንዴ! ምን ሆነሻል..ለምንድነው ልብስ የምትለብሺው….
– ልሄድ….
– ወዴት?
– ወደ ቤቴ ነዋ! እኔም ቤት አለኝ እኮ!
– ለምን? ደሞ በዚህ ሰአት? አራት ሰአት አልፏል እኮ!
– ይለፋ…!

ጫማዬን ፍለጋ ወደ ሳሎን ሄድኩ።

ተከተለኝ።
– ምን ሆነሻል?
– እኔ ተደራቢ ሴት መሆን አልፈልግም ገባህ….?
– ተደራቢ ምን? ምንድነው የምታወሪው?
– ክብር ያለኝ ሴት ነኝ… ውሽማ አልሆንም…

ጫማዬን በማይታመን ፍጥነት አድርጌ ቆም ብዬ አየሁት።
ፍፁም ግራ የተጋባ ይመስላል።
– አልገባህም እውነት? አልኩት ትንሽ ረገብ ብዬ
– ምኑ…ምንድነው? ለምን አትነግሪኝም…?
– ና…!

ሶፋው ጋር ጎትቼ ወስጄው ተቀመጥን።
– ቴዲ..
– ወይ….
– የለበስከው ቢጃማ…ቤላ ናት የሰጠችህ አይደል?

አንገቱን ደፍቶ ዝም አለ።
– ናት አይደል? አገጩን ይዤ አንገቱን በቀኝ እጄ ከፍ አደረግኩት።
ዝም አለ።
– ቴዲ…
– ወይ ቤቲ…
– የቤላ ነገር ያለቀ አይመስለኝም..አልፏል ብትልም ሁሌ ስለእሷ ታወራለህ…ቤትህ ሁሉ እሷ ናት…ከቤተሰቧ ጋር ትቀራረባለህ…ይባስ ብለህ እሷ ስለሰጠችህ የጠበበህን ልብስ ..ያውም ከኔ ጋር ለብሰህ ማደር ትፈልጋለህ። ተሳሳትኩ?

ዝም አለ።

ተነሳሁ።
በሩ ጋር ደረስኩ።
– ቤቲ…. አለኝ…
ዞር አልኩ። ከሶፋው ጋር የተሰፋ ይመስል ግኡዝ አካል፣ ከቤቱ እቃዎች አንዱን መስሎ ተቀምጧል።
– ጠራኸኝ? አልኩት በቆምኩበት እያየሁት…
– አዎ…..ሳይንቀሳቀስ መለሰ።
– እ….? አልኩ
– ረጅም ጊዜ አብረን ነበርን…ግን አሁን አልፏል….ጥለሽኝ አትሂጂ…እወድሻለሁ….

አሳዘነኝ። በጥሶ የጠበሰው አንጀቴ ተንሰፈሰፈ።

– ቤቲ…በናትሽ ጥለሽኝ አትሂጂ….

ሄጄ አቀፍኩት።
በፍጥነት አንገቴን ይስመኝ ጀመር።
-የምትፈልጊውን ነገር ሁሉ እንቀይራለን…ጥለሸኝ አትሂጂ ….እያለ ግንባሬን፣ አንገቴን፣ ከንፈሬን በፍጥነት እየሳመኝ ያንሾካሹክ ጀመር።

ሁሉን ነገር እናስተካክለን….ጥለሸኝ አትሂጂ…ይላል ….፣ ሹራቤን እያወለቀ…ጉርድ ቀሚሴን ወደ ታች እያንሸራተተ…..ቀኝ እጁን ጭኖቼ መሃል እየሰደደ…

ጥለሽኝ አትሂጂ…እ..እወደሻለሁ….ይላል ፣ በስሜት የጋለ ራቁት ገላዬን ሶፋው ላይ አጋድሞ እየሳመ…ጡቶቼን በከንፈሩ እየመጠመጠ….ሴትነቴን በወንድነቱ እየከደነ….በግማሽ ጆሮ፣ በተከፈለ ልብ የምሰማውን ወሬ እየቀጠለ…

እወድሻለሁ ቤላ……ጥለሽኝ አትሂጂ….ቤላዬ…እወደሻለሁ….

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • zerihuntemesgen12@yahoo.com'
    zerihun temesgen commented on August 16, 2018 Reply

    hewiye betam arif arif tsihufochin titsifyalesh!!yimechugnal plus demo betam nw yemiwodish!!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...