Tidarfelagi.com

የዘውግ ፖለቲካ እንደ ሀገር?

ወደ 25 ሀገሮች ፌደራሊዝምን ይከተላሉ ይላል አሰፋ ፍስሃ ስለ ፌደራሊዝም በፃፈው መፅሐፍ። ያዋጣቸውን አዋጥቷቸው ይሆናል። የኛ ግን የቆመበት መሰረት በራሱ «ፀብ ለሚሹ የሜዳ ጠረጋ» ስለሆነ አልተሳካም ብንል አያኳርፍም።

የዘውግ ፖለቲካ አያዋጣም ሲባል እንዲሁ ሳስበው ደስ አይለኝም ከሚል የሚሻገር ሰበብ አለው። ከሚያፀድቀው የሚያደቀው ይበልጣል።

የመጀመሪያው ነጥብ ዴሞክራሲ ነው። በዘውግ ፖለቲካ መስኮት ብቅ የሚል ዴሞክራሲ የለም። የዘውግ ፖለቲካ ለአቅም ሳይሆን ለራስ ወገን ተብሎ ለሚታሰበው ነው ቅርበቱ። የእኛ ተራ ነው በሚል የፈረቃ ስሜት ትልልቅ ተቋማትን መቆጣጠር ላይ ይለፋል።
Eva Poluha የተባለች ሴት «Ethnicity and Democracy: A viable alliance?» የሚል መፅሐፍ አላት አሉ። መፅሐፉን የማግኘት እድል ባይኖረኝም፣ «ዴሞክራሲ እና የዘውግ ፖለቲካ አብረው አይሄዱም» ማለቷን የተለያዩ ቦታዎች ሲጠቀሱላት አይቻለሁ። በራሷ ቋንቋ ይሄው፤
«it is impossible for Ethiopia to pursue ethnification process and to promote democracy at the same time»

ጥያቄ የሌለው ነጥብ ነው። ከዘውግ ፖለቲካ ዴሞክራሲን መጠበቅ፣ የበሬው ቆለጥ ይወድቅልኛል ብሎ ሲከተል እንደዋለው ቀበሮ መሆኑ ነው።

ከላይ እስከ ታች ያሉ መዋቅሮችን በራስ ሰው የመሙላት፣ ሌላውን የመግፋት ሂደት ፖለቲካዊ ፅድቅ ተደርጎ ይወሰዳል። የኛ ሰው እና የእነሱ በሚል መሀል የራስን ለመሳብ ሌላውን ለመግፋት ልክ እንደ አዲስ አበባ ቻርተር ያሉ የህግ ለውጦችን እስከማድረግ ነውር ሳይጎረብጥ ይከወንበታል። ዘመድን መሰብሰብ ስልጣንን የማስጠበቅ ተግባር አንድ አካል ስለሆነ ነውርነቱ ይረሳል።

ይሄ በተራው ኤኮኖሚያዊ ውጤት አለው። ሰዎች በአቅማቸው ሳይሆን በብሔራቸው የሚዘውሩት ስርዓት ለዘረፋ ቅርብ ነው። kleptocracy ይዘረጋበታል!

ብቃት ያላቸው ሰዎች ከጥሩ የስራ ዘርፎች ይገፋሉ። ሌስ ፕሮዳክቲቭ በሆኑ ሰዎች ቦታዎች ይገጠገጣሉ። ከዛ በታች ባሉ ዜጎች ላይ የስሜት ጉዳት እና የሀገር አልባነት ስሜት ይጭናል። ብዙ ለጋሚ ይፈጠራል፤ የጋራ ዓላማ ይጠፋል።

ከዚህም በላይ ቀልጣፋ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት እንዳይኖር ያደርጋል። ደካማ ብሔራዊ ስሜት፣ ደካማ የስራ ስሜት ምንጭ ይሆናል። መንግስት በውሳኔዎች ላይ ቀልጣፋ ውሳኔ እንዳያደርግ ሰበብ ይሆናል። ዜጎች ተንቀሳቅሰው ንብረት ማፍራታቸው ላይ ማነቆ ነው። ከአካባቢ ወጥቶ የሚኖር አምራችነትን አያበረታታም። መጤ እና ነባር የሚል ምድብን ለመፍጠር ምቹ መንገድን ይጠርጋል።

ብሔራዊ ስሜትን ማጥፋቱም ለብቻው ሊታይ የሚችል አንድ የዘውግ ፖለቲካ ችግር ነው። ብሔራዊ ስሜት የሌለበት ሀገር ደካማ የመሆን እድሉ በእጅጉ ሰፊ ነው። ሰዎች የሚለፉለት የጋራ ዓላማ፣ የሚተባበሩበት የጋራ ርእይ ይጠፋል። የሚጋጩ ህልሞች የሚፈሉበት መስክ ይሆናል!

ፎኮያማ ከወራት በፊት በፃፈው አንድ ፅሁፍ ላይ እንዲህ ያሰፈረው በስፋት ይገልፀዋል፤
«weak national identity has been the Major problem in the great middle east where yemen and Libya have disintegrated into failed states and Afghanistan, iraq, syria and Somalia have suffered from international insurgency and chaos. Other developing countries that have remained more stable have nonetheless found themselves beset by problem related to a weak sense of national identity»

የልሂቃን ቅራኔ ማጦዣ

በተጨማሪም መሰረታዊ የሕዝቡ ችግር ዳር ተገፍቶ የልሂቃኑ ጡንቻ ማሳያ፣ የፉክክራቸውን ዐውድ በማመቻቸት የሀገሪቱን እዛው የመርገጥ እድሜ ያረዝማል!

እና?
በየትኛውም ስሌት የሚያዋጣው አንድ መንገድ ነው። የዜግነት ሥርዓት ማቆም።
ዩሱፍ ያሲን እንደሚለው፤
«የመብቶችና የግዴታዎች እኩልነት የሰፈነበት ሥርዓት የግድ በዜግነት ዋስትና ላይ መመርኮዝ ይኖርበታል»

ጥቂት ገፆች ተሻግሮ እንደሚያነሳውም፤
«በዜግነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ ማንነት በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ምስረታ ሂደት ላይ አንድ የማዕዘን ድንጋይ ነው»

ይሄን ማድረግ ካልቻልን ግን የዛሬ መራኮቶች እድሜያቸው ረጅም፣ ፀጥ ብለው ቢቆዪ እንኳን ከሀገሪቱ ገላ ላይ የማይፋቁ ችግሮች ናቸው!

ብዙሃነታችንን የሚቀበል የዜግነት ፖለቲካ እስከሌለን፣ ሀዘናችን ከዚህ ሊዘልቅ ይችላልና ማዘናችሁን ቆጥቡ! ዜግነት ሲባልም «በአንድነት ስም ሊጨቁኑ» የሚል የተረት ወግ የትም አያሻግርም፤ ለመሸጋገርም የሚያበረክተው አንድ ፍሬ የለም!
ለማስታወስ ያህልም፣ ሀገሪቱ በታሪኳ የዜግነት ፖለቲካ ኖሯት አያውቅም!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...