Tidarfelagi.com

“የዘር በቆሎ” እና ሌሎች ነጥቦች

ሰሞኑን ኑሮ ተወዱዋል። ትንታኔና ትንቢት ጥንቡን ጥሉዋል። እኔም አይኔን አጥቤ ድርሻየን ልተነትን ነው። ቀልዱን እዚህ ላይ ላቆየውና ውደ ቁምነገሩ።

ባጭር ጊዜ እንደ ዶፍ የወረዱት ክስተቶች እንኩዋን ለመተንተን ለመቆጠር እንኩዋ እንደሚያቸግሩ አላጣሁትም። በሁለት ጉዳዮች ላይ ብቻ ባገር ልጅነት የሚታየኝን ለማካፈል እወዳለሁ። አብይ አህመድ በዘመነ መንግስታቸው ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ ጌቶችን ከቦታቸው አስነስቶ “በክብር” የሸኘበት መንገድ አስደንቆኛል። እንዲህ አይነቱ ዘዴ በፖለቲካ ፈላስፎች ዘንድ ምን ተብሎ እንደሚጠራ አላውቅም። አንዲት የጥንት አዝማሪ ” አመንምኖ መጣል” ትለዋለች።

“እንዋጋ ይላል ጉልበቱን ያመነ
መጣል እንዳንተ ነው እያመነመነ”

ያለቺው ትዝ ብሎኝ ነው።

በስልጣን ላይ የነበሩ ጌቶች መስቀል አደባባይ ላይ ቁልቁል ተሰቅለው ማየት ይናፍቅ የነበረ ሰው በጠቅላዩ አካሄድ እንደሚከፋ መገመት ይቻላል። ዋናው ነገር እንደ ዜጋ ምንድር ነው የምንፈልገው የሚለው ነው። ከበቀል የሚገኘውን ርካታ ወይስ ሰላም? ሁለቱንም ባንዴ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። ጉልበት አለኝ : ቀን ሰጠኝ ብለህ አንዱን ለመቀጣጫ ብትገድለው ከሱ ጋር ንክኪ ያለው ሁሉ ባልሞት ባይ ተጋዳይ መመከቱ አይቀርም። አገራችን ከወደቀችበት እንድትነሳ ካስፈለገ: የነውጥ የበቀል እና የብድር መመላለስ ፉርጎ የሆነ ቦታ ላይ መሰበር አለበት።

በግርግር ተለባብሶ ያለፈውን ሁለተኛውን ቁም ነገር አንስቼ ላምልጥ።

እነ መብራት ሃይልን ለ “ታምሪን” ብጤ ነጋዴዎች አሳልፎ ለመስጠት የተላለፈው ውሳኔ አሳስቦኛል። በነገራችን ላይ ታምሪን ማለት በክበረነገስት ውስጥ የተጠቀሰ: ንግስተ ሳባ (ማክዳ) ኢየሩሳሌም ሂዳ ከሰለሞን ጋር ባይነስጋና በግብረስጋ እንድትገናኝ ጎትጉቶ ያሳመነ ነጋዴ ነው። ሀብታቸውን ተጠቅመው የመንግስትን መንገድ የሚጠመዝዙ ከበርቴዎች ታምሪኖች እንላቸዋለን።

አብዛኛው ያገራችን ድሃ ተስፋው ምንድነው? የመንግስት ድጎማ አይደለምን? መክፈል እና መሸመት የሚችሉ ቱጃሮች ብቻ ሃይል ከመጠቀም አልፈው የሚያባክኑበት : ድሆች በጨለማ የሚኖሩበት ዘመን እንዲመጣ አልመኝም።

ዞሮ ዞሮ የህዝብ ትግል ግብ -መሰረታዊ ነገሮች የሚሰጡ እንጂ የሚሸጡ እንዳይሆኑ ማድረግ ነው።

ሰሞኑን የህዝብን ሀብቶች ለነጋዴዎች ለመሰጠት የተወሰነው ውሳኔ አሪፍ አርጎ የሚገልጠው ሰሞኑን ከሃያሁለት ወደ የረር በር ስሄድ አንድ ታክሲ ሹፌር ያወጋኝ ወግ ነው።

አንድ ድሃ ገበሬ በክፉ ቀን : እየቀላወጠ የሰውድግስ ሲነፋ ይውልና ወደ ቤቱ ይመለሳል።

ሚስቱ እና ልጆቹ የሚላስ የሚቀመስ ሳይሸታቸው ስለዋለ ለዘር ተብሎ ደጅ ጣራ ላይ የተንጠለጠለ በቆሎ ቆልተው ለመብላት አሳብ ያቀርባሉ። አባዋራው ግን ” አይደረግም!! በኔ መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር ይህ አይደረግም ” ብሎ ቀወጠው። በማግስቱ የሰውየው ጥጋብ እንደ ጉም አለፈ። የልጆቹና የሚስቱ ራብ ተጋባበት። እና ሲጨንቀው ሚስቱን ጠርቶ

” መቼም አያልፍልኝ!
በይ የዘሬን ቁይልኝ” አለ ይባላል።

የህዝብ መገልገያ ሀብቶችን ለነጋዴ መሸጥ ለዘር የተቀመጠ በቆሎ እንደመሸጥ ያለ ቀቢፀ ተስፋ ነው እላለሁ።

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

3 Comments

 • Kassahailu6@gmail.com'
  ጀማሉዲን ሚፍታ፡፡ commented on July 3, 2018 Reply

  አሁን የታሰበው ለባለሃብት የመሸጥ ሃሳብ እኛን ያማከለ ከሆነና በሌላው አለም እንደሚሰራበት ከሆነ አይጎዳንም ባይ ነኝ።

 • trueእንዳንተ አይደለሁሞ። commented on September 18, 2018 Reply

  30-25+2/3=10

 • weluteklit2017@gmail.com'
  ኢዞና ናዛኢ commented on July 5, 2019 Reply

  ነገረኛና አሽሙረኛ ብሎ የጥበብ ሰው የለም:አንተ ግን አጉል ልወደድ ባይ አይነቱ ቀልደኛ ምቀኛ ሸረኛ ነገረኛ ነገር ነህ…..

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...