Tidarfelagi.com

የወንዶች ሳሎን

በቀደም ዳጎስ ያለ ደመወዝ ተቀብየ ፥ ነጠር ነጠር እያልሁ በሰፈራችን ሳልፍ፥ “በውቄ ግባና ጸጉርህን ትንሽ ላሰማምርልህ “ የሚል ድምጽ ሰማሁ፤ የብዙ ዘመን ጸጉር አስተካካየ ሳሚ ነው ፤ ሚካያ በሐይሉ ‘ ጸጉሬንም ቆጥረሀል “ ብላ የዘፈነችው ለሳሚ ይመስለኛል፤ ሳሚ ፈጣን ነው ፤ ወሬ አያበዛም፤ በርግጥ ቶንዶሱ እንደ ጊንጥ ይቆነጥጣል፤ መቀሱንም በትርፍ ጊዜው የዳቦ ቆሎ እሚቆርጥበት ይመስለኛል ፤ ያም ሆኖ በሀያ ደቂቃ ውስጥ አሰማምሮ ይልከኛል፤ ሰባ ብር እከፍለዋለሁ፤ ሳሚ ብዙ አያወራም፤ደንበኞቹን አይሸነግልም፤

አንድ ቀን የሆነ ሰውየ ከመስተካከያው ወንበር ላይ ጉብ እንዳለ፥
“እንዴት ነው? ጸጉሬ ላይ ሽበት ጣል ጣል እያለበት ነው አይደል?” ሲል ሳሚን ጠየቀው፥ ምላሽ ሳይሆን ማጽናኛ ነበር የሚጠብቀው።
ሳሚ ፥ ከቦረንቅ ድንጋይ ተጠርቦ የወጣ የመሰለውን የሰውየውን ራስ በትካዜ እየተመለከተ፥ እንዲህ አለ፥
“በሽበቱ ላይ ጥቁር ጣል ጣል ብሎበታል ማለት ይሻላል“
ሰውየው በጣም ተናደደ እና እዚያው ወንበሩ ላይ ተጨማሪ ሽበቶችን አቆጠቆጠ፤
የዚያን ቀን ሳሚ “ ግባና ላሰማምርልህ “ ሲለኝ ፥ በልቤ ለእድሌም አላሳየው” አልሁና በአፌ “ ለዛሬ አያስፈልገኝም” ብየው አለፍሁ፤ ከጥቂት ደቂቆች በሁዋላ ፤በከተማው ውስጥ የታወቀ የከፍተኛው ማህበረሰብ መዋቢያ የሆነ የወንዶች ሳሎን ውስጥ ራሴን አገኘሁት።
ሰራተኞች በሙሉ ሴቶች መሆናቸውን ሳይ ፥ ለምን “ የወንዶች ሳሎን” እንደተባለ ሊገባኝ አልቻለም፤ የሌላቸው ማሽን የለም፤ ኤክስሬይና ሲቲ ስካን ሁሉ አላቸው፤ አንዲቱ አስተካካይ ዙፋን እሚመስል ወንበር ላይ አስቀመጠችኝና ግምጃ የመሰለ መጎናጸፍያ አለበሰችኝ ፤ ከዝያ ወናፍ መሳይ አንስታ አየር ስትለቅብኝ ጠጉሮቼ እንደማለዳ አንሶላ ቀጥ ብለው ቆሙ! ለመጀመርያ ጊዜ መሀል ራሴን በመስታውት ማየት ቻልኩ፤ መሀል ራሴ ላይ ከቀሩት ጸጉሮች ይልቅ አፍንጫየ ውስጥ የተሰገሰጉ ጸጉሮች በቁጥር እንደሚልቁ ስመለከት አልቅስ አልቅስ አለኝ፤ ወደ ሀብት እና ወደ መላጣነት በተመሳሳይ ሰአት መቃረቤን ስገነዘብ፥ የዚህ አለም ከንቱነት ጎልቶ ታየኝ፤

ስመለጥ ምን እንደምመስል ራሴን አሰብኩት፤ አጤ ምኒልክ ያለ ሻሽ ! እንደ ፓስተር ዮኒ አስተክላለሁ ወይስ እንደ ሰይፉ ፋንታ ሁን በመላጣየ ጸንቸ እኖራለሁ? እያልሁ ሳስብ፥ “ ቀጣዩ ክፍል ሂድና ኤሚ ታጥብሀለች” አለችኝ ፤ የማስዋብ ሙከራ የምካሂድበኝ ልጅ።
ቀጣዩ ክፍል እንደገባሁ፥ አማረች የተባለች ሴትዮ ተቀብላ መከዳ ያለው መክተፍያ እሚመስል ጣውላ ላይ አንጋለለችኝ ፤ ፊቴ ላይ አንድ እፍኝ ዝልግልግ ነገር ደፈደፈችበት! ከዛ ፊቴን ለፒዛ እንደታጨ ሊጥ ደጋግማ ዳመጠችው:: በማስቀጠል፥ የውሀ እሩምታ ዘለግ አድርጋ ለቀቀችብኝ ! ግልጡን ለመናገር ያክል waterboarding የተባለው የጓንታናሞ ቅጣት አካሄደችብኝ ! በመጨረሻ በመስታወት ፊት ቆምኩ፤ ተድበስብሶ የቆየው የግንባሬ መስመር አሁን በደንብ ፍጥጥ ብሎ ፥ የጉንዳን የቀለበት መንገድ ይመስላል ፤ ጸጉሬ ተቀባበለ የጃርት ወስፌ መስሎ ትኩረት ብቻ ሳይሆን እንደ ዲሸ ቻናል ይስባል!
በመጨረሻ አንድ ሺህ ብር ቆጥረው ሲቀበሉኝ “ ዊልስሚዝን መሰልህ “ ያሉኝን አልረሳውም።
ከሳሎንየው እንደወጣሁ ስልኬን አንስቸ ደወልኩ፤
“ ሄሎ ሳሚ!
“አቤት”
“ብዙ ወረፋ ከሌለበህ ብቅ ልበል?”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...