Tidarfelagi.com

የከምባታ ህዝብ አና የአጼ ዘርዓያዕቆብ መንግስት (1434 – 68) የወዳጀነት ታሪክ

የታሪክ መዛገብት አንደሚያስረዱት የከምባታ ህዝብ አና አጼ ዘርዓያዕቆብ በጣም የቀረበ የወዳጀነት ታሪክ ነበራቸው ። የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ሚስት ንግስት እሌኒ የሃድያው ንጉስ ልጅ የነበረች ስትሆን ከንጉሱ ሞት በኋላ በሌሎች ሶስት ነገስታት ዘመን ከፍተኛ የአስተዳደር ስራ ፈጽማ በ1522 ከዚህ አለም በሞት አርፋለች። የተቀበረችውም በትልቅ ጥበብ ባሰራችው ቤ/ክርስቲያን መርጡለ ማርያም፣ ጎጃም ነው። እሌኒ ከሞተች ከ7አመት በኋላ የግራኝ ጦርነት ተነስቶ በሁዋላ እሱዋ በጠየቀችው የፖርቹጋሎች እርዳታ አገሪቱን መከላከል ተሽሏል።

በነገራችን ላይ የከምባታ ስም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በግዕዝ ሰነድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በቀዳማዊ ዐምደፅዮን (1314-1344) መዘጋጀቱ የሚነገርለትና እንደገና በአጼ ሠርፀድንግል (1568-97) ጊዜ ተሻሽሎ መጻፉ የሚተረክለት “ሥርዓተ መንግሥት” በሚባለው በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በ12ኛው ተራ ክፍል “ከንምቦ/ከምባታ” ተመዝግቦ ይገኛል። ከአጼ ይስሐቅ ዘመነመንግሥት አንስቶ በግራኝ መሐመድ በተመራው ወረራና ቀጥሎም ባሉት ዘመናት (1642-1862 ዓ.ም) በተከታታይ በተቀሰቀሱት የኦሮሞ ማህበረሰቦች የመስፋፋት ዘመቻዎች ምክንያት የደቡብ ግዛቶች ከማዕከላዊው መንግሥት እስከተቆራረጡበት እስከ 17ኛው ምዕተዓመት መጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ከምባታ ያለማቋረጥ በታሪከ – ነገሥታትና በዜና መዋዕሎች ተደጋግሞ ሲጠቀስና ሲወሳ የኖረ አድያምና ሕዝብ ነው። በአንፃሩ እስከ 17ኛው ምዕተዓመት ድረስ የጠምባሮ ፣ የዶንጋ ፣ የዱበምና የሎካ ማህበረሰቦች ከከምባታ ተለይተው የተጠቀሱበት መረጃ በታሪክ ተመዝግቦ አይገኝም። ከነዚህ ማህበረሰቦች መካከል የጠምባሮና የዶንጋ ስሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሰው የሚገኙት በ1837 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1845) ወደ አሩሲ አካባቢ ድረስ ዘልቆ ክልሉን የጎበኘው የጂዎግራፊ ተመራማሪ አንቷን ዲ. አባዲያ በዘገበው መረጃ ላይ ነው።

ስለከምባታ ጥንታዊ ታሪክ ጠቃሚ መረጃዎችንና አስተማማኝ ዋቢዎችን ትተው ካለፉት አውሮጳውያን መካከል የሃይማኖት ፣ የታሪክ ፣ የቋንቋ ፣ የመልክዓምድር ፣ የሥነሕዝብ ከፍተኛ ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ኤፍ አልቫሬዝ (እ.ኤ.አ 1520-26) ፣ ማኑኤል ዲ. አልሜዳ ፣ ፔሮ ፔይዝ እና አንቶኒዮ ፌርናንዴዝ ፣ ዤሮሜ ሉቦ ፣ ኢዮብ ሎዶልፍ እና ኤም ሌግራንድ (እ.ኤ.አ 1628-46) ለከምባታ ታሪክ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ግለሰቦች ናቸው። በአጼ ይስሐቅ ዘመነ መንግስት (1412-29) ዓመታዊ ግብር ለማዕከላዊ መንግሥት ይከፍሉ ከነበሩት ሠላሳ ዘጠኝ (39) ግዛቶችና ሕዝቦች መካከል ሰባት የደቡብ ክልል ግዛቶች የም ፣ ከምባታ ፣ እነሞር ፣ አላባ (ሐላባ) ፣ ጉዴላ (ሀዲያ) ፣ ቀቤና እና ገደብ (ጎጀብ) ተመዝግበው ይገኛሉ።

በአንፃሩ በአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት (1434 – 68) በራሱ በአጼው ዜና መዋዕልና በሌሎች ሰነዶች ጭምር ውስጥ ተዘርዝረው ከሚገኙት አርባ ስምንት ዋና ዋና የማዕከላዊ መንግሥት ገባር ግዛቶች መካከል አንዱ ከምባታ መሆኑ ተመዝግቦ ይገኛል። በተመሳሳይ ሁኔታ በተከታታይ ነገሥታት የሕይወት ታሪክ ውስጥ ሁሉ ከምባታ ሳይጠቀስ የታለፈበት ዘመን የለም። ከ1628 – 46 (እ.ኤ.አ) ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጠ ይኖሩ የነበሩት ፖርቱጊዛውያን ማኑኤል ዲ. አልሜዳ ፣ ፔሮ ፔይዝ እና ሜንዴዝ ከምባታን ጨምሮ ሌሎች 47 ገባር ግዛቶች እንደነበሩ እነዚህ ፖርቱጊዛውያን ገልጸዋል።

አጼ ዘርዓያዕቆብ (1434-1468) በዘመነመንግሥቱ ከምባታን ጎብኝቶ እንደተመለሰና በዛሬው የሀዲያ ዞን በሊሙ ወረዳ “ሆሲስ-ሐምበሪቾ” የሚባለው ኮረብታማ ሥፍራ የአጼ ዘርዓያዕቆብ ጥንታዊ ከተማ እንደነበረ ታሪኩን ቀደምት አባቶች ለተተኪው ትውልድ ቃል በቃል ሲያስተላልፉት ኖረው ውርሱ ለዛሬው ትውልድ በመድረሱ ሕያው ምስክርነቱ ዛሬም በከምባታ አካባቢ ህብረተሰብ ይወሳል። ከምባታዎች የዚህን ንጉሥ ስምና ዘመን የሚያወሱት በአንድ ወቅት በሀገራቸው ውስጥ በማለፉ ብቻ ሳይሆን አጼ ዘርዓያዕቆብ ለ34 ዓመታት በቆየ ረጅም የአገዛዝ ዘመኑ በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ እምነትን በሚያስፋፋበት ዘመን ዘርዓ አብርሃም የተባለ የገዛ ልጁን ወደ ደቡብ በመላክ የክርስትናን እምነት ለማስፋፋት በመጣሩና በዚሁ ልጁ አማካኝነት የሦስት ሥፍራዎች አብያተክርስቲያናትን በማሠራት የማይረሳ መታሰቢያ ትቶ በማለፉ ነው። የአጼ ዘርዓያዕቆብ ልጅ ዘርዓአብርሃም በወቅቱ ሕዝቡ ሰፍሮ በሚገኝበት በሐምበሪቾ ተራራ አምባ-ምድር ላይ በጥቂት ተከታዮቹ አማካኝነት የክርስትናን ሃይማኖት እያስተማረ እንዲኖርና በተራራው ጫፍ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን “የክርስቶስ መለመኛ” ሥፍራ ብሎ ሰይሞት እንደነበረ በታሪክ የሚነገር ሲሆን ሕዝቡም በቋንቋው “ክቶሲ-ኡጨቃንቹ” (“የክርስቶስ መለመኛ”) ብሎ ይጠራዋል።

ከአጼ ዘርዓያዕቆብ ቀጥሎ በነገሠው በአጼ በዕደማርያም ዘመነመንግሥት (1468-78) ምሪተኛ ሠራዊት ወደ ከምባታ ተልከው እንደሰፈሩ ታሪክ ያወሳል። የንጉሥ በዕደማርያምን ዜና መዋዕል የተረጎመው ፔሩሾን ስለተጠቀሰው ሠፈራ የሚከተለውን ዘገባ ያትታል፡
“ሚስቶቻቸው ፣ የቤት ዕቃዎቻቸው ፣ ልጆቻቸውና ንብረቶቻቸው ሁሉ ወደ ከምባታ እንዲደርሱላቸው ተደርጓል። የዚህም ጉዞ ወይም የሰፋሪ መንገደኛ ስም ዳዊት አራዛ (ሃራሳ) ተብሎ ተሰየመ።”

ከአጼ በዕደማርያም ዘመነመንግሥት አንስቶ እስከ ግራኝ መሐመድ ጦርነቶች ድረስ ከምባታ የክርስቲያን ኢትዮጵያ አካል ሆኖ ከቆየ በኋላ ከ17ኛው ምዕተዓመት መጀመሪያ አንስቶ እስከ 19ኛው ምዕተዓመት መጨረሻ ገደማ ድረስ በኦሮሞ ወሪራ ምክንያት ክልሉ በትናንሽ ጠባብ ግዛቶች (ከምባታ ፣ ጠምባሮ ፣ ዶንጋ ፣ ዱበሞ ፣ ሶሮ ፣ ሌሞ ፣ ሻሾጎ ፣ መስመስ ፣ ባዶጎ ፣ ሃላባ ፣ በደዋቾ) ተከፋፍሎ እያንዳንዱ ግዛት በየራሳቸው ንጉሦችና መሪዎች የሚገዙበት ሁኔታ ተፈጠረ። ራቅ ባለው ዘመን በተለይ በ17ኛው ክፍለዘመን ከነበሩት የአውሮጳ ተጓዦችና የምርምር ሰዎች መካከል ስለከምባታ አስተማማኝ መረጃዎችን በማቅረብ ከታወቁት ተመራማሪ አንቶኒዮ ፌርናንዴዝ (1613-14) በአጼ ሱስንዮስ ዘመነመንግሥት የመልዕክተኞች ቡድን አባል በመሆን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ተጉዞ ከሦስት አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በከምባታ ውስጥ ያየውንና የደረሰበትን ሁኔታ የሚያስረዳ ጥናታዊ ዘገባ በጽሑፍ አስቀምጦ ያለፈ ስለሆነ ለከምባታ ዕውቅ የላቀ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ምንጭ „የከምባታ ጠምባሮ አድያም (Polity) እና ሕዝብ ታሪክ ከየት ወዴት?“ (ከአምባሳደር ተስፋዬ ሐቢሶ, 2013)

One Comment

  • ኮ ተክሌ commented on April 3, 2018 Reply

    Great piece of information about the greatest people of Kambata. Actually none or little is said and written about the beautiful people of Kambata and their culture. I love it and wish to read more articles about these people!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...