Tidarfelagi.com

የእናኑ መልዕክት ለሽሮ ሜዳ ዜጎች

. . . ሁሉን ነገር ካስተዋሉት ያስገርማል። የኑሮ ትንሽ የለውም። እዛ የወደቀችው ሳር አስገራሚ ናት። ወፍ ለቅሞ ጎጆ ይሰራባታል። ይሄን ሳር አጭዶ ያመጣው ማጭዱ አስገራሚ ነው። ሰዎቹ ማጭድ ማሰባቸው?! .. ሳሩን አጭዶ ያመጣልኝ ሰውዬ ዘገየ ይባላል። ጨዋታ ያውቃል። እሱ ሲያወራኝ የሚገርም ነው ታሪኩ። ‘ለምን?’ ብትል እንዳው ወንድ ሆነ እንጂ ታሪኩ ተኔው አንድ ነው።
የእኔ ታሪክ ምንም ብለፋ፣ ምንም ብቀባጥር የእኔ ብቻ አይሆን። ‘ለካ የእሱ የእኔን ይመስላል!’ ብለህ መታዘብ አለ።
ያንተ የአንተ ተሆነ፣ የእናትህ የእናትህ ተሆነ፣ የሰብለ የሰብለ ከሆነ፣ እንዴት እዝህ ደረስን? እሱ እኮ ነው!
***
ጠዋት እዚህ ፀሐይ ስሞቅ የቆረጥኩት የአውራ ጣቴ ጥፍር ለስንት ጉንዳን እራት ይሆናል?
ባላርስም አበላሁ ማለት አይደል? . . .
****
ፊታውራሪ መሸሻ ሰብለን አባረሩ። ጣሊያን እኔና ሰብለን፣ ሳርኪስን አባረረ። ሳርኪስ ሞተ። በዛብህ ሞተ። በመሸሻና በሞሶሎኒ መሃል ልዩነቱ ምንድን ነው? በኮሪያና በተማሪ ድንጋይ መሃልስ?
የዕውን ላስብ ብትለው አያሳስብም? . . . .
***
ነፃነት ተመለሰ። ያም ወሬኛ ንጉስ ነኝ ብሎ። እንግሊዝ እየነዳ አመጣው። ገረሱን አያደርጉትም ነበር? በላይን አያደርጉትም ነበር? አበበ አረጋይስ? ዞሮ ዞሮ ማን? እሱ!!
እድሮው መሬቴና ቤቴ ተመለስን። ጎጆዬ ፈርሳ የጣሊያን መኮንን ይሄን ሕንፃ ሰርቶበት አገኘሁ። ቤቱ ይበርደኛል፣ ይሸተኛል። አየር አያስገባ!! ይኼው አድሬበት አላውቅም። ከጀርባ ያለው ጭቃ ቤት ነው የምተኛው . . .
ብርዱን አልቻልኩትም። ቁርጥማቱ አላስተኛ አለኝ። ጭቃ ቤት ነው ለኔ የሚሆነኝ። ገና ለገና ፈረንጅ የሰራው ቤት ልኑር ብዬ ዕድሜዬን አላሳጥርም . . .
****
እኛ ሀገር ከአመት አመት ጦርነት ነበር ልጄ።
ስንቷ በሙሽርነቷ ቆማ ቀርታለች? እኔም አንዷ አይደለሁ?
ስንቷ ባሏን፣ ስንቷ የከንፈር ወዳጇን አጥታለች? ቤቱ ይቁጠረው።
ስንቱ ሎጋ አካለ ስንኩል ሆነ? ባሌ የነበረው የአሰፋ አባት (ሱባ ተጠናሁ በኋላ አግብቼው …. ማግባት ነው እንዴ?) የእኛው አላንስ ብሎ በሌላ ሰው ነገር ገብተን፣ ኮርያ ሄዶ ታሞ መጣ።
ብዙ አልቆየም ሞተ . . .
እናልህ ለሌላ ቆስሎ መሞት ምን የሚሉት ዘዬ ነው? እኔ አሁን ኮርያ የሚባል ሀገር ይኑር አይኑር በምን አውቃለሁ? ለራሳችን አንሶ ለሰው ተርፈን። ወንድ በዝቶብን ነው እንደ ቡና ወደ ውጪ እንልክ የነበረው? ኮርያ ለኔ ምኔ ነው? ስንቱ ገበሬ በጥልያን ቡዋንብ ተመታ? ዓይኑ ታወረ? ስንቱ ነው ‘መሶሎኒ’ የሚባል ፈረንጅ የሚያውቅ? እንደው በመንገድ ተላልፈው ‘ኖር’ ‘ኖር’ ‘ወያ’ ‘ወያ’ ተባብለው ያውቃሉ?
ተዚያ በሶማል በኩል፣ ተዚያ በሐማሴን በኩል በየቦታው ጦርነት። ማን አዘዘ ይሄን ሁሉ?
አሁን ደግሞ በየትምሕርት ቤቱ ተማሪ ይራበሻል። እኔ ይኼን አልወድም። ባለፈው እዚህ የተወረወረ ድንጋይ አንድ የቦሊስ ዓይን አጠፋ። አንድ ዓይኑ ፈረጠ። እንዲህ እኛ ሰፈር ተንጋሎ ሲያጓራ ነው ያየሁት። የተመታበት ድንጋይ ልጅ የወረወረው አይመስል። ተመሃል ሆሆሆ እያለ የስንት ሰው ቤት ይፈርሳል? እስኪ ንገረኝ . . . .
***
. . . ራስህን ጥንካሬ አስተምር። የከብት ጥንካሬ ሳይሆን የሰው። የአህያ ሳይሆን የሰው። ፅናትና ስራ አንድ ላይ ጎን ለጎን ካልሆኑ ድንጋይ መሆን ነው። አለዛ ትገፋለህ፣ ገድ ይርቅሃል . . .
***
#መረቅ
Photo – Marthas_point

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...