Tidarfelagi.com

ገፅታ ሳይኖር፣ ለገፅታ መጨነቅ ውጤት የለውም!

“በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ችጋር መጀመሪያ ነው፤ በመስከረምና በጥቅምት የዝናብ ወቅቱን ተከትሎ የሚመጣ ችጋር ገና መንገድ ላይ ነው፤ በአብዛኛዎቹ ገበሬዎች ላይ የሚደርሰው በመጋቢትና በሚያዝያ ነው፤ በድንቁርና ንግግርና በመመጻደቅ አይቆምም፤ አሁን የተከሰተውን ምልክት ለመቀበልና ዋናውን ችጋር ለመከላከል የሚያስፈልገውን እርምጃ በጊዜው መውሰድ ካልተቻለ ውጤቱ እልቂት እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፤ በ1977 ዓ.ም. የተከሰተውን የከፋ ችጋር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከአለፈው መንግሥት የወረስነው ነው በማለት ኃላፊነቱን ለመካድ ሞክሮ ነበር፤ አሁን ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚያመካኝበት አያገኝም፤ በየጋዜጣው ላይ በሚታዩት አንዳንድ ፎተግራፎች የተነሣ ዛሬ የሚገኘውን የእህል እርዳት ልማድ ሆኖ የሚቀራመተው ከመጣ ችጋሩን ለማክበድ ተፈልጓል ለማለት ይቻላል፡፡

በተባራሪ ወሬ እንደሚሰማው የችጋሩ ምልክት ከኦጋዴን እስከትግራይ እየታየ ይመስላል፤ ቀላል አይሆንም ማለት ነው፤ ሰፊ የኢትዮጵያ ክፍል፣ ብዙ የኢትዮጵያ አርሶ-አደር ችጋር ያርፍበታል፤ ብዙ ከብቶች ይሞታሉ፤ ብዙ የእርሻ በሬዎች ያልቀሉ፤ በዚህም ምክንያት ለሚቀጥለው ዓመት በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች የእርሻ መሬት ጦሙን ያድራል፤ ይህም ችጋሩን በአንድ ዓመት ብቻ የምንገላገለው አይሆንም ማለት ነው፤ ይህንን ረዥም የችጋር ጉዞ በዝርዝር ለመረዳት የፈለገ በእንግሊዝኛ የጻፍሑትን መጽሐፍ — Rural vulnerability to famine in Ethiopia … የሚለውን በመመልከት የበለጠ ግንዛቤ ማግኘት ይችላል፡፡” ፕ/ሮ መስፍን ወልደማሪያም

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ስለረሃብ ሁለት ጊዜ ጥናት አድርገዋል።
“በሁለቱ ጥናቶች የደረስኩበት መደምደሚያ ችጋር በይበልጥ፣ የጭቆናና የአፈና አገዛዝ ውጤት ውጤት እንጂ የተፈጥሮ መዛባት ብቻ የሚያመጣው አይደለም የሚል ነው ” ይላሉ!!…
“አደጋ ያንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ” በሚል መፅሐፋቸው!
ከታሪክ የምንማረው፣ ከታሪክ እንደማንማር በመሆኑ እንጂ ረሃብን ለመግታታት ብዙ እድል ነበረን። ያለፈው ይቅርና ያሁኑንም አልተጠቀምንበትም!
በርግጥ ለውጡ የማይመጣው ስለማይቻል አይደለም ስለማይፈለግ ነው። የሦርዐቱ ተጠቃሚ የሆኑት ገዢ መደቦች ለውጡን አይፈልጉትም።
በ16ኛው ክ/ዘ ዘድንግል የተባለው ንጉሥ የገባር ስርአት ገበሬውን እንደሚበዘብዝ ተረድቶ፣ የተሻለ ስርዓትን ለመትከል በመሞከሩ ራስ ዘስላሴ በተባሉ ሰው ተገደለ። የመገደሉ ምክንያት፣ ” ካቶሊክ በመሆኑ እንደሆነ ” ለሕዝቡ ተነገረ። ምናልባት፣ ዘድንግል ቢሳካለት የኢትዮጵያ መልክ አሁን ካለበት በብዙ መልኩ የተሻለ ይሆን ነበር።
ዛሬም ለሕዝቡ የማይመች፣ ለጥቂቶቹ የሚመች ፓለቲካዊ አካሄድ አለ። እንደልባቸው የሚዘርፉበት። ያሻቸውን ያህል የሕዝብ ገንዘብ ላሰቡት ዓላማ የሚያፈሱበት ስርዓት ” ሃላል ነው ” ተብሎ የታወጀ ነው የሚመስለው።
“The bottom billion ” በተባለ።መፅሐፉ፣ ፖል ኮሊየር የተባለው ኢኮኖሚስት የሚከተለውን ይላል።
“The leaders of the poorest countries in the world are themselves among the global super rich. They like things the way they are…”
.
.
የዚህ ረሃብ ቀዳሚ ተጣያቂም መንግስት መሆኑ ግልፅ ነው።

ዛሬ ክስተቱን ለጥቂት ወራት መሻገር ያቃተው ገበሬ፣ በኢቢሲ የስርአቱ ተጠቃሚ እንደሆነ፣ ከአስር እስከ ሃያ ሚሊዮን ብር እንዳለው፣ ባለ አይሱዙ መሆኑ ተደጋግሞ የተነገረበት ነው! የውሸት ክምር በችግር ጊዜ መናዱ አይቀርም! የታል ያ ገበሬውን ተጠቃሚ ያደረገ እድገት! ረሃብ ሲያይ የት ሸሽቶ ገባ?!

ለግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በየወሩ የሚከፈለው አራት መቶ ሺ ብር የማነው?
ጡረተኛ ለተባሉት ባለስልጣት ቤት የሚሰራበው በማን ገንዘብ ነው?
ነገም በዚህ አዙሪት ውስጥ ደግሞ ላለመገኘት፣ ትክክለኛው የችግሩን ምንጭ መውቀስና ማረም አለብን። ትክክለኛው የችግሩ ምንጭ ደግሞ መንግስት ነው!

drought2

ረሃብ ክፉ ነው! እጅግ ክፉ! የሰውን ልጅ ልእልና እንዳልነበር የሚያፈራርስ፣ ሞራልን የሚገድል ጥቂር ሞት፣ጥቁር ሰቆቃ ለብሶ የሚመጣ ክስተት ነው!
ህዝብ ሲርበው አይደለም ከሚቀይረው መንግስት፣ አይነኬ ከሚለው፣ ከማይለውጠው አምላክ ይጣላል፤ይሟገታል።
“ትችለናለህ ወይ እግዜር በትግያ…” እያለ ይሟገተዋል።
“እግዜርም እንደ ሰው በሃሰት እየማለ… ” እያለ ከሰው አቻ ያደርገዋል!
ረሃብ ክፉ ነው! “ክቡር ” ለሚባለው የሰው ልጅ፣ ለህሊና የሚከብዱ ፍዳዎችን ተሸክሞ የሚመጣ የክስተቶች መልከ ጥፉ ነው! ድቅድቅ ጥቁር! ጥፍራም! አስፈሪ ስቃይ ነው!
ሰው፣ የሰውን ስጋ እስኪበላ ሥነምግባራዊ አጥሩን ያስጥሰዋል! ይህ በ 1884 ዓ/ም ክፉ ቀን በተባለው የረሀብ ወቅት ተከስቶ ነበር።
:
ረሀብ ለህሊና የሚከብዱ ትዕይንቶችን አንድ ሰፈር አምጥቶ የሚያራግፍ ጨለማ ሃቅ ነው! ለመዋጥ የሚንቅ ሃቅ!!
እናት እጇ ላይ ልጇን የምታጣበት ነው፣ ረሃብ! ልጅ የደረቀ የእናቱን ጡት በአፉ እንደያዘ የሚቀርበት ነው ረሃብ!
አባወራ ሚስትና ልጆቹን በአንድ ቀን የሚቀብርበት ነው ረሃብ! አስር ሃያ ሰዎችን በየቀኑ መቅበርን ተራ ነገር የሚያደርግ ነው ረሃብ!… ረሃብ ክፉ ነው!! በተደበቀ ቁጥር ደሞ፣ ክፋቱን እያወፈረ ይሄዳል!!
ህንዳዊው ኢኮኖሚስት Amartya sen, “poverity and Famine” በተባለ ስራው ስለረሃብ ጠንካራ ክንድ ሀገራትን ምሳሌ አድርጎ ከተነጋረቸው መሃል የሚከተሉት አሉ።
— በ436 ዓመተ ዓለም በሺ የሚቆጠሩ ሮ ውያን ራሳቸውን ወደ Tiber ወንዝ ወርወሩ (በረሃብ ከማለቅ አይነት ነው ነገሩ)
— በ918 ዓመተ ምህረት በካሽሚር፣ vitasa የተባለ ወንዝ ሙሉ ለሙሉ በሬሳ ተመሸፍኖ ነበር! በረሃብተኞች አስክሬን!
— በ313-7 በቻይና አራት ሚሊዮን ህዝብ ከአንድ ክልል ብቻ አልቋል!
— በ1770 በህንድ አስር ሚሊዮን ሰዎች!
— በአየር ላንድ፣ ከ1845-51 የፖታቶ ረሃብ ተብሎ በሚታወቀው ረሃብ የህዝቡ አንድ አምስተኛ ህዝብ እንዳለቀ ይነግረናል።
እንግዲህ አማርቲያ ሴን፣ ረሃብ መንግስት ሰራሽ እንደሆነ አጥብቆ የሚያምን ነው ነው!
መንግስት ህዝቡን ሁለቴ ይገድለዋል። አንድ ለረሃቡ በመሆን ሲሆን፣ ሁለተኛው ረሃቡን አላምንም ብሎ ድርቅ በማለት ነው። በመንግስት ድርቅና፣ ጉዳቱ ማድረስ ከሚችለው ጉዳት በላይ ይወፍራል።
ባለፉት ዘመናት የሆነው ያ ነው።
ሃይለስላሴ ከሰማንያኛ ዓመት ልደታቸው የተለየ ክብደት አልሰጡትም!
ደርግ፣ የኢሰፓ አስርኛ ዓመት የልደት በዓሉን እንዲረብሽበት አልፈለገም!
ኢህአዴግ፣ ከበአዴን ልደት የተለየ ትኩረት አልሰጠውም!
:
:
ያለፉት እድሎች አልፈዋል። የዛሬ እድል እጃችን ላይ ነው። መንግስት እርዳታውን ለሚያስተባብሩ ሰዎች በሩን ካልከፈተ፣ ጥፋቱን ድርብ ያደርገዋል።
“ማጥፋት ” ቅር የማይለው መንግስት ባይመከርም፣ ይሄን ለማገናዘብ ሰው መሆን ይበቃል!!
ገፅታ ሳይኖር፣ ለገፅታ መጨነቅ ውጤት የለውም! ወይ፣ መስታወት ማየት ነው። ሀቅ መስታወት ነው!!

በ ስልሳ ስድስት ህዝብ ተርቦ፣ ሃይለስላሴ ውሻቸውን ኬክ ሲያበሉ ነበር!
በሰባ ሰባት ህዝብ ተርቦ፣ ኢሠፓ የምስረታ በአሉን ውስኪ እየተራጨ ሲያከብር ነበረ!
በሁለት ሺ ስምንት ህዝብ ተርቦ፣ መንግስት ለታማኝ አዳሪዎቹ 25 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት እያሰራ ነው!
ያቺም እቺም አልማዝ ነው ነገሩ!
# በብዙ ሰዎቹ መራብ ላይ ጥቂት ሰዎች የሚጠበዱሉበት ስርአት የሚወርድበት ፍርማታ ምን ያህል ይርቃል!
# ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
ነው እንደመንግስት፣ ፕሮፖጋንዳ ያደራጃል!
ለግድቡ የነዘነዘኝ መንግስት የታል?!!!

ethiopia_food_shortage_areas

ከኤሊኖ በፊት ጭቆና ነበረ። ድርቅን ማስቀረት ባይቻልም፣ ረሃብን ነፃ የፓለቲካ ስርአትን በመትከል ማራቅ ይቻላል። ይሄ ሃቅ ነው!
መሰል ስርአት እስካለ ነገም ረሃብ አለ። ኤሊኖ ላይ የተንጠለጠለ ፕሮፖጋንዳ ከመንዛት ተግባር ይቅደም!
ማውራት ቀላል ነው የምትል አጉል ሚዛናዊ ነኝ ባይ፣ መንግስት እያወራ እንጂ ይሄ ነው የሚባል ስራ እየሰራ እንደሆነ እንዴት አልታይህም ባክህ!
ለሚዛንም ጊዜ አለው! ሚዛኑን በሰበሩ ዱርዮች ፊት ሚዛን ይዞ መንከረታት ሚዛን የሳተ እይታ ውጤት ነው!
መንግስት ወሬውን ትቶ ስራውን ያሰየን። አሁን እንኳ ፕሮፖጋንዳዋ አየር ትውሰድ!
እንኳን 15 ሚሊዮን፣ 15 ሰው ቀልድ አይደለም!!!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...