Tidarfelagi.com

የአጎቴ አነቃቂ ንግግሮች እና የእኔ መፍዘዝ!

እንደማንኛውም ዕድሜው ለማትሪክ የደረሰ ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት መጥቶልኝ፣ ዩኒቨርሲቲ የመግባትና ተመርቆ የመውጣት ዕድል ገጥሞኛል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ አጎቴ ብዙ ምክርና ትንሽ የኪስ ገንዘብ በመላክ እያማረረ አስተምሮኛል። (አጎቴ ግን ለሰዎች ሲናገር “እያዝናናሁ አስተማርኩት” ነው የሚለው) የሚልክልኝ ብር በጣም ከማነሷ የተነሳ፣ አንዳንዴ እንደ ደሃ የሻምፖ ዕቃ፣ ኪሴን አለቅልቄ ነበር የምጠቀምባት።

ተመርቄ እንደወጣሁ አጎቴ ድል ያለ ድግስ ደግሶ፣ ያንን ሁልጊዜ ፍርድ ቤት ሲሄድ የሚለብሰውን ሰማያዊ ኮትና ሱሪውን ለብሶና ነጭ ከረቫት አስሮ ፣ ለታዳሚው ረዘም ያለ የመክፈቻ ንግግር አደረገ። “አብርሃም ከድሮውም ገና ከልጅነቱ አንጎሉ ለትምህርትና ለነገር እንዲሁም ለእንስቶች ጨዋታ ክፍት ነበር፤ እንሆ አሁንም ከታላቁ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ ተመርቆ አኩርቶናል” አለ። ታዳሚው ቀልቡንም ዓይኑንም ወደተዘጋጀው ቡፌ እንደላከ፣ በየአራት ነጥቡ ያጨበጭብ ነበር። ወደጆሮው ጠጋ ብዬ ‹‹ሳይኮሎጂ አይደለም አጎቴ ሶሾሎጂ ነው›› ብዬ አረምኩት! ወደኔ ገልመጥ ብሎ ‹‹ተወው ይኼ ሕዝብ የወሬ ጅራት ይዞ ነው የሚሮጠው … ምናለ በለኝ ‹ሎጂ› የሚለውን ብቻ ነው የሚያስታውሰው›› አለኝ ! እውነትም ታዳሚው ከበላና ከጠጣ በኋላ ‹‹በምን ሎጂ ነበር የተመረቅኸው?›› እያለ ይጠይቀኝ ነበር። ኑሮና ዕድሜ አጎቴን በሳይኮሎጂ ሳያስመርቁት አልቀሩም!

እንደአብዝሃኛው ኢትዮጵያዊ ተመራቂ ሁሉ እኔም ሥራ አጥቼ ለአንድ ዓመት ተቀመጥኩ። በዚህም አጎቴ በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ እቤት ተቀምጨ፣ ወይም አየር ልቀበል ብዬ የሰፈራችን ልጆች የሚቆሙባት ሱቅ ቆሜ ባዬኝ ቁጥር ‹‹አሁን እኔ ሰው አስመረኩ ነው የምል ወይስ ሐውልት አስመረኩ?›› እያለ ያጉረመርማል።
እንዲያው ‘ጨለምተኛ’ አልባልና፣ የአገራችን ሥራ አጥነት በዚህ ከቀጠለ በቅርቡ ተመራቂዎች ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ! ›› የሚለውን መዝሙር እንደሙሾ ደረታቼውን እየደቁ መዘመራቼው አይቀርም!

ሥራ አጥቼ በተቀመጥኩባቸው ጊዚያት ከምንም በላይ ያስመረረኝ እና ያፈዘዘኝ ‹‹የአጎቴ አነቃቂ ንግግር›› ነበር። አንድ ቀን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዞ መጣና እፊቴ እንደምንጣፍ ዘረጋግቶ ‹‹ ተመልከት ›› አለኝ። እኔ ደግሞ የሥራ ማስታወቂያ መስሎኝ ጋዜጣውን አዬት አደረኩት ‹‹ሁለት እጅ የሌለው የእንጨት ባለሙያ ›› ይላል …ጋዜጣው ላይ በአንድ እግሩ ጣቶች፣ ባለባርኔጣውን ሚስማር ፣ በሌላኛው እግሩ፣ መዶሻ የያዘ አካል ጉዳተኛ ኩርሲ ወንበር ሲሠራ ይታያል። አጎቴ ኮስተር ብሎ ‹‹ አዬህ አብረሃም፣ አንተ በእግርህ ሮጥ ሮጥ ብለህ ሥራ መፈለግ ሰንፈሃል፣ሰው በእግሩ የሚሠራውን ተዓምር አዬህ አይደለም? …እንድትነቃቃ ብዬ ነው ጋዜጣውን የገዛሁት …በእርግጥ አዋጅም ታትሞ ከሆነ ብዬ ነበር፤ አለና ጋዜጣውን አጣጥፎ ሄደ።

ሌላ ቀን ወደቤት ስገባ፣ አጎቴ በእጁ በያዘው ሪሞት ወደ 15 ኢንች ቴሌቪዥኑ እየጠቆመኝ ‹‹ና ተቀመጥ ! እግርህ ጥሩ ነገር ላይ ነው ዛሬ የጣለህ …. ተመልከት …እየው ይኼ ሰውዬ እንዳንተው ሰው ነው …ግን በምን እንደሁ እንጃ እንደምታየው እግሩ አይሠራ ፣እጁ አይንቀሳቀስ ፣ አፉ አይናገር፣ ከንፈሩ አይላወስ …. ዓይኑ ብቻ ናት የምትርገበገበው:: አንተ በጥቅሻ የሰፈሩን ልጃገረድ ስታማልል ፣ እሱ በጥቅሻ ሰማዬ ሰማያት ዘልቆ፣ ፀሐይ አልቀረው ጨረቃ ….እስተ ሰባተኛው ሰማይ ዘልቆ ስንት ሳይንስ፣ ስንት ምርምር ሠራ !…አሁን አንተ ተሱ ታንሳለህ አብርሃም ? እንድትነቃቃ ነው ይኼን የምነግርህ …አዚምህ እንዲለቅህ ›› ቴሌቪዥኑ ላይ ፈጥጨ ቀረሁ ። ከሱ አታንስም ያለኝ ታዋቂው እንግሊዛዊ ፊዚስት እና ኮስሞሎጅስት ስቴፈን ሃውኪንግን ነው! የፊቱን ስሜትና የዓይኑን እንቅስቃሴ እየተረጎመ በሚተነትን የዘመነ ዊልቸሩ ላይ እጥፍጥፍ ብሎ ተቀምጦ ስለብላክ ሆል የሠራው ምርምር ይተረክለታል … ምነው ይቺን ዊልቸር ባገኘኋትና ሸጨ የዶሮ እርባታ በጀመርኩ እላለሁ በውስጤ!

ሌላ ቀን ሥራ ፍለጋ ስንከራተት ውዬ በድካም ወደቤት ስንከላወስ…አጎቴ ከኋላ ጠራኝ ‹‹አብርሃም …ጠብቀኝ አንዴ የማሳይህ አለኝ …›› ኮቱ እስኪውለበለብ እየገሰገሰ መጣና ቁና ቁና እየተነፈሰ፣ በእጁ የያዘውን የግል ጋዜጣ ነፋስ ጋር እየታገለ መንገድ ላይ ዘረጋጋው …‹‹ስኬታማ ሥራ የሠሩ የዓለማችን አስደናቂ የአካል ጉዳተኞች›› ከሚል ርእስ ሥር አንዷን እየጠቆመ …. ‹‹ይችን ሴት ታያታለህ ?….ይች ሴት…እ… ?ሁለት እጅ የላትም ….አዬህ … ! እጇን አጣጥፋ እንዳንተ እቤት ቁጭ አለች ?…አለች ወይ? ››
‹‹እጅ ከሌላት እንዴት እጇን አጣጥፋ ቁጭ ትላለች አጎቴ? ››
ጥያቄዬን እንዳልሰማ አለፈኝና ….
‹‹ምን እያረገች ነው ….?አንብብልኛ?! ›› ብሎ አፈጠጠብኝ። ጀሲካ የምትባል በእግሮቿ አውሮፕላን የምታበር ሴት ታሪክ ነበር…ጭራሽ ጋዜጣው ‹‹ብዙዎች እግርና እጅ እያላቸው ለሥራ በሰነፉበት ዘመን …ይች አሜሪካዊት አካል ጉዳተኛ ግን ››….ይላል ! ጸሐፊው አጎቴ መሰለኝ! እንዳቀረቀርኩ ወደቤት መንገዴን ልቀጥል ስል…
‹‹ቆይ! ይኼን ደሞ ተመልከት!›› አለና ከሥር ሌላ ፎቶ ጠቆመኝ …ይኼንኛው ሁለት እጅም፣ ሁለት እግርም የለውም …ኒኮላስ ጀምስ የሚባል አውስትራሊያዊ ነው ….አጎቴ አንዴ እኔን በትዝብት፣ አንዴ ደግሞ በአድናቆት ጋዜጣውን እያዬ …‹‹ ሥራ ከመያዝ አልፎ ሁለት ወርቅ የመሳሰሉ ልጆች ወልዷል …አዬህ? …እያት ሚስቱ ማማሯ … አንተ ሥራው እንኳን ቢቀር፣ ሙሉ አካል ይዘህ ደህና ሴት ጓደኛ አታደርግም! ዝም ብለህ ከዚች ከቦጋለች ልጅ ጋር ትጓተታለህ! …ይኼን የማሳይህ ሮጥ ሮጥ ብለህ ሥራ እንድትፈልግ ለማነቃቃት ነው ….ለሌላ አይደለም …››

ምርር አለኝ …‹‹ አጎቴ! …ለምንድነው አንዴ እግር አንዴ እጅ የሌላቸው ሰዎች እያመጣህ የምትነዘንዘኝ? …እዚህች አገር ላይኮ ደህና ዘመድ ካለህ ፣ እንኳን እግርና እጅ ጭንቅላት ባይኖርህ ራሱ ጥሩ ሥራ ታገኛለህ! ›› ብዬ አጎቴን በቆመበት ትቼው ወደኋላዬ ተመለስኩ።
ከኋላ ድምፁ ይሰማኛል ‹‹እኔ እንድትነቃቃ ብዬ ነው አብርሃም …››

One Comment

  • yonasbirhanu17@gmail.com'
    yonas birhanu commented on September 20, 2022 Reply

    ግሩም እውነት አሌክሶ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...