Tidarfelagi.com

የአገር ፍቅር በቪያግራ !?

ምን ሰለቸኝ ? ፉከራ! ታዝባችኋል ግን ? በቃ ወጣቱ ሁሉ በየመድረኩ ነጭ ልብሱን ለብሶና አናቱ ላይ ባንዲራ አስሮ እየተንዘረዘረና ዱላውን እየወዘወዘ ዘራፍ ማለት ሆነኮ ስራው ! ጭንቅላት ባንዲራ ስለታሰረበት አይለወጥም! ባንዲራም አናት ላይ ሰለታሰረ ከፍ አይልም! ጭንቅላት በትምህርት እና ዊዝደም ሲያድግ ግን በዜጎች ከፍታ ባንዲራ ከፍ ይላል ! አገር ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ትላለች!! ከዚህ ውጭ በባዶው ስትጎደራ ብትውል በተወደደ እህል የበለሃትን ቁርስና ምሳ በከንቱ ማቃጠል ነው ትርፉ !

እንዴት ልበልህ ስለልማት ፎክረህ ህዝቡን አነሳሳህ እንበል ፣ ያነሳሳሃው ህዝብ እልፍ ሳይልይቆማል ! ስንት ነገር ዘራፍ ብለን ጀመርን ስንቱንስ ዘራፍ ብለን በተነሳን ማግስት ተውንው?(የባለጌ ምሳሌ ልጨምርልህ ! ) የምትወዳትን ልጅ ሰታቅፍ ገና ስታያት ሁሉ ያለምንም ማነሳሻ ጅስምህ ይግላል አይደል? ችግር ካለብህ ግን ቪያግራ ሁሉ ወስደህ ጉዳይህ እድሜው አጭር ነው ! አገርህን ከወደድክ በየቀኑ የስራ ሰሜትህ እንደዛር እንዲነሳ አርቲሰቱም ፖለቲከኛውም ከቦ ሊያጏራልህ አይገባም! ፉከራ የተፈጥሮ ወኔውን ላጣ ልብ የሚሰጥ የቃል ቪያግራ በለው !
አንዳንዱ የአባቶቻችን ነው ይልሃል ! አባቶቻችን ስለፎከሩ የግድ መፎከር አለብን እንዴ ? ሳይፎክሩ የገነቡትን መከባበር ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር አሸቅንጥረን ፉከራቸውን ማንጠልጠል ያሳቅቃል! በነገራችን ላይ የአባቶቻችን ፉከራ የሚበዛው ለጦርነት ነበር ! ፉከራ ሁለት ዓላማ አለው ! አንድም የሰው ህሊና ሰው መግደል (ጠላትም ቢሆን) ስለሚከብደው ይራራል ! ይራራል በጦር ቋንቋ ይፈራል ማለት ነው! እንግዲህ ሰው መሞትን ብቻ ሳይሆን መግደልንም ይፈራል!

‹‹ሽ ገዳይ ›› ‹‹አንበሳ ገዳይ›› ‹‹በሌሊት ገዳይ ›› ‹‹ አልሞ ገዳይ ›› ገዳይ ገዳይ ….በሚል ቁሰቆሳ በደሉን አስታውሶ ገዳይ ቃታሰቦ አናት መበርቆስ ፣ ጦር የሰው ደረት ላይ መሸቅሸቅ ፣ በጎራዴ የሰው አንገት ቆርጦ መጣል እንዳይፈራ በፉከራ ሆድ ማስባስና ደሙን ማፍላት ግድ ይል ስለነበር የጦርነት አበረታች ዕፅ ሁኖ አገልግሏል !! ሁለተኛው የፉከራ ጥቅም ሳይኮሎጅካል ዋርፌር የሚሉት ዓይነት ነው ! ለጠላት ከዋናው ጦርነት በፊት ሞቅ ያለ ዛቻ በመላክ ወኔውን መስለብ! ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ !

እንግዲህ ዛሬ ለአንድነትም ፉከራ ፣ ለምግብም ፉከራ፣ ለእምነት ሁሉ የሚፎክሩ አሉ ! ዘራፍ በማለት ገነት ይገባ ይመስል ! የሆነው ሁኖ ዛሬ ላይ ወጣቱ ወኔው በዘራፍ ሳየሆን በእውቀት የሚነሳሳ መሆን ካልቻለ ወደየትም አንሄድም!አገሩን ለማልማት የአገር ፍቅር እንጂ ዘራፍ ጊዜው አይደለም ! ምንም የሚያስፎክር ነገር የለም! ለመጋጨትም ዘራፍ ፣ለመፋቀርም ዘራፍ ! አሁን ባለው ኮንቴክስት ይቅርና በድሮውም ጦር አውርድ ቢቸግር ነው! እስቲ ቆም ብለህ አስበው መሳሪያ ተሸክመህ ኪስህን በጥይት ሞልተህ ተኩሰህ የማትስት መሆንህን አወጅክ ! ከዛስ? እኔ ነኝ ያለ ያገሬን ጀግና ተኩስ ብትለው ወፍ ከሰማይ ያወርዳል ! ስለሚተኩሰው መሳሪያና ጥይት አሰራር ብትጠይቀው ግን ወፍ የለም !

በጥይት ውስጥ የሚፈጠረው የኬሚካል ሪአክሽን አንዳች አስማት ነው! ለዛውም የሚባል ነገር መኖሩን ካወቀ! የሆኖ ሁኖ አሁን ጀግና የምንለው ‹‹ጀግና›› ፊዚክስ አያውቅ ኬሚስትሪ በቃ መተኮስ ነው ! ዋናው ነጥብ ጥይትና ጠመንጃ የሚያመርቱ እጆች እንጅ በየሜዳው የሚተኩሱ እጆች የሚፎክሩበት ዘመን አይደለም !! የሄ እውነት የገባው አንድ ጀግና ጥራ ብትለኝ አፄ ቴውድሮስ እላለሁ ! አተኳኮሱን ለኛ ተውት አሰራሩን አሳዩን ሲል መይሳው ምን ማለቱ መሰለህ ? ቪዚክስና ኬሚስትሪውን አስተምሩን ፉከራው በቂ አለን!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...