Tidarfelagi.com

የአብሲት ተራ ወጎች

ልጅነቴ ከተጓዘባቸው ፈለጎች አንዱ ‘እንጀራ መሸጥ’ ነው። ቡታጅራ ውስጥ ‘ሶርሴ ተራ’ በምትባል የገበያ ቦታ የእማማን ለምለም እንጀራ ከፈላጊው ጋር አገናኝ ነበር። አንድ ሰው ለብቻው የማይጨርሰውን ‘ግብዳ’ እንጀራ [ውሻ በቁልቁለት የማይስበው የሚባልለትን] የብር አምስትና አራት ሽጬያለሁ። 5ቱ ሁለት ብር ሲገባም በዚያ ነበርኩ። ሶርሴ ተራ የልጅነቴ ወዝ ከነጠበባቸው ቦታዎች አንዱ ነው። እንጀራ ተራውን በስማቸው ያስጠሩት ወይዘሮ የተከበሩ ጠጅ ጣይ ነበሩ። ጠጅ ቤታቸውን ታከን ስለምንቀመጥ ነበር ‘ሶርሴ ተራ’ የተባለው።
~
እንጀራ ንግድ የእማማ የጠዋት እጣ ነው። ለረጅም ዓመት እንጀራ ሽጣለች። [እኔን አራስ ሆና ቤት ውስጥ ምግብ ትሸጥ ነበር። በየዓይነት በ 25 ሳንቲም። የሚገርመው ከምትሸጠው እንጀራ ለሯሷ አጥፋ ላለመብላት ‘በይጎድልብኛል’ ሳስታ ቃሪያ በጨው አጥቅሳ ‘በላሁ’ እያለች ያሳለፈቻቸው ቀናት ብዙ አሉ። ልጅ ይሉትን ችግኝ ያለ አባት ለማጽደቅ] ~
እንጀራ ለመጋገር ብዙውን ጊዜ የምትነሳው ለሊት ነበር። ውድቅት 9 ሰዓት። የጨለማ ፍርሃትና የድካም እንቅልፍ እንዳያሸንፋት አብሬያት ተነስቼ መጽሐፍ አነብላት ነበር። ራዲዮኗ ነበርኩ ማለት ይቀላል። [የሬዲዮ ሰውነት መሻቴ የተወለደው እዚያ ይሆን?] በተራው እኔን እንቅልፍ ሲያንጎላጀኝ እርሱዋ ተረት ትነግረኛለች። ኑረቴ በብዙ የተቃኘው በእርሷ ተረቶች ውስጥ ይመስለኛል።
~
የተራው ልጆች የእንጀራ መሸጫውን ቦታ ‘አብሲት ተራ’ እንለዋለን። ዛሬ ብዙ ቦታ የደረሱ የዚያ ተራ ወዳጆች አሉኝ። ብዙዎቹ ሴቶች ናቸው። አልፎ አልፎ የሚቀላቀሉኝ ወንዶችም ነበሩ። እናቶች ዋነኞቹ ናቸው።

እንጀራችንን ሳጠራ ላይ በላስቲክ ሸፍነን እናስቀምጥና ከላይ ዳንቴል አልብሰን ሰፌድ እንደፋበታለን። በጋሪ አልያም በጭንቅላታችን ተሸክመን ሊሆን ይችላል እዚያ የምናደርሰው። በጋሪ ያመጣነውን ራሳችን ስናወርድ ተሸክመን ያመጣነውን ደግሞ ሌሎች ያወርዱልናል። አንዳንዴ ከአናታችን ላይ ክንብል ብሎ መሬት ሊፈጠፈጥ ይችላል። [ገራሚው ነገር ንጹህ ጤፍ እንጀራ ከሆነ በቀላሉ አይቆረስም። ውህድ ካለው ግን እንኩሮ ነው የሚሆነው። ] ~
አቀማመጣችን በመደዳ ነው። ቡና ቤት በሉት። እንዳደራረሳችን ቦታ እንይዛለን። (እርግጥ ‘የእከሊት ነው’ የሚባሉ የማይደፈሩ ቦታዎችም ነበሩ) እኔ ብዙ ጊዜ በዓይን ፍቅር የልጅ ልቤን ከነደፈችው ጉብል ፊት መቀመጥ አበዛ ነበር። ሲበዛ ቆንጅዬ ነበረች። ፈጽሞ የማልረሳው ቅንድቦቿንና ሹሩባዋን ነው። እርሷ ቀርታ እናቷ ወይም እህቷ ሲመጡ አልያም የትምህርት ፈረቃ ተለያይቶ ሳንገናኝ ስንቀር ቅር እንዳለኝ እውል ነበር። [የት ደርሳ ይሆን አሁን?። መቼም እንደኔ ቆማ አትቀር። ሃሃሃ]

እንጀራ ፈላጊዎች ወደ አብሲት ተራ ሲመጡ ከአንድ እንጀራ አንስቶ እስከ ሙሉ ሳጠራ (ከ 50 እስከ 70 እንጀራ ይሆናል) ሊገዙ ይችላሉ። ይህም ማለት ለቤት ፍጆታ ከሚገዙት አንስቶ እስከ ሆቴል ቤቶች ያሉ ደንበኞችን ያጠቃልላል። ገዢው/ዋ ገና ሰፌድና ዳንቴላቸውን አልያም ፌስታላቸውን ይዘው ብቅ ሲሉ ከዳር እስከዳር የተቀመጡ እንጀራ ሻጮች። ‘ነይ ና። ና ነይ። ነይ ና። የእኔ እንጀራ ምርጥ ነው። ማኛ። ነጭ ጤፍ። ወፍራም። ደግሞም ሰፊ ነው። ተመልከት/ች። ‘ እያሉ ይጮሃሉ። እንጀራቸውን ይከፋፍታሉ። ገዢው እግሩ ይተሳሰርበታል። ግራ ይጋባል። እኔ እቴ.. አጠገቤ ደርሰው ‘እስኪ እንጀራህን’ ካላሉኝ በስተቀር ትንፍሽ አልልም ነበር። በጣም አይናፋር ነበርኩ። የነጭ ጤፍ፣ሰርገኛና ቀይ (ጥቁር) ጤፍ እንጀራዎች መሸጫ ቦታዎች የተለያዩ ነበሩ። ዋጋቸውም እንዲሁ።
~
ገዢው ከጠሪዎች መርጦ አንደኛዋ ጋ ጎንበስ ይላል። እንጀራው ይከፈትለታል። ከላይ ሁለት እንጀራ ተደፍቶ ስለሚቀመጥ ገዢው ሲመጣ ተገልብጦ መልኩን እንዲያየው ይደረጋል። ይህች የጭንቅ ሰዓት ናት። እንጀራ ሻጩ በጸሐይ በብርድና ዝናብ የተመረረ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም በምንም ሁኔታ ውስጥ እንጀራውን አጣርቶ ቤቱ መግባት አለበትና የገዢውን ትኩረት ለመያዝ የማያደርገው የለም።
~
ገዢ የእንጀራው ዓይን ክፍትፍት ያለ መሆኑን ያያል። [ዓይኑ የጠፋ እንጀራ እኮ መለስተኛ ቂጣ ነው.. ሃሃ] ነጭ ጤፍ ነው ሰርገኛ ይለያል። ‘አፍለኛ ነው፣ ‘ቆጮ ቆጮ ይላል’፣ ኮምጥጧል’ ። በሽታ ይለያል። ቀጥሎ ከላይ ያለውን እንጀራ መሃል ለመሃል ያጥፍና ወፍራም ነው ቀጭን እያለ በእጆቹ ይመዝናል። [እንጀራ የቆጮ ቁራሽ ካልሆንኩ የሚለው በሊጥ ማኖሪያው ዕቃ ውስጥ የሚዘቅጠው ውጋጅ ተደባልቆ ሲጋገር ነው]። አንዳንድ ደንበኞች የእንጀራውን ጠርዝ ቆርሰው እያኘኩ ቀጭ ቀጭ እንዳለው ያጣራሉ። [ጤፍ እብቅ ብቻ አይደለም.. አሸዋውም አይጣል ነው። ያው ሲነፋና ሲበጠር ግድ አልባ ከሆኑበት እንጀራው ቀጭ ቀጭ ይኖረዋል። ማዘር ይህን የምትለየው ከጤፍ ግዢ ጀምሮ ነው። ጤፉን ከጆንያው ላይ ቆንጠር ታደርግና በእጇ መዳፍ ታንጠረጥረዋለች። ሸካራ መዳፍዋ ብናኝ አሸዋ ከድቃቂ የጤፍ ፍሬ የሚለይ ሰፌድ ሲሆናት እያየሁ እገረም ነበር። ] ___________

ገዢው ለመግዛት ሲስማማ እንደ ግዢው ብዛትና እንደያዘው ዕቃ የእንጀራው አቀማመጥ ይለያል። ለምሳሌ ፌስታልና ዘንቢል ሲያመጣ እንጀራው መሃል ለመሃል ይታጠፍና ዳርና ዳሩ ወደ መሃል ገብቶ ሦስት ማዕዘን ቅርጽ እንዲይዝ እየተደረገ ዕቃው ውስጥ ይጨመርለታል። ትሪና ሰፌድ ከሆነ ደግሞ አስር አስር እየተቆጠረ ሰፌዱ ላይ ማስቀመጥ ነው።
~
አስር እንጀራ ቆጥሮ በሁለት እጅ ሰቅስቆ ማንሳትና ሳይቆረስ ሌላ ሰፌድ ላይ መዘርጋት እውቀትም ጥበብም ነው። መቆረስ የለበትም። በጣት መብሳትም ስንፍና ነው። እንደነገርኳችሁ ንጹህ ጤፍ ከሆነ በቀላሉ አይቆረስም። ሌላም ነገር አለ። የተጋገረበት ምጣድ ሰባራ መሆን የለበትም።
~
ለምግብ ቤት እንጀራ የሚገዙ ደንበኞች የሰባራ ምጣድ እንጀራ አይመርጡም። የተሰበረ ምጣድ ላይ የሚጋገር እንጀራ ጀርባው ላይ በሚኖር የጎመንዘር ፈለግ ይታወቃል። አንዳንዴ ይህ መስመር ጎልቶ እንዳይወጣ ምጣዱ በሽሮና ዘይት ይታሰሳል። አዲስ ምጣድ ማሟሸት ጊዜ ስለሚወስድና ‘እጅ የለመደ’ ምጣድ በቀላሉ መተው እናቶች ስለማይፈቅዱ የተሰበረውን ማስታመም ይቀናቸዋል።
____________

የአንድ እንጀራ ነጋዴ ትልቅ ግብ በሆቴል ኮንትራት መያዝ ነው። ገበያ ውስጥ መሸጥ ብዙ ችግሮች ስላሉት ለአንድ ምግብ ቤት እንጀራ ጋግሮ ማቅረብ እንደ ትልቅ ዕድል ይቆጠራል። ማዘር ብዙ ጊዜ ይሄ ዕድል ይገጥማት ነበር።
~
ከኮንትራት ደንበኞቻችን የማልረሳቸው የአልማዝ እናትን ነው። ምርጥ ሰው ናቸው። የሆሳዕና ተጓዦች ወደ ሸገር ሲሄዱ ቁርስና ምሳ ከሚበሉባቸው የከተማው ምግብ ቤቶች የአንዱ ባለቤት ናቸው። የማዘር የረጅም ጊዜ ደንበኛ ናቸው። ደንበኞቻቸውን የሚያስተናግዱት ጠዋት፣ ረፋድና ምሳ ሰዓት ላይ ስለሆነ ከማለዳ እስከ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ ሦስት ጊዜ እንጀራ አደርስላቸዋለሁ። ከገዳም ሰፈር ሆሳዕና በር ድረስ በጋሪ አልያም በጭንቅላቴ ተሸክሜ የምሄድባቸው መንገዶች ዛሬም በአዕምሮዬ ውስጥ እንደ ፊልም ይጠነጠናሉ። ረጅም ነው መንገዱ።
~
የአልማዝ እናት የዕለቱን ኃላፊነቴን ሳገባድድ ምሳ ያበሉኝና 60 ሳንቲም ይሰጡኝ ነበር። ሳንቲሞቹ ድፍን ሽልንግና አስር ሳንቲም ናቸው – ሁሌም ። ይህን ሲያደርጉ በልግስና ነው። የሰራሁት የቤቴን ስራ መሆኑን ልብ በሉ። 60 ሳንቲምን ከዚህ ወቅት የብር አቅም ጋር ካለካካችሁት ስህተት መስራታችሁ አይቀርም። በወሩ መጨረሻ ከእንጨት ባንክ ውስጥ ወጥቶ ሲቆጠር የአንድ ሸራ ጫማ ዋጋ ይችል ነበር። ካንጋሮ የሚባል እንደ ታኬታ ጉጥ ያለው ጫማ ፋሽን ነበር ያኔ። ምን እርሱ ብቻ Creation ባለ ሻማ ሱሪና ጃኬት። White horse ሱሪ። Frezer ጂንስ ሱሪ። Damage ጃኬት። ካራቴ ጫማ። ወዘተ። የ 60 ሳንቲም በረከቶች ናቸው። [ድሮ ድሮ በቆጣቢነት የሚደርሰኝ አልነበረም። ማዘር ለሰበሰበችው እቁብ ጸሐፊ ሆኜ (ሞኖፖሊውን ልብ በሉ) የደረሰው ሰው የሚሰጠኝን 5 ብር እዚያው እየጣልኩ በ 200 ብር silver tape የገዛሁበት ወቅት አይረሳኝም። ለቤታችን ታሪካዊና የበኩር ቴፕ ነበር። ሃሃ] ~
የማዘር እንጀራ ደንበኛ የነበሩት ሆቴሎች ብቻ አልነበሩም። መምህራን፣ የህክምና ባለሙያዎችና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ይገኙበታል። መ/ር አበበን አስታውሳለሁ። ሕፃናት አምባ ሰፈር፣ ዘለቀ የአብዮት አደባባይ ደንበኛችን ነበር ከወንድሞቹ ጋር፣ ኤደንና ጥሩዬ ደግሞ ሐኪሞች ናቸው። በጣም ቆንጆ ከመሆናቸው የተነሳ ለረጅም ጊዜ ቁንጅና የሐኪምነት መስፈርት ይመስለኝ ነበር። ሃሃሃ። ለሁሉም ቤታቸው የማደርስላቸው እኔ ነበርኩ።
____________

ሶርሴ ተራ የጫት ንግድ ከሚጦፍባቸው ቦታዎች አንዱ ስለሆነ እጅግ ብዙ በጎችና ፍየሎች ከስፍራው አይጠፉም። ታዲያ። የአብሲት ተራ ልጆች ፈጽሞ የማንረሳት አንዲት በግ ነበረች። አይጥማ መልክ ያላት። እንጀራ ለደንበኞች ለማሳየት ጎንበስ ከማለታችን ከየት መጣች ሳይባል ሳጠራው ላይ ትሰፍርና ሰባት ስምንት እንጀራ ትገምስልናለች። አስባችሁታል። ደንበኛው የመግዛት አፒታይቱ ሲቆለፍ። እንግዲህ ይህን እንጀራ መሸጥ አይቻልም። ጠቅልሎ ወደቤት መውሰድ እንጂ። [ዛሬ ሰይጣኗ ጎብኝታኝ ነበር እንላለን ቤት ስንገባ] ። ለተራው ልጆች በጊቱ ‘ሰይጣን’ ናታ። ‘መጣች መጣች’ ይባላል ገና ብቅ ስትል። ለማባረር ስንነሳ ሌላ በግ ይመጣል። ብዙ ጊዜ የዚህችው በግ ልጆች ነው የሚሆኑት። [ስትራተጂ ነድፈው የሚሰማሩ እኮ ነው የሚመስሉት] .. ሴቶች እግራቸውን አጥፈው ስለሚቀመጡ ብድግ ሲሉ እንጀራ የሸጡበት ሳንቲም መሬት ላይ ይዘራል። በጊቱ ቅድመ አያት እስክትባል አውቃት ነበር። የልጅ ልጅ ልጅ እስክታይ።
~
ሌላ ያልነገርኳችሁ። እማማ ለዚህ ስራዬ የምትከፍለኝ በሳምንት እሁድ 50 ሳንቲም ነበር። እርሱንም ‘ቡፋሎ ስታንስ’ ወደሚባለው የአሊ ቪዲዮ ቤት ሄጄ ‘120 ፕሮግራም’ አይበት ነበር። [አይ ማዘር። ከገበያ የተገዛ እህል ቤት አምጥቼ። የሚፈጭ እህል ወፍጮ ቤት አድርሼና መልሼ። እንጀራ ገበያ ወስጄ ሽጬ ተመልሼ.. አንዳንዴም እንጨት ለቅሜ.. ጉቶ ነቅዬ.. ምንዳዬ ‘ቼላ’ ወይም ‘ቼንች’ ብቻ ነበር። ሃሃሃ። ነፍፍፍፍፍፍ ፍቅሩ ሳይዘነጋ] ~
እስኪ ልጅነታችሁን ከትቡልንማ። በሌላ ጊዜ ‘የጋሪ ተራ ተረኮችን፣ የፉርኖ ተራ ወጎቼንና የጠላና አረቄ ቤት ጨዋታዎቼን’ ማንበባችሁ አይቀርም። ዛሬዬን የሰሩት ጡቦች እንደምን ያማሩ ናቸው!!!
~
ክብር አይሆኑ ሆነው ሰው ሊያደርጉን ለሚታትሩ እናቶቻችን!!
~
መልካም አሁን!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...