Tidarfelagi.com

የአርሲ ዐጃኢባት

እኛ (እደግመዋለሁ “እኛ”፣ “ኑቲ”፣ “ናህኑ”) የኢትኖግራፊ ፈረሳችንን ተሳፍረን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከመሀል እስከ ሰሜን መጋለብ ሱስ የሆነብን ጸሐፊ ከሀረር መሆናችንን ታውቃላችሁ አይደል? ታዲያ እኛ (አሁንም እደግመዋለሁ “እኛ”) ወደ ሌሎቹ ስፍራዎች ስንጋልብ የነበረው ከሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የሚቀርበንን አንድ ጎረቤታችንን እያለፍን ነው። ይህ ጎረቤታችን በቅናት ያልተበከለ ደግና ቸር በመሆኑ ወደ ሌሎች ስፍራዎች በምናደርገው ጉዞ ብዙም ቅሬታ አይሰማውም ነበር። ምልልሳችንን በጣም ስናበዛው ግን የኦሮሞን ባህል እየጠቀሰ፣ አብሮ የመኖር ደንቦችን እየመዘዘና የሰው ልጆችን የማህበራዊ ኑሮ ወጎች እንደ ምስክር እየነቀሰ ቅሬታውን እንዲህ ሲል አሰምቷል።

“ጓድ አፈንዲ! በክፉም በደጉም በጣም የምንቀርባችሁ እኛ ነን እኮ”
“አቤት ጎረቤቴ! አንተማ የኔ ነህ ብዬ ነው እኮ”
“ቢሆንም….”

እውነቱን ነው። አንድ ቀን ሌባ ወይንም ጂንኒ አንቆኝ ብጮኽ በቅድሚያ ሊረዳኝ የሚጣደፈው ጎረቤቴ ነው። ኮሳሳ ጎጆዬ ቢቃጠልብኝ ከእሳት አደጋ መከላከያ በፊት እየሮጠ ከእሳቱ ጋር ግብግብ የሚገጥመው ጎረቤቴ ነው። ወደፊት ፈጣሪ ብሎልኝ ሰርግ ብደግስ ለእንግዶች ማረፊያ ለመስጠት ከማንም ቀድሞ የሚተባበረኝ ጎረቤቴ ነው። ስለዚህ ጎረቤቴ በኔ ላይ ከባድ ሐቅ አለው።

እንግዲህ ጥሪውን ተቀብለናል። ፈረሳችንን ጭነን ከሚጨታ ማዶ ያለውን ጎረቤታችንን ልንዘይረው ተነስተናል። ቼ…ቼ…. ቼ! ፈርዳ ጮሌ….!! ቼ ፈርዳ ኮ ሚቹ!!

Arsii Arsiyyoo yaa hawwii keennaa (አርሲ አርሲዮ አንቺ ምኞታችን)
Siif dhufne yaa biyyoo teennaa (መጥተንልሻል አንቺ ሀገራችን)

አዎን! ዛሬ አርሲን ልንዘይር ነው! ዛሬ አሰላን ልናያት ነው! ዛሬ በቆጂን ልናወሳት ነው! ዛሬ ሳጉሬን ልንከልማት ነው! ዛሬ አሳሳን ልናደምቃት ነው! የዛሬው የኢትኖግራፊ ግልቢያችን ወደ አርሲ ነው! እዚያ ምድር ብዙ ተአምራት አለ!! እዚያ ምድር ብዙ ዐጃኢባት አለ!! እዚያ ምድር ብዙ በረከት አለ!! እዚያ ምድር ብዙ ታሪክ አለ! እዚያ ምድር ብዙ ወግና ጨዋታ አለ!!

“መርቃ” (ገንፎ) እና “ጨጨብሳ”ን በኢማን እንዲገምጡ
ከተዋበው ምድር ወደ አርሲ ይምጡ።

እንዲህ ተብለን ነው በክብር የተጠራነው!! ልበ ቀናውና ለጋሱ የአርሲ ሕዝብ እጁን በግንባሩ ላይ እንደ ጃንጥላ ተክሎ “ገብተዋል ወይንስ አልገቡም?” እያለ በጉጉት እየጠበቀን ነው። ደግሞም ሌላ ግብዣ አለ እኮ ጓዶች!!

Ashoo Ashillaan sigammachiisudhaaf (በ“አሾ-አሺላ” ቶሎ እንዳስደስትህ)
“Shamba Shamba” jedhee jaalalaan sijjeesuudhaaf (“ሻምባ! ሻምባ” ብዬ በፍቅር እንድገድልህ)
“Tirri Tirri` jedhee si booji’uuf qophawwe (ፀጉሬን በ“ቲርሪ” አዙሬ እንዳፈዝህ)
Daddafii naaf kottu garaan koo umnaawee (አረ ቶሎ ናልኝ በሞቴ ይሁንብህ።

“ዱብሬ አርሲ” (የአርሲዋ ኮረዳ) ናት ይህንን የሙሐባ መልእክት የሰደደችልን። ያቺ ቦንቱ ዱብሬ! ያቺ የአሰላ ሱካሬ! ያቺ ከረሜላ ማሬ! ያቺ ውብ የፍቅር ፍካሬ! ድምጿ የሚጥመው እንደ ወፍ ዝማሬ! ከጭላሎ ተራራ ግርጌ ባለው የአሰላ ሜዳ ላይ የ“አሾ-አሺላ”ን መወድሳዊ ትርኢት ልታሳየንና በ“ሻምባ” ኦሪጂናሌ ጥበብ ልታስጨፍረን ተሰናድታለች።
—–
አርሲ ደርሳችሁ የነገሮች ውል ጠፍቶአችሁ በግርታ “በዘበዛ” እንዳትሆኑ በማለት በ“ሻምባ” እና በ“አሾ-አሺላ” ዙሪያ አንዲት ኦሬንቴሽን አዘጋጅተንላችኋል። በቅድሚያ እዚሁ እያለን ያቺን “ኦሬንቴሽ”ን ገረፍ ገረፍ እናደርጋትና ጉዞአችንን እንቀጥላለን (አብሽሩ!! አጭር ናት። እንደ ካድሬ ኦረንቴሽን በማራቶን ወሬ ጆሮአችሁን አንጠርበውም)።

“አሾ-አሺላ” የአርሲ (ባሌንም ይጨምራል) ሴቶች ብቻ የሚታደሙበት ባህላዊ ጨዋታ ነው። ሴቶቹ ጨዋታውን በቡድን ነው የሚጫወቱት። ይህ ጨዋታ ቀዝቀዝ ባለ ምት የሚሄድ ነው። የጨዋታው ታዳሚዎች እጆቻቸውን እያነሱ ከማውረድና የተለያዩ ግጥሞችን በመዘማመር ወደ ኋላና ወደፊት ከመመላለስ በስተቀር ሰውነታቸውን እየነቀነቁ አይጨፍሩም። በመሆኑም የጨዋታው “መቅኒ” የሚገኘው በጭፈራው ላይ ሳይሆን በግጥሞቹ መልእክት ውስጥ ነው።

በዚሁ የአሾ-አሺላ (“ላ” ይጠብቃል) ጨዋታ የሚታደሙ ሴቶች ስለጾታዊ ፍቅር አያዜሙም። የጨዋታው ግጥሞች ተፈጥሮን፣ ማህበራዊ ህይወትን፣ የዕለት ተዕለት ኑሮን፣ ልጆችን፣ ጓደኝነትን፣ መልካም ስነ-ምግባርን፣ የፈጣሪ ጸጋዎችን ወዘተ… ነው የሚያወድሱት። በተለይም የአርሲና የባሌ ሴቶች እንደ ሀብት መለኪያና ዋነኛ የተፈጥሮ ፀጋ የሚቆጥሯቸውን ከብቶቻቸውንና በየዕለቱ ከነርሱ ጋር የሚያደርጓቸውን ውጣ ውረዶች በአሾ-አሺላ ግጥሞች ማንፀባርቅን በሰፊው ተክነውበታል። በጨዋታው ያገቡትም ሆነ ያላገቡ ሴቶች መሳተፍ ይችላሉ።

“ሻምባ” ሌላኛው ታዋቂ የአርሲ ባህላዊ ጨዋታ ነው። በዚህኛው ጨዋታ የሚታደሙት ያላገቡ ኮረዶች ሲሆኑ ጨዋታውን የሚጫወቱት ደግሞ በወጣት ወንዶች ተከበው ነው። ኮረዶቹ ሻምባን በሚጫወቱበት ጊዜ በእጃቸው በአራት ማዕዘን ቅርጽ የተሠሩ ሁለት ትናንሽ እንጨቶችን ይይዙና እነርሱን እያጋጩ ለጨዋታው ድምቀት ይሰጣሉ። ወንዶቹ ደግሞ በፉጨት ጭፈራውን ሞቅ ደመቅ ያደርጉታል።

ታዲያ በዚያ መሀል አንድ የማይዘነጋ ትእይንት አለ። ይህም ኮረዶቹ ተራ በተራ እየወጡ ራሳቸውን በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር ጸጉራቸውን የሚያዘናፍሉበት ድርጊት ነው። “ሻምባ” ማለት እንዲህ ዓይነቱ ጨዋታ ነው እንግዲህ። ብዙ ጊዜ በቴሌቪዥን አይታችሁት የለ?… አዎን! እርሱኑ ነው በቃላት የጻፍኩት።
——-
አሁን ተነቃነቁ ጓዶች!! ፈጠን በሉ! ፍጠን ፈረሴ! ቼ በል ፈረሴ!! ጉዞአችን ወደ አርሲ ነው!! ዳይ…ዳይ..ዳይ..ዳይ…ዳይ!!

ከላይ ወጌን ስጀምር “ከሚጨታ ማዶ ያለው ጎረቤታችን” ነበር ያልኩት አይደል? ልክ ነኝ። አልተሳሳትኩም። አባቶቻችን የሚሉትን ነው የደገምኩት። ደግሞም እውነታቸውን ነው የተናገሩት። መቻራና ሚጨታ የሀረርጌ ምድር ማብቂያ ነው። ከሁለቱ ከተሞች ጀርባ ያለውን የጉጉ ተራራ (አርባ ጉጉ) ስንወጣ ሀረርን ጨርሰን ወደ አርሲ ክልል ገባን ማለት ነው። የጥንቱም ሆነ የአሁኑ ጂኦግራፊ የሚለው እንደዚያ ነው።

ይህንኑ ጂኦግራፊ ተከትለን ዚያራችንን እናስኪደው እንዴ? ደግ! እንዲያውም መንገዱ አጭር በመሆኑ ቶሎ እንደርሳለን። ስለዚህ ፈረሳችንን “ቼ!” ብለነዋል። ቼ ፈረሴ! ቼ ነፍሴ! “ጮሌ ኮ” እባክህ ቶሎ ድረስ! እኛም በጊዜ ደርሰን የአርሲን “መርቃ” እና “ጨጨብሳ” እንድንጎርስ፣ አንተም የአርዳይታን እና የሲሬን ገብስ እስኪበቃህ ድረስ እንድትቆረጣጥም ቶሎ ሰግረህ የልባችንን አድርስ!! ቼ..ቼ… ፈርዳ ኮ!!
——
ለኪ! ለኪ! ለኪ!!! “ሀርዳን ዋ ዸገዬ” አለ የአርሲ ሰው (“ዛሬ ነው ጉድ የሰማሁት” ማለቱ ነው)!! ወደፊት መግፋት አልተቻለም ጓዶች! ወቅቱ ክረምት መሆኑን ዘንግተነው ነበር ለካ! ይኸው እንደምታዩት ወደ አዋሽ የሚወርደው ትልቁ የኤጀርሳ ወንዝና የዋቤ ሸበሌ ዋነኛ ገባር የሆነው የሸነን ወንዝ ሞልተዋል! ስለዚህ በዚህ በኩል ሊሳካልን አልቻለም። እርግጥ የሚቀረን ነገር ከሁለቱ ወንዞች በአንደኛቸው ላይ ዘለን ወደ አርሲ ምድር “ጨለው” ብሎ መግባት ብቻ ነበር። ነገር ግን ወደፊት ከገፋን ባለግርማ ሞገሱን ፈረሳችን ተፈናጥጠን በፈረሰኛ ውሀ ከተወሰድን በኋላ እንደ ግሪካዊው ዚቶ “በፈረሱ ባሕሩን ሊዋኝ የሞከረ ጅል” የሚል ስነ-ቃል (mythology) በኛ ስም እንዳይፈጠርብን ያሰጋናል። ስለዚህ ፊታችንን ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ መልሰን ጉዞአችንን በአዋሽ “መልካ-ሰኣ” መንገድ ማድረግ ግዴታ ሆኖ ተገኝቷል!!

እነሆ በፈረሳችን እየሰገርን “መልካ ሰኣ” ደረስን!! በሜዳው ከሚቦርቁት የአርሲ ላሞች የታለበውን ትኩስ ወተት ተጎንጭተን አለፍን! “ሶደሬ” (ሶዳ ሬኤ) ደረስን! ገላችንን በፍልውሀው ታጥበን ድካማችንን ካቃለልን በኋላ አለፍን። ዼራ ደረስን! የመጫና ቱለማ ማህበር መሥራች አባቶች የነበሩት እነ ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ እነ ኃይለ ማሪያም ገመዳ! እነ ዓለሙ ቂጤሳ፣ እነ ማሞ መዘምር! እነ ሐጂ አደም ሳዶ! እነ ቀኛዝማች ዐብዱል አዚዝ አሕመድ! እነ ሼኽ ሑሴን ሶራ ወዘተ….የአርሲ ህዝብ ታላቅ አባት በነበሩት ሐጂ ሮበሌ ቱሬ እና በሌሎች የኦሮሞ ሽማግሌዎች ተጋብዘው በመቶ ሺህ ህዝብ ፊት “ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር የምናደርገውን ትግል ላናቆመው ቃል እንገባለን” በማለት ኪዳን ያሰሩበትን ስፍራ እየገበኘን ታሪካቸውን ከተማርን በኋላ አለፍን።

አርዳይታ ደረስን! ቃል በገባነው መሠረት በግልቢያው መደካከም ለጀመረው ፈረሳችን ለምለሙ የአርሲ መሬት ያፈራውን ገብስ ዘገን አድርገን በመስጠት አነቃቃነውና ጉዞአችንን ቀጠልን። ሲሬ፣ ጎንዴ፣ ኢተያ፣ ሳጉሬን በተከታታይ አየን። በወጣት ዕድሜአቸው የተንደላቀቀ የምቾት ኑሮአቸውን ትተው ለሕዝባቸው መብት መታገልን ምርጫቸው ያደረጉትንና ለወጡለት ዓላማ ክቡር ህይወታቸውን የሰውትን መገርሳ በሪን (በሪሶ ዋቤ)፣ ቃሲም ሑሴንን (ነዲ ገመዳ) እና ጀማል ሮበሌን (ጉተማ ሀዋስ) የመሳሰሉ የአርሲ ጀግኖችን በዐይነ ህሊናችን እያስታወስን አለፍን።
——
አዎን! አዎን! ከዱብሬ አርሲ ጋር በሻምባ የምንቦርቅበት ቀጠሮ እንዳያመልጠን ወደፊት ሽምጥ ጋልበናል። እንደ ዐረቢያው ሐኒድ የሚሳበውን የአርሲ “መርቃ” መጎረስ ያማረው ጉሮሮአችን አስር ጊዜ ምራቅ እየዋጠ ጉዞአችንን ቀጥለናል። አብሽር ፈረሴ! ወደ ተዋበው የአሰላ ሜዳ እየደረስን ነው።

ቼ….ቼ..! ቼ!! ግፋ.. ግፋ ግፋ ፈረሴ! ጉዞህን ቀጥል! ልጓምህን እንዳትጥል! በሁሩታ ስንዴ ዕድሜህ እንዲቀጥል! ፈረሴ ቀጥል! ልጓምህን እንዳትጥል! ኦውውውውውው!! ያ ሰላም!! በዚህም መንገድ ክረምቱ ጉድ ሰርቶናል። የጉዞአችንን የመጀመሪያ ምዕራፍ ከምናሳርግበት ስፍራ ከመድረሳችን በፊት ሌላ ተግዳሮት ገጥሞናል።

እንደምትመለከቱት በኢትዮጵያ በከፍታው አራተኛ የሆነው የጭላሎ ተራራ በኃይለኛ ጉም ተከቧል። ጉሙን ሰንጥቀን ወደፊት ማለፉ አስቸጋሪ ሊሆንብን ነው። እኛ ብናልፈው እንኳ ለቦሐርቲ (መዝናኛና ፍንደቃ) የቀጠረችንን “ዱብሬ አርሲ”ን ላናገኛት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ምን መሰላችሁ? በአርሲ ህዝብ ሰፉ (የስነ-ምግባር ደንብ) መሠረት ጭላሎ በጉም ከተከበበ “ዱብሬ አርሲ” ለአሾ-አሺላም ሆነ ለሻምባ አትወጣም። ጉሙ ተራራውን የሚከበው ዜጎች የፈጣሪ (ዋቃ) በረከት የሆነውና የሰዎችንና የእንስሳትን ህይወት የሚያስቀጥለው ዝናብ እየመጣ እንደሆነ አውቀው ዝናቡ የሰላምና የበረካ እንዲሆንላቸው እንዲለማምኑ ምልክት ለመስጠት ነው ይባላል። በዚህ ጊዜ ሁሉም ልቡን ወደ ፈጣሪው መመለስ አለበት። “ዱብሬ አርሲ”ም የህብረተሰቡ አካል ስለሆነች ይህንን ደንብ ታከብራለች። ስለዚህ በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ ከቤት ወጥታ “ሻምባ” እና “አሾ-አሺላ” አትጫወትም።
——
ታዲያ ምን ተሻለን? ጭላሎን የከበበው ጉም “ዱብሬ አርሲ”ን ከቀጠሮአችን ሊያስቀርብን ነው እኮ! እንዲያው ብዙ ኪሎ ሜትር እየጋለብን የመጣን ዘመድ ጠያቂዎች መሆናችንን ተረድቶ እንኳ በዛሬው ዕለት የተሰጠውን ዝናብ የመጥራት ግዳጅ ለሌላ ጊዜ አያስተላልፈውም ማለት ነው?

አህ!! ልባችን መለስ ብሏል (እፎፎፎይ)!! አንድ መልእክት ከውስጠ አዋቂዎች ደርሶናል። መልእክቱም “ጭላሎን በሙሐመድ ጠዊል ዜማ አናግሩትና ሐሳቡን እንዲቀይር አድርጉት” የሚል ነው። ብራቮ! ፎርሙላው ተገኝቷል! ኧረ እንዲያውም “ዱብሬ አርሲ”ን የምናናግርበት ሐረግም አብሮ ዱቅ ብሏል! እንዴት ደስ ይላል?

እነሆ የጠዊልን ዜማ አንድ ላይ ልንዘምረው ነው።

Hurrii Gaara Cilaaloo saaqami mee (አንተ ጭላሎን የከበብከው ጉም ተገለጥልኝ)
Dubree Arsii onnee tee naaf bani mee (አንቺ “ዱብሬ አርሲ”ም ልብሽን ክፈችልኝ)

መገን! መገን! መገን! ጭላሎ ቃላችንን ሰምቶ እንደ ገለምሶው “ጋራ አባ ያያ” ተራራ ግልጥልጥ አለ። “ዱብሬ አርሲ”ም ጥሪያችንን ስትሰማ ቀጠሮአችን ትዝ አላትና ከተፍ አለች!!
መጣች ዱሬቲ! መጣች ቦሀሬ! መጣች አያንቱ! መጣች ኤለምቱ! መጣች ሌሎ! መጣች ሀመርቲ! መጣች መርዲያ! ጸጉሯን “ሻምባ! ሻምባ! ሻምባ!” እያደረገችው ዓለምን ጉድ ልታሰኘው ከአሰላ ጥግ ወዳለው ለምለም መስክ ወረደች።

Mee tarree gali bakka kee (እስቲ ተሰለፊ በቦታሽ)
Mee kottuu himi yaada kee (እስቲ ተናገሪ ከትዝታሽ)
Ee tolee tole waa tolee (እንዴት ግሩም ሆኗል ግሩም)
Mee Shambaa godhi yuuba kee (እስቲ “ሻምባ” አድርጊው ሹሩባሽን)
Shambaa (ሻምባ)
Shambaa (ሻምባ)
Shambaa (ሻምባ)
Shambaa (ሻምባ)
—-
(ይቀጥላል)
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 10/2009
በሸገር- ተጻፈ።

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...