Tidarfelagi.com

የትርፍ ጊዜ ሥራ ( ክፍል ሁለት) 

– ቀሚስሽ በጣም ያምራል አለች ገነት ምግብ ቤቱ ውስጥ ገብተን እንደተቀመጥን።
– ይሄ? አልኩ በመገረም ቀሚሴን እያየሁ። ተራና ረዘም ያለ ነጭ ቀሚስ ነው የለበስኩት።
– አዎ…ቅልል ያለ ነው…ለነገሩ ከመስቀያው ነው…አለች አተኩራ እያየችኝ።

(በተሰቀልኩ። እዚሁ እንዳለሁ ተሰቅዬ በሞትኩ!)

ፈገግ ብዬ አቀረቀርኩና ዝም አልኩ።

አስተናጋጅዋ መጥታ ፊታችን ቆመች።
– ምን እንብላ ፍሬሕይወት? አለች ገነት የምግብ ዝርዝር የያዘውን ትልቅ ወረቀት አገላብጣ እያየች።
– ደስ ያላችሁን…እኔ ሃይለኛ ቁርስ ነው የበላሁት…ብዙም አልራበኝ….አልኩ።

ሶስት ምግብ አዘዘች።

– ገኒ ሶስት ምግብ አይበዛም? አለ ደቤ።
– ከሚያንስ አይሻልም? ሚጠጣስ ምን ይምጣልሽ ፍሬ?

(ፍሬ? ፍሬ ነው ያለችኝ? ጭራሽ ታቆላምጠኝ ጀመር? የህግ ባሏን ውሽማ እንደምታቆላምጥ ብታውቅ ምን ትል ይሆን? …አይደለም። ውሽማ አይደለሁም….ውሽማ አልባልም….በጎን በኩል ያለሁ ሚስት ነኝ…ሚስት።)
– እ..? ውሃ….አልኩ
– በቃ ሁለት ሊትር ውሃ ከውጪ….ብላ አዘዘች።
ገነት ፣ አስተናጋጇ እንደሄደች ህጻን ልጅ አኩርቶ ሊይዝ ከሚችል ትልቅ ቦርሳዋ ውስጥ ሚጢጢ የምሳእቃ አወጣች። በመገረም አየኋት። ጥያቄዬ እንደገባት ሁሉ
– ለማርኮን ነው…የውጪ ምግብ አይስማማውም…ና ማሬ….አለችና ልጇን ከነተቀመጠበት ወንበር ጎትታ አስጠግታው ምሳ እቃውን ከፈተች።
መኮረኒ።

ራሴን በገባኝ ነቅንቄ ወደ ደቤ አየሁ። አቀርቅሯል። ወደ አርሴማ ዞርኩ። አቀርቅራ ስልኳን ትጎረጉራለች።

ገነት ልጇን ጉረስ አትጉረስ እያለች ትታገላለች።

ሰአት መሄድን አሻፈረኝ ብሎ የቆመ፣ ጊዜ አልሄድ ብሎ የተገተረ መሰለኝ።
በረጅሙ ተነፈስኩ።ሰመመን ላይ ያለሁ፣ በህልም አለም ውስጥ የምመላለስ መሰለኝ።

ማርኮን –
– ማማ…እሷ ታብላኝ…. ብሎ እየጮኸ ትንሽ እጁን ወደኔ ሲጠቁም ነቃሁ።
– አይሆንም አርፈህ ብላ….ብላ ማንኪያ ወደ አፉ ሰደደች
– እምቢ…እሷ ታብላኝ…..ለቅሶ ጀመረ።

(ወይ ታሪክ…)

– ወዶሻል መሰለኝ…..አለ ደቤ ወደኔ ዞሮ….
– ስጪኝ አበላዋለሁ …አልኩ ነቃ ብዬ
– ተይው…ሲቀብጥ ነው…ያስቸግርሻል….ገነት ልጇን በመቆጣት እያየች መለሰች
– ችግር የለውም ስጪኝ…
– ተይ…?
– ግዴለም ገነት…አምጪው ላብላው….
– ምሳ ብዩ ብዬ አምጥቼሽ ሞግዚት አደረኩሽ እንግዲህ…
– አረ ችግር የለውም

ማርኮን ተንደርድሮ መጣና ጭኖቼ ላይ ተቀመጠ።

ደቤ ፈዝዞ ያየናል።
– እሱ ሰው አንዴ ከወደደ እንዲህ ልጥፍ ነው….ቻይው እንግዲህ…አለች ገነት…
– ችግር የለም

(ባልሽን እየተሸማሁሽ ቢያንስ ልጅሽን ልመግብ እንጂ የኔ እናት….)

ማርኮን ስጎ የበዛበትን መኮረኒ ቶሎ ቶሎ መጉረስ ጀመረ። በመሃል እየሳቀ ቀና ብሎ ያየኛል። የአባቱ እና የእናቱ ግሩም ቅልቅል ቆንጅዬ ልጅ ነው።
– አ….! ስለው ይስቃል።አፉን ይከፍታል። ይጎርሳል። ያኝካል። ይውጣል። ከዚያ ደግሞ መልሼ አ! ስለው ይስቃል።

ማር ነገር።

– ይገርማል ለማንም እንዲህ አይበላም እኮ በጣም ቢወድሽ ነው…አለች ገነት እየሳቀች።

(መጀመሪያ ባልሽ አሁን ደግሞ ልጅሽ…ቻይው እንግዲህ አንቺ መልካም ሴት። ቻይው።)

ትንሽ ቆይቶ፤ የመጨረሻዎቹን ጥቂት መኮረኒዎች ላጎርሰው ስሞክር በቃኝ…! አለና እጄን ሲመታው ሁለት መኮረኒዎች ከነብዙ ቀይ ስጓቸው ቀጥ ብለው የት ሄዱ? ነጩ ቀሚሴ ላይ። ገነት የወደደችው ነጭ ቀሚሴ ላይ።

ጭቦ መሰለኝ።

– ማርኮን! ና…ና ወደዚህ…ፍርዬ ወይኔ…በጣም ይቅርታ በናትሽ…በጣም ይቅርታ….. አለች ገነት እየተርበተበተች።
– ችግር የለውም….ብዬ መኮረኒዎቹን በእጆቼ አነሰሳሁና ቀዩን ስጎ ለማስለቀቅ ሞከርኩ። ስፈትገው ጭራሽ አሰፋሁት።
– ኖ ኖ…በውሃ ይሻላል…ቆይ ውሃ ታምጣልሽ…አስተናጋጅ….!

ገነት በሰው በተሞላው ትልቅ ምግብ ቤት መሃል ጥሪዋን ሰምቶ የሚመጣ አስተናጋጅ ስታጣ ራሷ ተነስታ ሄደች። ውሃ ልታመጣ።

(ምስኪን። የምስኪን ጥግ።)

ራቅ ስትል ደቤን አየሁት። ስሜት በማይታይበት ሁኔታ ደንዝዞ ያየኛል።
ወደ አርሴማ ዞርኩ። አሁንም ስልኳን ይዛ እንዳቀረቀረች ነው።

– ደቤ….ልሂድ እኔ…አልኩት ቀስ ብዬ…
– እንዴ? ምግብ ሳይመጣ? ምን እንድታስብ ነው…..? አለኝ

ሳልመልስለት ገነት ውሃ ከያዘች አስተናጋጅ ጋር እየተጣደፈች ተመለሰች።

– ሽንት ቤት አይሻልም? አለች አስተናጋጇ በስጎ የተበላሸውን ቀሚሴን ስታይ። ሰው ትን ብሎታል ተብላ ስትሮጥ ውሃ ያመጣችና ቀሚስ ለማስለቀቅ መሆኑን ስታውቅ ቅር የተሰኘች ትመስላለች።
– ልክ ናት…እዛ ሄጄ ባስለቅቀው ይሻላል…አልኩና ተነሳሁ- ለጥቂት ደቂቃዎች ከዚህ መጥበሻ ላይ መውረድ በመቻሌ እፎይታ ቢጤ እየተሰማኝ።

ገነት ራሷን በእሺታ ነቅንቃ ስትቀመጥ ደቤ ተከትሎኝ መጣ።

ማመን አልቻልኩም። ምንድነው ሚሰራው?

– እጄን ታጥቤ መጣሁ እኔም….አለ ጮክ ብሎ

(ወይ እጅ መታጠብ። )

ሽንት ቤቱ የወንዶችና የሴቶች ተብሎ የሚከፈልበት ኮሪደር ጋር ጠበቅኩት።
እንደደረሰ ጮህ ብዬ-
– ጭራሽ ትከተለኛለህ? አልኩት
– እጄን ልታጠብ ነው አልኩ አይደል?
– ብትልስ?
– ማለት?
– ብትጠረጥርስ?
– ምንድነው ምትጠረጥረው? ሰው አብሮ እጅ አይታጠብም እንዴ?

ዝም ብዬ አየሁት።
– ምን ሆነሻል? አለኝ እጆቹን ዘርግቶ።
ሊነካኝ ነው? ሚስትና ልጆቹን በሜትሮች ርቀት አስቀምጦ ሊነካኝ ነው?
– እንዳትነካኝ! ብዬ ጮህኩ
– ምን ሆነሻል?
– ምን ሆነሻል ብለህ ትጠይቀኛለህ? ሲኦል ውሰጥ ከተኸኝ?
– አይ ኖው ደስ የሚል ነገር አይደለም ግን ይሄን ያህል ምነው?
ዝም ብዬ አየሁት።
– ፍሬ….አለኝ አሁንም ሊነካኝ እጆቹን ዘርግቶ
– በናትህ እንዳትነካኝ! ብዬ ሸሸሁት
– ምንድነው እንዲህ የሚያደርግሽ…የማታውቂው ነገር ተፈጠረ? ሚስትና ልጆች እንዳሉኝ ታውቂ የለም?

እውነቱን ነው። አብሬው መተኛት ከመጀመሬም በፊት ሚስትና ሁለት ልጆች እንዳሉት አውቅ ነበር። የሚስቱን ስም አውቅ ነበር። የልጆቹን እድሜና ስም አውቅ ነበር። ከሚስቱ ጋር ለአስራ ሁለት አመታት በትዳር እንደኖረ አውቅ ነበር። ከአስራ ሁለቱ ስምንቱ ጥሩ፣ አራቱ ደግሞ የደባልነት እንደሆኑም አውቅ ነበር።
– እ? አለኝ
– አውቃለሁ እሱማ…
– ታዲያ ምንድነው እንዲህ ያስደነበረሽ?

ምንድነው እንዲህ ያስደነበረኝ?

አገኘኋቸዋ! ተዋወቅኳቸዋ!
ሳላገኛቸው በፊት አሃዝ ነበሩ። አንድ ሚስት ሁለት ልጆች። ቁጥር ብቻ። ስም ያላቸው ቁጥሮች። ከዚያ ባለፈ ስለነሱ አስቤ አላውቅም ነበር።

ከባሏ ጋር በየሆቴሉ ስጋደም ስለ ሚስቱ መኖር እንጂ ምን አይነት ሰው እንደሆነች ለማሰብ ሞክሬ አላውቅም። የዋህ እና ደግ ሴት ትሆን ይሆን ብዬ ገምቼ አላውቅም። እኔን መርጦ ጥሏት ቢሄደ ትጎዳ ይሆን ብዬ አስቤ አላውቅም። ለፍታ ስላቀናችው ትዳር፣ ደክማ ስላቆየችው ጋብቻዋ፣ ስለ መልካም ሚስትና እናትነቷ በፍፁም አስቤ አላውቅም።

ልጆቹስ?

ሁለት ስለመሆናቸው፣ በደምሳሳው በአባትነት እንደሚወዳቸው እንጂ አብሬው በመሆኔ የአባታቸውን ጊዜ እንደተሸማሁባቸው ገምቼ አላውቅም። ጨዋና ሰው ወዳድ፣ እናታቸውን የሚታዘዙ ቆንጆ ልጆች ስለመሆናቸው አስቤ አላውቅም። እኔን መርጦ እናታቸውን ቢተው ስሜቷ በተጎዳ እናት እና ያለ አባት ወይ ደግሞ ነጋ ጠባ በሚደበድባቸው እንጀራ አባት የማደግ እጣ ፈንታ ላይ ልጥላቸው ስለመቻሌ አስቤ አላውቅም።

– ፍሬ! መልሺልኝ እንጂ…የት ሄድሽ? አለ ደቤ።
– ሚስትህና ልጆችህ ጋር ሂድ…ልብሴን አስለቅቄ መጣሁ አልኩና ሴቶቹ ክፍል ገባሁ። እንደገባሁ ቀሚሴን ማስለቀቄን ትቼ ማልቀስ ጀመርኩ።

ለቅሶዬን ጨርሼና በደንብ ያልለቀቀ ብልሹ ቀሚሴን ለብሼ ስመለስ ምግቡ ቀርቧል።
– አልለቅ አለሽ አይደል? አይ ማርኮን…! ፍርዬ በቃ ቤትሽ ድረስ እናደርስሻለን…አለች ገነት ያለመልቀቁን ስታይ።

በወሬ ብዙም ሳልሳተፍ ምግቡን ለኮፍ ለኮፍ አድርጌ በደቤ የሚሾፍረው መኪና ውስጥ ገብተን መንገድ ጀመርን። ገነት ከፊት ስትቀመጥ እኔ ከልጆቹ ጋር ከኋላ ተሳፈርኩ። ማርኮን ተለጥፎብኛል።

የምኖርበትን ህንጻ አቅጣጫ ልክ እንደ አዲስ ሰው እየነገርኩት ቤቴ ደረስን።

ለምሳውም ለመሸኘቴም ምስጋና አቅርቤ እየተደናበርኩ ቤቴ ገባሁና ቀሚሴን አውልቄ የተበላሸው ቦታ ላይ ብቻ ውሃ እና ሳሙና አድርጌ የእጅ መታጠቢያው ላይ ማጠብ ጀመርኩ። አስቸገረኝ።

ይሄን ስጎ ከምንድነው የሰራችለት?

ብስጭት ብዬ እዛው ውሃ ውስጥ ዘፈዘፈኩትና ሳሎን ሄጄ ሶፋ ላይ ተዘርፍጬ እንደገና ማልቀስ ጀመርኩ።

ብዙ ሳይቆይ ስልኬ ሲርገበገብ ተሰማኝ። አየሁት።

ቴክስት።
ደቤ።

ከፈትኩት።

– የኔ ቆንጆ …በጣም ይቅርታ…እንድክስሽ አስራ ሁለት ሰአት ላይ የለመድናት ቤታችን እንገናኝ? ያቺ የምትወጃትን ነገር ይዤልሽ እመጣለሁ ይላል።

ህም።

ደግሜ አነበብኩት። ከሚያባብል መልእክቱ ይልቅ የማርኮን ልብ የሚያሟሟ ሳቅ ታየኝ። የገነት ‹‹ለመስቀል እንዳትቀሪ…አሪፍ ክትፎ ትበያለሽ›› ታወሰኝ። የአርሴማ እኔን ለመሳም መንጠራራት ውል አለኝ።

አስር ደቂቃ ቆይቼ –
– አልችልም…የእኔና አንተ ነገር አብቅቷል። ተወኝ….ብዬ መለስኩለትና ሌላ ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባት ስልኬን አጥፍቼ ወደ መታጠቢያ ቤት ተመለስኩ።

ቀሚሴን ከውሃው አውጥቼ አየሁት።

ስጎው ውልቅ ብሎ ወጥቷል።ቀሚሴ በደንብ ለቅቋል።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...