Tidarfelagi.com

”የቱ ይበልጣል?“

ዛሬ ነው። የቀጠርኩት ሰው እስኪመጣ ፣ ከከተማችን ቅንጡ የገበያ ማዕከሎች በአንዱ ውስጥ ያለ ግብ እዞራለሁ።

ለድሪቶነት ለሚቀርብ ሱሪ የሃምሳ ኪሎ ጤፍ ሂሳብ የሚያስከፍሉ ሞልቃቃ ቡቲኮች።
ርካሹ ኬክ በ 40 ብር የሚሸጥባቸው ካፌዎች።
አምስት ካሬ የማይሞላ የቄንጠኛ የግድግዳ ወረቀት ጥቅልን በሺህ ብር የሚያቀርቡ ሱቆች።

የቀጠርኩት ሰው እስኪመጣ ፣ ከከተማችን ቅንጡ የገበያ ማዕከሎች በአንዱ ውስጥ ያለ ግብ እዞራለሁ።

በመሃል ከድካም ብዛት እግሮቼ አልሄድ ሲሉኝ፣ ግድግዳና ጣራ ወደሌለው ሞባይልና ተከታዮቹን ወደሚሸጥ ሰፋ ያለ ሱቅ ጋር ደገፍ ብዬ ቆምኩ።

የአዲስ አበባ ፀሐይ የተጫወተበት ፊት ያለው ጎልማሳ ከሱቁ ባለቤት ጋር ጮክ ብሎ ይነጋገራል። ድርድር መሰለኝ።

እንዲህ ያወራሉ።

– አንቺ ደግሞ….. የማይረባ ከቨር እየሸጥሽልን በየ15 ቀኑ ታመላልሺኝ ጀመር አይደል…?
– ኧረ አባት እኛ የማይረባ እቃ አንይዝም….. እቃችን ሁሉ ብራንድ ነው
– ባክሽ ብራንድ ምናምን አትበይኝ… እዚህ ሱቅ ለከቨር ብቻ የከፈልኩት ገንዘብ ሌላ ሱቅ ያስከፍታችኋል
ልጅቱ በመሽኮርመም ሳቀችና ወሬያቸውን ቀጠሉ።
– ምን ሆነብህ የምር…?
– ባለፈው ሌላ ልጅ ነበረች መሰለኝ….. ሶስት መቶ ብር ከፍዬ የገዛሁት ከቨር ስልኬ አንዴ ሲወድቅ ስንጥቅጥቁ ወጣ…….ስልኬም ለጥቂት ነው የተረፈው……
– የእኛ እቃ?
-አዎ አልኩሽ እኮ….. የቻይና እቃ እየሸጣችሁልን… ለከቨሩም ከቨር መግዛት ሳያስፈልገን አይቀርም በዚህ አይነት

ልጅቱ እንደገና በመሽኮርመም የታጀበ ሳቅ ሳቀችና
– በቃ እኔ ዛሬ መርጬ እሰጥሃለሁ…… ከአራተኛ ፎቅ ብትጠለው እንኳን ከተሰበረ በኔ ነው…… ሃሃሃ
– ሃሃሃ….. እሺ አሳይኝ…

ከአምስት ወይ ስድስት በላይ የተለያዩ ሽፋኖችን በፍፁም ጥንቃቄ፣ በከፍተኛ ትዕግስት ሲመርጥ ይታየኛል። እኔ ለእሱ ደከመኝ፤ እኔ ለእርሱ ታከተኝ። በትጋቱ እየተገረምኩ የስንት ሺህ ብር ሞባይል ቢይዝ ነው ይሄ ሁሉ ጭንቀት? ብዬ እያሰብኩ ሳለ ወሬያቸውን እንደ ቅድሙ ጮክ ብለው ሲቀጥሉ ማዳመጤን ቀጠልኩ።

– እርግጠኛ ነሽ በቃ ይሄ ይሁን አይደል? (ጎማ የሚመስል እጅግ ወፍራም እና ቄንጠኛ ሽፋን ይዞ)
– አዎ አልኩህ እኮ….
– እሺ ስንት ነው….?
– እንግዲህ ኳሊቲ ነገር ብለሃል… ይሄ የቻይና አይደለም… የአውሮፓ ነው……
– እሺ ስንት ነው?
– አራት ከሃምሳ

አራት መቶ ሃምሳ ብር ለሞባይል ሽፋን…? ብዬ እያሰብኩ ሳለ ሰውየው ያለምንም ክርክር ኪሱ ገብቶ ገንዘብ ቆጥሮ ሲሰጣት አየሁ።
– አራት ከሰላሳ ነው ያለኝ… ይበቃሻል….
– እሺ… ካልክ ምን ይደረጋል….

ገንዘቡን ተቀብላ፣ እሱም አዲሱን የአውሮፓ ሽፋን ለስልኩ ሲያጠልቅ፣ የምጠብቀው ሰው ደውሎ ከህንፃው ውጪ እየጠበቀኝ እንደሆነ ሲነግረኝ ትቻቸሁ ወጣሁ።

ወጥቼ የጓደኛዬ መኪና ውስጥ ገባሁና ልንቀሳቀስ ስንዘጋጅ የሚከተለውን አየሁ።

ከብዙ መጨነቅና መጠበብ በኋላ አራት መቶ ሃምሳ ብሩን ሆጭ አድርጎ ቄንጠኛ የሞባይል ሽፋን የገዛው ጎልማሳ ሞተሩን አስነስቶ ቱ— ር— ሲል አየሁት።

“ሄልሜት” አላደረገም።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • Anonymous commented on April 21, 2018 Reply

    Yemigerm eyta

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...