Tidarfelagi.com

የተቸካዮች ምክር ቤት

ትምርት በጨረስን ማግስት እኔና ፍቅር ይልቃል ፈረንሳይ ለጋስዮን ኣካባቢ በዘጠና ብር ቤት መሰል ነገር ተከራይተን እንኖር ነበር፡፡ በየሳምንቱ ቅዳሜ ወደ ቪድዮ ቤት ጎራ እንላለን ፤ እነኩማር በዜማቸው ወፍ ሲያረግፉ ፤ እነ ቫንዳም በጫማ ጥፍያቸው ጥርስ ሲያረግፉ በመመልከት ራሳችን ዘና ለማረግ እንሞክራለን፡፡ ፊልም ዛሬ እንዲህ ጥንቡን ሊጥል ያኔ በጣም ብርቅ ነበር፡፡ ፊልም ሰሪዎች እንኳ እኛ ፊልም ለማየት የምንከፍለውን ያክል መስዋእትነት የሚከፍሉ ኣይመስለኝም፡፡ ያኔ ፊልም ማየት የጫማና የግስላ ሲጃራ ድብልቅ ሽታ የመቻል ቁርጠኝነት ይጠይቃል ፡፡ እናም በጊዜው የሁለት ሰኣት ፊልም ኣይተን የሁለት ሳምንት ጉንፋን ተረክበን ለመውጣት እንገደድ ነበር፡፡
ኣሁን ሳስበው፤ ከፊልሙ በላይ የፈረንሳይ ልጆች በፊልሙ ላይ ተመስርተው የሚሰጡት ኣስተያየት ያዝናናኝ ነበር፡፡ ኣንድ ቀን በጣም እጅ እጅ የሚል ፊልም ስናይ “ፓርላማውን ቀይርልን ፓርላማውን ቀይርልን ”ብለው ቀወጡት፡፡ ኣሰልቺ ፊልሞች” ፓርላማ “ተብሎ እንደሚጠሩ ያወኩት ያኔ ነው፡፡ ባለቪድዮ ቤቱም ኣብላጫውን ድምጽ ኣይቶ ሌላ ፊልም እንዲቀየር ውሳኔ ኣስተለለፈ፡፡
የተወሰኑ የተቃዋሚ ድምጾች በሚሰሙበት ሰሞን እንዳሰልቺ ፊልም ይታይ የነበረው ፓርላማ ዛሬ ይሄ ኣይነቱ ኣጠራር እንኳ የሚበዛበት ይመስለኛል፡፡ እኔን የሚገርመኝ የተወካዮች ምክር-ቤት የሚለውን ስም እስካሁን ይዞ መቆየቱ ነው፡፡ የሚወከልም ሆነ የሚማከር በሌለበት ይሄን ስም መሸከም ኣይከብድም? እንዲያው ቤቱ ስሙ ከብዶት ኣለመፍረሱ ይገርማል፡፡
ያገራችን ፓርላማ ኋላቀር መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ግን ከመቶ ኣመት በፊት ከነበረው የምክክር ባህል ኣንጻር ሲወዳደር እንኳ እጅግ ኋላቀር መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን??
“ብራናው ይገለጥ ተዘርግቶ በኣትሮኖሱ ላይ”::

1

በጅሮንድ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም ባድዋ ጦርነት ዋዜማ ስለነበረው ምክር ያይን እማኝ ሆነው የተመለከቱትን ጽፈውልናል፡፡ልቀንጨበው፤
“ራስ(መኮንን)…መኳንንታቸውን ሰብስበው የጦር ምክር ተደረገ፡፡ ራስ ኣሉላም ምክሩ ላይ ነበሩ፡፡
ሌሊት ሲነጋጋ ሸለቆ ለሸለቆ ወርደን እግንቡ ስር ተጠግተን በመሰላል እየተንጠላጠልን ከምሽጉ ውስጥ ገብተን(ጠላትን) እንፍጀው መንገዱን የራስ ኣሉላ ሰዎች ይመሩናል ተባለና ተቆረጠ፡፡ ይህንን ምክር መኳንንቱም የጦር ኣለቆችም ባለሟሎቹም ወደዱት፡፡ ኣንድ ሰው ብቻ በማእረጉ ዝቅተኛ የሆነ(የደራሲው ወንድም ኣብዩ)እየተቃወመ ተናገረ፡፡
ይህ ምክር ትልቅ ጉዳት ያመጣል ሰራዊታችንም በከንቱ ያልቃል ይልቅስ ታግሰን ቀንና ሌሊት ዘብ እየጠበቅን ውሃ ከምሽጉ ውጭ መቅዳት እንዳይችል እናድርግ …”ብሎ ተናገረ፡፡
ቀኛዝማች በሻህ ያብዩን ነገር ክፍኛ ነቀፉት…”ኣንተ ወረቀት ሲጻፍ ትመክራለህ ፡፡ፈርተህ እንደሆነ እሰፈር ዋል ፡፡ እኛ በሾተል እየቀነጠስን እንደኣይጥ እንፈጀዋለን ኣሉ….“
…ኣብዩ ከምንም ኣልቆጠራቸውም ፡፡ በትእግስት መለሰላቸው፡፡”ሰራዊታችን በከንቱ እንዲያልቅ በመደረጉ ኣዝናለሁ፡፡ እናንተ ስትሞቱ እኔ የቀረሁ እንደሁ ያን ጊዜ ፈሪ ተብየ እሰደባለሁ፡፡ “ይህ ተናገረና ወጣ፡፡”
(ኦቶባዮግራፊ፤ ገጽ 60)
የምክሩ ውሳኔ ምንም ይሁን ሰዎች በትልልቅ ኣገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሰብስበው ይሟገቱ እንደነበር እንረዳለን ፡፡ በምክሩ ላይ የተለያየ ማእረግ ያላቸው ብቻ ሳይሆን የተለያየ ኣመለካከት ያላቸው ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ በምክክሩ ኣብላጫውን ውሳኔ መቃወም ብቻ ሳይሆን ስብሰባ ረግጦ መውጣትም ይታወቅ ነበር ማለት ነው(ይህን ተናገረና ወጣ“ ተብሎ የተጻፈለትን ኣብዩን ኣስታውሱ )

2

ፕላውደን የተባለ የንግሊዝ ተጓዥ፤ በዘመነ መሳፍንት ማብቂያ በጉድሩ(ወለጋ)የተመለከተውን የሪፐብሊክ ኣስተዳደር እያደነቀ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡፡
•”ከሌሎች ጎሳዎች ጋር ስለሚኖረው ጉዳይ የሚወሰነው በጉባኤ ነው፡፡ ባደባባዩ ጉባኤ ለመታደም የሚፈልግ ሰው ሁሉ ክብ ሰርቶ ጦሩን ተደግፎ ከብቦ ቆሞ ይመለከታል፡ ፡ ሽማግሌዎች በሚያስደንቅ መንገድ ተራቸውን እየጠበቁ በሰላምና በጦርነት ዙርያ ይከራከራሉ።“
በራስ መኮንን የሸማ ድንኳን ውስጥ እና በጉድሩ መስክ ላይ የታየው ክርክርና ሙግት ፤ በዛሬው ፓርላማ ውስጥ ይታያል?ያለፈውን ስርኣት የመናፈቅ መብት በህገ መንግስቱ ይካተትልንማ!
ዲሞክራሲ ሂደት ነው ይባልልኛል፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ባገሬ ግን እንኳን ሲሄድ ሲንፏቀቅ ኣይታየኝም፡ ፡ የሚሄድ ቢሆን ኖሮ ከቀደምቶቻችን ውጥን ላይ ተነስቶ ዛሬ ትልቅ ደረጃ ደርሶ እናየው ነበር፡፡ የሚታየኝ ወንበር ላይ ተቸክሎ በድሃ እንባ የተቦካ እንጀራ የሚበላ ሰው ብቻ ነው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ሳይወጡ ሳይወርዱ ቀኝ እጃቸውን ብቻ እያወጡ እያወረዱ እንጀራ የሚበሉበት ቤት፤ “ የተወካዮች ምክር” ቤት መባሉ ያስቃል፡፡ ምናልባት” የተቸካዮች ምክር ቤት “ የሚለው ስም ይመጥነው ይሆን?

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...