Tidarfelagi.com

የተበረገደ ልብ

ልቤ ድው ድው። አይኔ ቦግ ቦግ። ጆሮዬ ቆም ቆም። ምላሴ ዝርክርክ አለብኝ፡- ሃብሉን ሲሰጠኝ።
ልብ እና ቁልፍ አንድ ላይ ያንጠለጠለ ሃብል ነው። አቤት ማማሩ። አቤት ማብረቅረቁ። ከዚያ ሁሉ ደግሞ አቤት ትርጉሙ!
‹‹የልቤ ብቸኛ ቁልፍ ያለው አንቺ ጋር ብቻ ነው ለማለት ነው። ገባሽ አይደል?›› አለኝ እኔ ረጅም ፀጉሬን በሁለት እጆቼ ከአንገቴ እያባረርኩ፣ እሱ ከጀርባዬ ቆሞ ልቡን እና ቁልፉን ሲያጠልቅልኝ።
ሳልሞት ያረግኩ መሰለኝ። እርግ ያልኩ!
‹‹አውቄያለሁ›› አልኩት በጡቶቼ መሃል ያለው ገደል ውስጥ የገባውን ባለቁልፍ ልቡን አጎንብሼ እያየሁ። ከልቤ በቅርብ ርቀት መቀመጡን እያስተዋልኩ- ‹‹አውቃለሁ›› አልኩት እየተስለመለምኩ።
ድል አድራጊነት ተሰማኝ።
ፈፁም ድል አድራጊነት ተሰማኝ።
አማንን መሳይ ቆንጆ፣ አማንን መሳይ ጎበዝ ወንድ ልቡን ከነቁልፉ እንዲሰጠኝ ማድረግ መቻሌ ኩራት ኩራት አለኝ። ይሄ ሁሉ ቁንጅና፣ ይሄ ሁሉ ጉብዝና፣ ይሄ ሁሉ ወንዳወንድነት የኔ አይደለም ወይ…ኩራት አይለኝም ወይ !
መሬትን በእግሬ ጨፍልቄ፣ ፀሃይን በቀኝ እጄ፣ ጨረቃን በግራ እጄ የጨበጥኩ ያህል ድል አድራጊነት ተሰማኝ።

ሳምንት አላለፈም። እንጃ አምስት ቀንም መሙላቱን።
እዛ አስቤዛ የማደርግበት ቤት ቲማቲም ልገዛ ስገባ የድሮ ፍቅረኛውን አገኘኋት። ስም ይንሳት እና ስሟ ቤተልሄም ነው። ‹‹ቤቲ በይኝ›› ትለኛለች ደሞ።አርባ ቦታ ይበታትናትና። ቡትቶ ነገር።
ቢሆንልኝ ‹‹አንቺ ቡትቶ›› ብላት ደስ ይለኛል። በየቦታው ከፈላ ቤት ለምን እኛ አስቤዛ የምናደርግበት ቦታ እንደምትመጣብኝ አይገባኝም። ሰፈሯ አቧሬ ነው።አቧራ ይድፋባትና። ታዲያ ነገር ፍለጋ ካልሆነ ከዚያ ድረስ ለቲማቲም እና ሽንኩርት ጉርድ ሾላ ድረስ ምን ያመጣታል? ጎደሎ!
እንደናፈቀችኝ ሁሉ ሳመችኝ ። በኔ በኩል ያመለጣትን ፍቅሬን ልትስም ነው….?በዙሪያ ጥምጥም ከንፈሩን ልታገኝ ነው….?ብነክሳት ደስ እያለኝ እሷን የምስም አስመስዬ፣ እንደ ሳትኳት ሁሉ በዙሪያዋ ያለውን አየር ሳምኩ። እንኳን እሷ ፤ የከበበችው አየር ደስ የማይል ነገር ይሸታል።
‹‹በይ እሺ…›› ብዬ ወደ ቲማቲሜ ልሄድ ስል ፤ ‹‹እንዴ…ቆይ ቆይ አንዴ…››አለችና እጄን አፈፍ አደረገችው። እጇ እንደገበሬ እጅ ይሻክራል። አማንዬ ምንሆኖ ነው ከዚህች ባላገር ጋር ላይ ታች ሲል የኖረው?
ምን ሲል ወደዳት…?መተት ብታደርግበት ነው። ቡትቷም መተተኛ።
ዞሬ ሳልጨርስ ፤ ‹‹ ቆይ አንዴ…ሃብልሽ…እስቲ ሃብልሽን ልየው!›› ብላ ልብ እና ቁልፍ ሃብሌን ልትጎትት ያንን የገበሬ እጇን ስትሰድ ባላሰብኩት ፍጥነት ገፋኋት።
‹‹እንዴ ምን ሆነሻል?›› አለችኝ::
‹‹ምንም…እንዳትበጥሺብኝ ነው…ስፔሻል ሃብል ነው›› ሃብሌን ሁለት እጆቼን ጋሻ አስመስዬ እንደጋረድኩ መለስኩላት::
‹ላየው እኮ ነው…ለምን እበጥሰዋለሁ…?››ሳቀችብኝ። በዚያ ቢጫ ቀለም የተቀባ በሚመስል ጥርሷ ሳቀችብኝ።
ነደደኝ።
‹‹ አማንዬ ነው የሰጠኝ…ዝም ብሎ ሃብል አይደለም…እይው…ቆይ …አትንኪው እዛው ሆነሽ እይው…ልብ አለው። አብሮ ደግሞ ምን እንዳለው ታውቂያለሽ..?›› አልኳት ጠብረር -ገንተር ብዬ ጠጋ እያልኳት::
‹‹ቁልፍ?›› አለችኝ አፍታም ሳትቆይ።
ደነገጥኩ።
‹‹እንዴት አወቅሽ?›› አልኳት ብልጭ እያለብኝ።
መልስ ትሰጠኛለች ብዬ ስጠብቅ ለቢትልስነት ትንሽ የቀረው አስቀያሚ ሹራቧን በግድ ከአንገቷ ወደ ጡቶችዋ እየገፋች ምዝዝ አድርጋ አወጣችው።
የኔን ሃብል። ራሱን የኔን ሃብል። ባለልብ እና ባለቁልፉን። ቁጭ ራሱን።
ዞ…ር… አለብኝ።
‹‹ ሃ ሃ ሃ! በማርያም ልገምት ! ሲሰጥሽ ምን አለሽ ….?’የልቤ ብቸኛ ቁልፍ ያለው አንቺ ጋር ብቻ ነው ለማለት ነው’ አለሽ? ›› አለችኝ የሚያነፍር ሳቋን ሳታቋርጥ።
‹‹እ…አዎ…በምን አወቅሽ?..››
‹‹አንቺ ደግሞ አሪፍ መስለሽ ገና እርጥብ ነሽ ልበል ..!ለኔም እንደዛ ብሎ ስለሰጠኝ ነዋ!››
‹‹ አማንዬ…አማን…ይሄን ሃብል ላንቺም እንዲህ ብሎ…ልክ እንደኔ …ልክ እኔን እንዳለሽ ብሎ ሰጠሽ…?›› አልኳት እየተንተባተብኩ። እፍረቴን ትቼ ቡትቶ ፊት ላለቅስ ነው መሰለኝ።
‹‹ወይ የኔ እናት…!ከኔ በፊት ላለችውም ልጅ…ማነው ስሟ ያቺ…ሃዊ ናት ሂዊ…?ውሃ ይብላት እና…ይህንኑ ሃብል እንዲህ ብሎ ሰጥቷት ነበር። አሳይታኝ ነበር።›› አለችኝ መሳቅ አቁማ።
ሳላሳዝናት አልቀረሁም።
የምንቃት ቡትቶ፣ የምጠየፋት ቡትቶ ለኔ ትዘንልኝ!? ወይኔ ልጅት! አማንዬ…ይሄ አማን.. ቡትቶ ለኔ እንድታዝን የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ይቀላቅለኝ…?
ይድፋው። ክልትው ያድርገው።
ቤቲ ሳትቆይ የምትገዛውን ነገር ገዝታ ሄደች። እኔ ግን ነፍዤ ቀረሁ። እግሬ ከአስቤዛ ቤቱ መሬት ጋር የተለሰነ ይመስል ተገትሬ ቀረሁ።
በስተኋላ ፤ ወደ ቤቴ የመመለስ ጉልበት አግኝቼ ስመለስ የማስበው ግን ይሄን ብቻ ነበር።
‹‹ለዚህ ሁሉ ሴት ቁልፉን የሚሰጥ ከሆነ ልቡን መቆለፍ ምን አስፈለገው?
በርግዶ አይተወውም? የሚበረግድ ይበርግደውና…ይሄ ቁሌታም። የወንድ ሸርሙጣ….
አማን ብሎ ሰው። ጆፌ አሞራ ይልቀቅበትና….››

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...